ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ እምነት ለሚሰቃዩ ሰዎች ዓይኖቻችንን እንድንከፍት ያግዘናል ሲሉ አስገነዘቡ
ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለምዕመናን ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! ወደ አራተኛው የዐቢይ ጾም እሑድ የሚወስደን የዛሬው የቅዱስ ወንጌል ንባብ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ዕውር የነበረን ሰው መፈወስ ይተርካል (ዮሐ. 9:1-41)። በምሳሌያዊ አነጋገር ወንጌላዊው ዮሐንስ ስለ መዳን ምስጢር ይነግረናል፡- በጨለማ ሳለን የሰው ልጅ በጨለማ ውስጥ ሲመላለስ (ኢሳ. 9:2) ዕውራን እንዲያዩ እና ሕይወታችን እንዲበራ እግዚአብሔር ልጁን የዓለም ብርሃን አድርጎ ላከው።
ነቢያት በትንቢታቸው መሲሑ የዕውሮችን ዓይን እንደሚከፈት አስታውቀው ነበር (ኢሳ. 29:18፤ 35:5፤ መዝ. 146:8)። ኢየሱስ ራሱ ‘ዕውሮች ያያሉ (ማቴ. 11:5) በማለት የተልዕኮውን ትክክለኛነት አረጋግጧል። እንደዚሁም ‘እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ’ (ዮሐ. 8:12) በማለት ራሱን ገለጠ። በእርግጥ ሁላችንም ከተወለድንበት ጊዜ ጀምሮ ዕውሮች ነን ማለት እንችላለን። ምክንያቱም የሕይወትን ጥልቅ ምስጢር በራሳችን ብቻ ማየት አንችልም። ለዚህም ነው እግዚአብሔር ሥጋን በመልበሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በጸጋው እስትንፋስ የተቀረጸው ሸክላ ሰውነታችን ራሳችንን፣ ሌሎችን እና እግዚአብሔርን በእውነት እንድናይ የሚረዳንን አዲስ ብርሃን እንዲያገኝ ያደረገው።
ከዘመናት ጀምሮ እስከ ዛሬ የዘለቀው አስተሳሰብ፥ በእምነት መኖር ማለት በጨለማ ውስጥ መጓዝ፣ አስተሳሰብን መካድ እና ጭፍንነት ማለት እንደሆነ የሚገልጹ አስተያየቶች እስከ ዛሬ ድረስ ተስፋፍተው ቀጥለዋል። ሆኖም ግን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስንገናኝ ዓይኖቻችን እንደሚከፈቱ ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል። በእርግጥ የሙሴ የሕግ መምህራን የተፈወሰውን ዕውር ሰው፥ ‘ታዲያ ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?’ ሲሉ አጥብቀው ይጠይቁታል (ዮሐ. 9፡10)። ‘ኢየሱስ ዓይኖችህን እንዴት ከፈታቸው?’ ሲሉ እንደገናም ጠየቁት’ ((ዮሐ. 9፡ 26)።
ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! እኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ተፈውሰናል። እምነታችንን በተከፈቱ ዓይኖች በተግባር እንድንኖር ተጠርተናል። እምነት ስውር ተግባር አይደለም። ምክንያታዊነትን መተው ወይም እይታችንን ከዓለም እንድናዞር የሚያደርገን አይደለም። ወይም ከሃይማኖታዊ እርግጠኛነት ማፈግፈግ አይደለም። በተቃራኒው እምነት ማለት ነገሮችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዓይኖች እንድናያቸው ይረዳናል። ‘በእርሱ የማየት ዘዴ መሳተፍ ማለት ነው’ (ሉመን ፊዴይ፣ 18)። በዚህ መልኩ እምነት ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳደረገው በተለይም የሌሎችን ስቃይና የዓለምን መከራ ለመመልከት ዓይኖቻችንን እንድንከፍት የቀረበልን ግብዣ ነው።
በተለየ መንገድ ዛሬ የሰው ልጅ በልቡ ውስጥ ብዙ ጥያቄዎች አሉት። በጊዜያችንም ውስጥ የፍትሕ መጓደል፣ አሳዛኝ ዓመፅ እና ስቃይ መኖራቸውን እንገነዘባለን። በመሆኑም እምነታችን ንቁ፣ ትኩረትን የሚስብ እና ትንቢታዊ መሆን ያስፈልጋል። ዓይኖቻችን የዓለም ጨለማን ለማየት የተከፈቱ፣ ለሌሎች ሰላምን፣ ፍትህን እና አብሮነትን ለማምጣት የሚተጉ፥ የወንጌልን ብርሃን ለሌሎች ለማምጣት የቆረጡ መሆን አለባቸው።
የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን የልባችንን ዓይን እንዲከፍትልን፣ ለእርሱ በትህትና እና በድፍረት የምንመሰክርበትን ኃይል ከልጇ እንድታማልደን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንለምን።”
