የእግዚአብሔር አገልጋይ እህት ስታኒስላዋ ሳሙሎውስካ፤ የእግዚአብሔር አገልጋይ እህት ስታኒስላዋ ሳሙሎውስካ፤  

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ስድስት የቅድስና ጉዳዮች ጥናት ወደፊት እንዲቀጥል ማድረጋቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የቤተሰብ አባት የነበረ ጣሊያናዊ፣ ለእምነት ሲል ሕይወቱን ለሞት የሰጠ ሌላ ሰው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያንን ያገለገለ የስፔን ገዳማዊን ጨምሮ የበርካታ ሰዎች የቅድስና ጉዳይ ጥናት ወደ ፊት እንዲቀጥል ማድረጋቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰኞ መጋቢት 14/2018 ዓ. ም. ጠዋት የቅድስና ጉዳዮች ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ የሆኑትን ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሴሜራሮን በቫቲካን ተቀብለው ስድስት ግለሰቦችን ለብጽዕና የሚያበቃቸውን ድንጋጌዎችን እንዲያወጡ ፈቃድ ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 17/1805 ዓ. ም. በጣሊያን መዲና ሮም የተወለዱት የሮማዊት ቤተ ክርስቲያን እና የአልባኖ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ለሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዶቪኮ አልቲየሪ የሕይወት መስዋዕትነት እውቅና ሰጥተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሉዶቪኮ አልቲየሪ በጣሊያን ኮረብታማ ከተማ አልባኖ ላዚያሌ ላይ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በነሐሴ 11/1867 ዓ. ም. ማረፋቸው ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው አራት ገዳማውያን እና አንድ የቤተሰብ አባት የነበሩት በእምነታቸው ላሳዩት ከፍተኛ ገድል   እና በጎነቶች እውቅና ሰጥተዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 13/1886 ዓ. ም. በአየርላንድ ባሊሞ ከተማ የተወልዱ የሀገረ ስብከት ካህን፣ የወንዶች መንደር መሥራች የነበሩ እና ግንቦት 15/1948 ዓ. ም. በጀርመን በርሊን ከተማ  ያረፉት የእግዚአብሔር አገልጋይ ኤድዋርድ ጆሴፍ ፍላናጋን፤

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 30/1903 በፈረንሳይ ሊዮን ከተማ የተወለዱ የሀገረ ስብከት ካህን፣ የ የእመቤታችን ማርያም ቡድኖች ማኅበር መሥራች፥ “የትንሣኤ እመቤታችን ማርያም ወንድማማችነት ዓለማዊ ተቋም መሥራች እና መስከረም 18/1996 ዓ. ም. በቦውቫስ ያረፉት የእግዚአብሔር አገልጋይ ሄንሪ ካፋሬል፤

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥር 30/1865 ዓ. ም. በዎሪቲ፣ በአሁኗ ፖላንድ የተወለደች የቅዱስ ቪንሰንት ደ ፖል የሴቶች የበጎ አድራጎት የገዳማውያት ማኅበር ተከታይ ነበረች እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታህሳስ 6/1950 ዓ. ም. በላቲን አሜሪካ አገር ጓቲማላ ያረፈች የእግዚአብሔር አገልጋይ እህት ስታኒስላዋ ሳሙሎውስካ፤

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 7/1916 ዓ. ም. በስፔን ሴቪል ከተማ የተወለደች፣ የመለኮታዊ ልብ አገልጋዮች ማኅበር ተከታይ የነበረች እና ህዳር 12/1977 ዓ. ም. በሳንሉካር ላ ማዮር ከተማ ያረፈች የእግዚአብሔር አገልጋይ እህት ማርያ ዶሎሬስ እና፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 15/1909 ዓ. ም. በጣሊያን ሞንቴባራንዞን የተወለደ፥ ታማኝ እና የቤተሰብ አባት የነበረ ሰኔ 22/1965 ዓ. ም. እዚያው ያረፈ የእግዚአብሔር አገልጋይ ጁሴፔ ካስታኜቲ ሲሆኑ፥ ለእምነታቸው ሲሉ ሕይወታቸውን ለሞት አሳልፈው በመስጠት ከፍተኛ ገድል የፈጸሙ እነዚህ እጩዎች በድንጋጌው መሠረት የተከበሩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ወይም ብጹዓን የሚያሰኛቸውን የቤተ ክርስቲያን ማዕረግ እንደሚያገኙ ታውቋል።

 

24 Mar 2026, 15:05