ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ቆሞ ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሁድ መጋቢት 6/2018 ዓ. ም. ባቀረቡት ጥሪ፥ አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር ለሚያደርጉት ጦርነት ተጠያቂ የሆኑት በሙሉ ጦርነትን አቁመው እንደገና ውይይት እንዲጀምሩ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በሚገኙት ክርስቲያኖች እና በጎ ፈቃድ ባላቸው ሰዎች ስም አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሁድ መጋቢት 6/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላደረሱ በኋላ ባሰሙት ንግግር “ዓመፅ ሰዎች የሚጠብቁትን ፍትህ፣ መረጋጋት እና ሰላም ሊያመጣ አይችልም” ብለው፥ የመካከለኛው ምሥራቅ ሕዝቦች ለሁለት ሳምንታት በአስከፊ ጦርነት ሲሰቃዩ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
“በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ሰዎች ተገድለዋል፣ ሌሎች ብዙዎች ቤታቸውን ጥለው ለመውጣት ተገደዋል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና የመኖሪያ አካባቢዎች በጦርነት መጠቃታቸውን ገልጸው፥ በጦርነቱ ምክንያት የሚወዷቸውን ሰዎች ያጡትን በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል።
በሊባኖስ ውስጥ ባለው ሁኔታ ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ለሊባኖስ ሕዝብ የጋራ ጥቅም ሲባል እየደረሰ ላለው ከባድ ቀውስ ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማግኘት የሚረዱ ውይይቶችን እንደሚያደርጉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ሲቪሎች በኢራን ጦርነት ከፍተኛ ጭንቀት ይሰማቸዋል
ኢራን የተሳተፈችበት እና በመካከለኛው ምሥራቅ እየተባባሰ የመጣው ጦርነት በኢራን እና በሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ ሲቪሎችን ክፉኛ መጉዳቱ ተመልክቷል።
ባለፈው ዓርብ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኝ የጤና ማዕከል ላይ በፈጸመችው ጥቃት አሥራ ሁለት የሕክምና ሠራተኞች መገደላቸው ይታወሳል። የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊው ጥቃቱን አውግዘው “በንጹሐን ሰዎች ላይ የደረሰው ሞት ተቀባይነት የሌለውም” ሲሉ ገልጸውታል። የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጦርነቱ ከተቀጣጠለ ወዲህ በእስራኤል የአየር ጥቃት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ800 በላይ እንደ ሆነ እና ከ800,000 በላይ ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን አስታውቋል።
እስራኤል ይበልጥ ዒላማ አድርጋ ጥቃት የምትፈጽምባቸው ቦታዎች ሂዝቦላህ ጥቃቶችን ለማስተባበር የጦር መሣሪያዎችን በሚያከማችባቸው ቦታዎች ላይ መሆኑን ትናገራለች። ሂዝቦላህ ጦርነቱ ከተጀመረ ብዙም ሳይቆይ ኢራንን ለመደገፍ ወደ ሰሜን እስራኤል ሮኬቶችን መተኮስ መጀመሩ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ያለፈው ቅዳሜ በኢራን ውስጥ ቢያንስ 15 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። የኢራን ባለስልጣናት፣ የኢራን ቀይ ጨረቃ እና በርካታ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ከአሜሪካ እና እስራኤል ወረራ ጀምሮ ከ1,230 እስከ 1,300 የሚደርሱ ሲቪሎች እንደተገደሉ ቢገምቱም አሃዞቹ በተናጥል አልተረጋገጡም።
እጅግ አስከፊ ከሆኑ ክስተቶች መካከል አንዱ ጦርነቱ በተጀመረበት ማለትም ቅዳሜ የካቲት 21/2018 ዓ. ም. በሚናብ በሚገኝ አንደኛ ደረጃ የሴቶች ትምህርት ቤት የተፈጸመ ጥቃት እንደ ነበር ታውቋል። የኢራን ሚዲያዎች በጥቃቱ ከ168 እስከ 180 ሰዎች እንደተገሉ እና ከእነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ ልጆች መሆናቸውን አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ክልሉ ውጥረቶች መስፋፋታቸው ቀጥለዋል። የሳውዲ አረቢያ የመከላከያ ሚኒስቴር በሪያድ እና በምሥራቅ ክልል ሰባት ድሮኖችን አግኝቶ ማውደሙን ተናግሯል። በዱባይ እና በኳታር የሚገኙ ባለስልጣናት እሁድ ዕለት በሰጡት መግለጫ በአየር መከላከያ ላይ ጣልቃ ገብነት እንደተከሰተ ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፥ ኩዌት ደግሞ አንድ ድሮን በዓለም አቀፍ አየር ማረፊያው ላይ የራዳር ሥርዓቶችን ማውደሙን ተናግራለች። የእስራኤል ጦር እሁድ ማለዳ ከኢራን የተወነጨፉ ሚሳኤሎች መኖራቸውን ተናግሯል። የአደጋ ጊዜ ማሳሰቢያ አገልግሎት ጥቃቱ በማዕከላዊ እስራኤል ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ዘግቧል።
በዚህ ሁሉ መካከል በባግዳድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ኢራን ቅዳሜ ዕለት የተኮሰችው ሚሳኤል የኤምባሲውን ግቢ ከመታ በኋላ ዜጎች ኢራቅን ለቀው እንዲወጡ አዲስ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል። ኤምባሲው በመግለጫ “የአሜሪካ ዜጎች አሁኑኑ ኢራቅን ለቅቀው መውጣት አለባቸው” ሲል አሳስቧል።
