ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ “በጦርነት መካከል ሕይወትን ከአደጋ መከላከል አለብን” ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሕይወት ቅድስናን በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ዓለማችን በጦርነት ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ሕይወት ከተጸነሰበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተፈጥሯዊ ፍጻሜው ድረስ መንከባከብ አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህን ማሳሰቢያ የሰጡት ረቡዕ መጋቢት 16/2018 ዓ. ም. ጠዋት በቫቲካን ለታዳሚዎቻቸው ባቀረቡት ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ የሕይወት ቅድስና ቀንን በማስታወስ ለፖላንድ ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት እንደ ነበር ትውቋል።
በፖላንድ የሕይወት ቅድስና ቀን በየዓመቱ መጋቢት 16 የሚከበር ሲሆን፥ የተጀመረውም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2004 ዓ. ም. ከቤተ ክርስቲያኗ ዓመታዊ የብስራተ ገብርኤል በዓል ጋር እንዲገጣጠም ተብሎ እንደ ሆነ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለፈረንሳይኛ ተናጋሪ ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ወንጌልን በቅንዓት እንዲሰብኩ በማሳሰብ፥ ክርስቲያኖች በሙሉ ሰላማዊ ዓለምን ለመገንባት ራሳቸውን በንቃት እንዲያዘጋጁ በመርዳት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህንን ጥሪያቸውን ለምዕመናን በሙሉ በማስተላለፍ፥ ለአረብኛ ተናጋሪ ምዕመናንም ባስተላለፉት መልዕክት እንደዚሁ፥ “እያንዳንዱ ክርስቲያን በፍቅር የተሞላ ደቀ መዝሙር እና ወንጌልን በዓለም ዙሪያ ለማወጅ ደፋር የኢየሱስ ክርስቶስ መልዕክተኛ እንዲሆን ተጠርቷል” ሲሉ አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ በዕለቱ ተከብሮ የዋለውን የብስራተ ገብርኤል በዓልን በማስታወስ፥ ሁሉም ሰው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ምሳሌ በመከተል እና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ዘወትር ዝግጁ ሊሆን ይችላል” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።
