ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጤና ለጥቂቶች የተሰጠ ቅንጦት ሊሆን አይገባም ማለታቸው ተገለጸ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ረቡዕ ዕለት መጋቢት 09/2018 ዓ.ም “ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ሊደረስበት የሚገባ የቴክኒክ ግብ ብቻ አይደለም፤ እራሳቸውን ፍትሃዊ ብለው ለመጥራት ለሚፈልጉ ማህበረሰቦች የሞራል ግዴታ ነው” ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል፣ ነገር ግን ኢ-ፍትሃዊነት የግጭት መንስኤ እንዳይሆን ለመከላከል ጭምር በጤና መስክ የእኩል ተደራሽነትን ማረጋገጥ ተገቢ ነው ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በአውሮፓ የጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት፣ የዓለም ጤና ድርጅት (የአውሮፓ ክልል) እና የጣሊያን ጳጳሳት ጉባኤ በቫቲካን በተካሄደ ስብሰባ ላይ ባዘጋጁት “ዛሬ ባልንጀራዬ ማነው?” በተሰኘው መሪ ቃል በተዘጋጀው ኮንፈረንስ ላይ ባደረጉት ንግግር ነበር ይህንን የገለጹት።
ሁለተኛው “የዓለም የጤና ድርጅት የአውሮፓ የጤና እኩልነት ሁኔታ ሪፖርት” በተወጣበት ቀን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሰነዱ “በአውሮፓ ውስጥ ብዙ ድሆች እና ተገልለው የሚኖሩ ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ሁኔታዎች ላይ ትኩረት እንደ ሚስብ ገለጸዋል።
በብዙ የአውሮፓ አገራት በጤና አጠባበቅ መስክ ያለው ኢ-ኩልነት እየጨመረ መሆኑን በመጥቀስ፣ በተለይም ለወጣቶች የአእምሮ ጤና አፋጣኝ ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
የጤና አጠባበቅ እና ማህበራዊ ሰላም
“ጤና ለጥቂቶች የቅንጦት ተግባር ሊሆን አይችልም” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ተናግረዋል። “ለማህበራዊ ሰላም አስፈላጊ ሁኔታ” መሆኑንም አጉልተው ገልጸዋል።
“የጤና አጠባበቅ ለተጋላጮች ተደራሽ መሆን አለበት፣ ክብራቸው የሚፈልገው ብቻ ሳይሆን ኢ-ፍትሃዊነት የግጭት መንስኤ እንዳይሆን ለመከላከልም ጭምር ነው” ብለዋል።
ከወንጌል፣ ከዘፍጥረት መጽሐፍ፣ ከቅዱስ አውጉስጢኖስ ጽሑፎች እና ከቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያነኛ ቋንቋ "ፍራቴሊ ቱቲ" (ሁላችንም ወንድማማቾች ነን) ከተሰኘው ጳጳሳዊ መለእክት የተወሰዱ ምንባቦች ላይ ካሰላሰሉ በኋላ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ “ርቀት፣ ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮች እና የሌሎችን ስቃይ አለማየት ወደ ግድየለሽነት ይመራናል” ብለዋል። ሆኖም ግን ሁሉም ወንዶችና ሴቶች፣ በተለይም ክርስቲያኖች፣ ትኩረታቸው በሚሰቃዩት ላይ እንዲያተኩር ተጠርተዋል፤ በብቸኝነት ስሜት፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተገለሉ እና “እንደተረሱ” ተደርገው በሚቆጠሩት ላይ። ምክንያቱም ያለእነሱ፣ በሰው ልጅ ላይ የተመሰረቱ ፍትሃዊ ማህበረሰቦችን መገንባት አንችልም ሲሉ ተናግረዋል።
አንድ ላይ ብቻ፣ “ለሁሉም ሰው የሚንከባከብ፣ ደህንነት እና ሰላም ለሁሉም ጥቅም የሚያብብበት የአንድነት ማህበረሰቦችን መገንባት እንችላለን” ያሉ ሲሆን አክለውም “ለሌሎች ሰብአዊነት መጨነቅ የራሳችንን ሕይወት ሙሉ በሙሉ እንድንኖር ይረዳናል”።
የክርስቲያን የአኗኗር ዘይቤ የሳምራዊነትን መንፈስ ያንፀባርቅ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የቤተክርስቲያኗን ሚና በማረጋገጥ ሁልጊዜ “ለሰብአዊነት እድገት እና ለአለም አቀፍ ወንድማማችነት አገልግሎት” ላይ ያለውን ሚና አረጋግጠዋል።
በአውሮፓ እና በመላው ዓለም ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር "ዛሬ በጤና አጠባበቅ ረገድ በተለይም በጣም ተጋላጭ ለሆኑ ህዝቦች ድጋፍ በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወት እንደሚችሉ" ተናግረዋል።
በመጨረሻም፣ ክርስቲያኖችን "የክርስትና አኗኗራችን ሁልጊዜ ይህንን የወንድማማችነት፣ የ'ሳምራዊ' መንፈስ - አቀባበል፣ ደፋር፣ ቁርጠኛ እና ደጋፊ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን አንድነት እና በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እምነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን እንዲያረጋግጡ ጥሪ አቅርበዋል።
