ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የተሻለ የወደፊት ጊዜን ለማረጋገጥ ቀውሶችን በጋራ መፍታት እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በ “ግሪን አኮርድ” አዘጋጅነት በጣሊያን ትሬቪሶ ከተማ መጋቢት 9/2018 ዓ. ም. የተከበረውን 17ኛ ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ጥበቃ የመረጃ መድረክ በማስመልከት ለትሬቪሶ ጳጳስ አቡነ ሚሼል ቶማሲ መልዕክት ልከዋል።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በቅዱስነታቸው መልዕክት ላይ ፊርማቸውን ባኖሩበት ወቅት፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለመድረኩ ተሳታፊዎች ሰላምታቸውን በማቅረብ ያላቸውን ጥልቅ አድናቆት ገልጸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ዘንድሮ “የወደፊት መልካም ሕይወትን የሚጠማ አዲስ ሰብዓዊነት መገንባት” በሚል ጭብጥ በሥነ-ምህዳር እና ሕዝቡ የጋራ መኖሪያ ምድርን ለመጠበቅ ባለው ኃላፊነት ላይ ለመወያየት ከ40 በላይ አገራት የተወጣጡ ሰዎች በሰሜን ምሥራቅ የጣሊያን ከተማ ትሬቪሶ ላይ ተሰብስበዋል።
ቅዱስነታቸው ለአባላቱ በላኩት መልዕክት፥ በዘላቂ የልማት ምርምር ፕሮጀክቶች የፍጥረትን እንክብካቤ በተመለከተ ቀጣይነት ያለው የአንድነት እና የግንዛቤ ጥረት እንዲኖር አበረታተዋል።
“ሥነ-ምህዳራዊ ኃላፊነት በቴክኒካዊ መረጃ ብቻ የሚሟላ አይደለም” ሲሉ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እንዲህ ዓይነቱ መረጃ አስፈላጊ ቢሆንም ነገር ግን በቂ እንዳልሆነ ገልጸው፥ አእምሮን፣ ልብን እና እጆችን የሚያሳትፍ ትምህርት፣ አዳዲስ ልማዶች፣ የጋራ የአኗኗር ዘይቤዎች እና መልካም ልምዶች እንደሚያስፈልጉት አስረድተዋል።
ሰዎች የዛሬውን ቀውሶች ለመፍታት አብረው ቢሠሩ አክብሮት የተሞላበት፣ ሁሉን አቀፍ ማኅበራዊ አካባቢን እና የተሻለ የወደፊት ጊዜን ለአዲሶቹ ትውልዶች ማረጋገጥ እንደሚቻል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ፍጥረትን ለመንከባከብ ገደብን አልፎ መሄድ
በትሬቪሶ በተካሄደው ስብሰባ ላይ በብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ስም የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ የፍጥረታት ውዳሴ እና ሞቱ 800ኛ ዓመት በማስመልከት የተላከውን መልዕክት ብጹዕ ካርዲናል ቤኒአሚኖ ስቴላ ለተሳታፊዎች በንባብ አቅርበዋል።
“የወደፊት ሕይወትን አንድ ላይ መገንባት እውነት የጋራ ግባችን ከሆነ” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ በመጀመሪያ ይህን ማድረግ የሚከለክለውን ገደብን ማለፍ እና አዲስ ቤት መግባት እንደሚገባ አሳስበው፥ ይህ ከሌለ ለፍጥረት የሚደረግ እንክብካቤ በርዕዮተ ዓለም እና በቴክኖሎጂ፣ በስሜታዊ ጉጉት እና በቀዝቃዛ ሂደት፣ በአነቃቂ ንግግር እና በነፍስ አልባ አስተዳደር መካከል የመወዛወዝ አደጋ አለው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ዓመታዊ ክብረ በዓሉን ማስታወስ ብቻ ሳይሆን፣ ማካተት እና ኅብረትን መፍጠር የሚችሉ ዓርማዎችን እንደገና ማግኘት እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተዋል። “የውዳሴ ዜማው ለተፈጥሮ ያለውን ስሜት ብቻ እንደማይገልጽ ነገር ግን መንፈሳዊ እና አእምሯዊ አመለካከትን የሚቀርጹ ቃላትን እንደሚያቀርብ፣ የሰውን ልጅ ከቁጥጥር እና ከብዝበዛ ነፃ በማውጣት ለእንክብካቤ በሚያግዝ ዘላቂ የሙያ መስክ ውስጥ የሚያኖር፣ የሌለንን ነገር ወንድም እና እህት ብሎ መጥራት ጥልቅ የእንክብካቤ ተግባር፣ እውነታን እንደ ግንኙነት እና እንደ ፍጥረት ስጦታ አድርጎ መገንዘብ መሆኑን አስረድተዋል።
በስብሰባው ላይ ከተነሱት ጭብጦች መካከል ለሰው ልጅ ብስለት ፈተና ተደርጎ የሚታየው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሠራሽ አስተውሎት ይገኝበታል። “ሁሉ አቀፍ የማሰብ ችሎታ” የሚለውን ጠቁመው፥ “ከዚህ በኋላ ተግባራዊ ለማድረግ የምንቸኩለው ለእርማት ሳይሆን ነገር ግን ከጅምሩ ውሳኔዎችን የሚቀርጽ መሪ ራዕይ፣ የዲዛይን ምርጫዎች፣ የአስተዳደር ሞዴሎች፣ ግልጽነት፣ ክትትል እና መሣሪያዎችን እና መረጃዎችን የሚቆጣጠሩ ሰዎች እውነተኛ ተጠያቂነት” ነው ሲሉ አስረድተዋል።
“አብሮ መሥራት ማለት በቂ ነገር ያላቸው ሰዎች የበላይነት ሳይሆን የሰው ልጅ ብቻውን ከችግር የማይተርፍ ስለመሆኑ እና ለእርስ በርስ መተማመን እውቅና መስጠት ማለት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ “የውዳሴ ዜማው ምድር ውስጥ እና በሰዎች መካከል ያለው ሰላም የማይነጣጠሉ መሆናቸውን፣ ፍጥረት የሚጎዳ፣ ኅብረተሰብ የሚበታተን፣ የሰው ልጅ ክብር የሚረገጥ፣ ተፈጥሮ የሚበዘበዝ፣ ግንኙነቶች የሚፈርሱ፣ ቴክኖሎጂ ሰዎችን የሚከፋፍል ኃይል ያለው መሆኑን ያስታውሰናል” ብለዋል።
የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ሞት፥ ሕይወት ተላልፎ ሲሰጥ ፍፃሜውን የሚያገኝ መሆኑን የሚያስታውሰን ከሆነ፣ የውዳሴ ዜማው ዓለምን እንደ ባለቤት ወይም እንደ አዳኝ ሳይሆን እንደ ወንድማማችነት እንድንመለከት የሚያስተምር ከሆነ፣ የወደፊቱን ጊዜ አንድ ላይ መገንባት ወደ ተግባርነት ወይም ወደ ስትራቴጂነት ዝቅ የሚል ሳይሆን የኑሮ መንገድ መሆን አለበት” ሲሉ በማሳሰብ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን መል ዕክታቸውን ደምድመዋል።
