ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የጣሊያን ብሔራዊ የአየር መንገድ የሥራ አስፈፃሚዎችን እና ሠራተኞችን በቫቲካን ተቀብለው ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የጣሊያን ብሔራዊ የአየር መንገድ የሥራ አስፈፃሚዎችን እና ሠራተኞችን በቫቲካን ተቀብለው  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ አውሮፕላኖች ጦርነትን እና ጥፋትን ሳይሆን ሰላምን ማምጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የጣሊያኑ ብሔራዊ የአየር መንገድ ITA በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ወቅት ለሚያበረክቷቸው አገልግሎቶች ምስጋናቸውን አቅርበው፥ አውሮፕላኖች በጦርነት ወቅት ሞትን እና ጥፋትን እንዲያስከትሉ በመዋላቸው የተማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ አራቱ የአፍሪካ አገራት የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው ከሃያ ቀናት በፊት ከጣሊያን ብሔራዊ አየር መንገድ እና ከሉፍታንሳ ግሩፕ ከተውጣጡ የሥራ አስፈፃሚዎች እና ሠራተኞች ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል።

ቅዱስነታቸው የጣሊያን አየር መንገድ “ITA Airways” እና የቀድሞው “አሊታሊያ” ከር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ጀምሮ ልዩ ልዩ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ሐዋርያዊ ጉብኝቶች በማመቻቸት ላደረጉት አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው እንደዚሁም የክብር አጃቢዎቻቸውን እና ከእርሳቸው ተጉዘው ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ለሚዘግቡ ጋዜጠኞች የተረጋጋ ድባብ የሚፈርትጠሩ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችንም  አመስግነዋል።

የጣሊያን አየር መንገድ “ITA Airways” የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የውጭ አገራት ሐዋርያዊ ጉብኝቶች በቤተሰብ ድባብ የተሞላ፣ ከአክብሮት ከታማኝነት ጋር የተቆራኘ እንዲሆን ይረዳል ብለዋል።

“እናንተን መገናኘት ለዚህ ውድ አገልግሎት የራሴን እና የቅድስት መንበር አድናቆት እና ምስጋናን ለመግለጽ ዕድል ይሰጠኛል” ብለዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በረራዎች በዘመናዊው ማኅበረሰብ ውስጥ ለቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ተልዕኮ አንጸባራቂ ምልክት እንደሚሆኑ ተናግረዋል፣ “ምክንያቱም ዘወትር ወደ ልዩ ልዩ አገራት የሰላም መልዕክተኛ ሆኖ ስለሚጓዝ ነው” ብለዋል።

“ሐዋርያዊ ጉዞአቸውም ዘወትር የውይይት፣ የእርስ በርስ ግንኙነት እና የወንድማማችነት ድልድዮች ናቸው” ብለዋል።

ሆኖም አውሮፕላኖች ብዙውን ጊዜ በጦርነት ውስጥ ጥፋትን እና ፍርሃትን ለማስከተል ጥቅም ላይ እንደሚውሉ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዩ 14ኛ፥

“አውሮፕላኖች የጦርነት ሳይሆን ሁልጊዜ የሰላም መልዕክተኞች መሆን እንዳለባቸው በማሳሰብ “ማንም ሰው የሞት እና የጥፋት ዛቻ ከሰማይ ሊመጣ ይችላል ብሎ መፍራት የለበትም” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የዓለም ጦርነቶችን፣ የአየር ላይ የቦምብ ድብደባዎችን እና እስከ ዛሬ የቀጠሉትን ሌሎች ግጭቶችንም እና አስታውሰዋል።

“በሃያኛው ክፍለ ዘመን ከተከሰቱ አሳዛኝ ተሞክሮዎች በኋላ የአየር ላይ የቦምቦች ጥቃቶች ለዘላለም መከልከል ነበረባቸው!” ብለው፥ የቴክኖሎጂ ልማት በአዎንታዊነት ለጦርነት አገልግሎት እየዋለ እንደሆነ በመግለጽ፥ “ይህ ዕድገት ሳይሆን ወደኋላ መመለስ ነው!” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በማጠቃለያቸው፥ የወንጌልን ሰላም ለማሰራጨት በሚያደርጉት ጥረት የጣሊያን አየር መንገድ “ITA Airways” ሠራተኞች ላደረጉላቸው እገዛ ምስጋናቸውን አድሰዋል።

“አሁን ባለው ሁኔታ ውስጥ በሰማይ ላይ የሰላም መንገዶችን መጓዝ የበለጠ አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል” ብለው እናም ጌታ በአደራ በሰጠኝ ተልዕኮ መካከል በእናንተ ላይ መተማመን እንደምችል ስለማውቅ አመሰግናችኋለሁ” ብለዋል።

24 Mar 2026, 14:59