ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሞናኮ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት መጀመራቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቅዳሜ መጋቢት 19/2018 ዓ. ም. ጠዋት በሮም ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ከሃያ ላይ ከቫቲካን የሄሊኮፕተር ማረፊያ ወደ ግዛት ዋና ከተማ ሞናኮ ጉዞ መጀመራቸውን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው አስተባባሪ ክፍል አስታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14 በሞናኮ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ጉብኝት ሲሆን በዘመናችን ውስጥ አንድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ትንሿ የግዛት ከተማ የሚያደርጉት የመጀመሪያ ጉብኝት እንደሆነ ተነግሯል። የካቶሊክ እምነት የመንግሥት ሃይማኖት ወደ ሆናት ሞናኮ የሚደርሱት በአገሩ አቆጣጠር ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት እንደሚሆን ተገልጿል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከጣሊያን የግዛት ክልል ሲወጡ ለጣሊያን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ለክቡር አቶ ሴርጂዮ ማታሬላ በላኩት የቴሌግራም መልዕክት፥ በሞናኮ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓላማ የክርስትና እምነት ምስክርነትን እና የጋራ ጥቅም ግንባታን ለማበረታታት እንደሆነ ገልጸው፥ እንዲሁም ለጣሊያን ሕዝብ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ዕድገትን በጸሎት ተመኝተዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሞናኮ ሐዋርያዊ ጉብኝት ከዘጠኝ ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ አራት ዋና ዋና ዝግጅቶች እንዳሉት፥ እነዚህም የሞናኮ ልዑል አልበርት ዳግማዊን በቤተ መንግሥታቸው መጎብኘት፤ ከአገሪቱ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ጋር በጽንሰተ ማርያም ካቴድራል ውስጥ መገናኘት፣ ከወጣቶች እና ከንዑሠ ክርስቲያን ጋር በቅዱስ ዴቮታ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ባለው አደባባይ መገናኘት እና በሉዊስ ዳግማዊ ስታዲየም በተዘጋጀውን ሥፍራ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከመሩ በኋላ በምእመናን መካከል አጭር ጉብኝት እንደሚያደርጉ ታውቋል።
ቅዱስነታቸው በሞናኮ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከፈጸሙ በኋላ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር በግምት ከሰዓት በኋላ በአሥራ አንድ ሰዓት ከአርባ አምስት ላይ ወደ ቫቲካን እንደሚመለሱ የጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመላክቷል።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀደም ብሎ ባደረጉት ንግግር፥ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ለአካባቢው ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ አዲስ ጉልበት እንደሚሰጥ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ይህም በተለይም ተጋላጭ ለሆኑት ትኩረት በመስጠት የፍጥረት እንክብካቤ፣ የሰው ልጅ ሕይወትን ከጉዳት መጠበቅ እና ዓለም አቀፍ አንድነትን ማስፋፋት ለሚሉት አስቸኳይ ጉዳዮች የጋራ ቁርጠኝነትን እንደሚያጠናክር አስረድተዋል።
