የር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የአልጄሪያ፣ የካሜሩን፣ የአንጎላ እና የኢኳቶሪያል ጊኒ የጉዞ ሰሌዳ ይፋ ሆነ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከሚያዝያ 5-15/2018 ዓ. ም. ድረስ በአልጄሪያ፣ ካሜሩን፣ አንጎላ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ሊያደርጉት ያቀዱት ሐዋርያዊ ጉብኝት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳነት ሥልጣናቸውን ከጀመሩ በኋላ ከጣሊያን ውጭ ለሦስተኛ ጊዜ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚሆን ታውቋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. መጨረሻ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ቱርክ እና ሊባኖስ በመሄድ ጉብኝት ማድረጋቸው ሲታወስ በቀጣዩ ጉዞአቸው የአውሮፓ አገር የሆነች ሞናኮን ከጎበኟት በኋላ በሦስተኛው ዙር ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወደ አራት የአፍሪካ አገሮች እንደሚጓዙ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።
ሰኞ መጋቢት 7/2018 ዓ. ም. ይፋ የወጣው የቅድስት መንበር መግለጫ እንዳስታወቀው፥ ቅዱስነታቸው በ11 ቀናት ውስጥ 11 ከተሞችን እንደሚጎበኙ፣ 6 የሰላምታ ንግግሮችን እንደሚያደርጉ፣ 10 ንግግሮችን እንደሚያደርጉ እና 8 የቃለ ምዕዳን ንግግሮችን እንደሚያሰሙ ታውቋል።
በአልጄሪያ ከሚያዝያ 5 እስከ ሚያዝያ 7/2018 ዓ. ም. ድረስ
ቅዱስነታቸው በአልጄሪያ በሚጀምሩት የአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሰኞ ሚያዝያ 5/2018 ዓ. ም. ወደ ዋና ከተማዋ አልጄርስ እንደሚደርሱ ታውቋል። ወደ አልጀርስ እንደደረሱም በአልጄሪያ የተካሄደውን ጦርነት ለማስታወስ እና አልጄሪያ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1982 ዓ. ም. ነጻነቷን ያገኘችበት 20ኛ ዓመት መታሰቢያን ካከበሩ በኋላ በዕለቱ የተመረቀውን የማቃም ኢቻሂት የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልትን ጎብኝተው የሰላምታ ንግግር እንደሚያደርጉ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመቀጠልም ወደ ፕሬዚዳንታዊው ቤተ መንግሥት ተጉዘው እዚያም ከሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቴቡኔ ጋር እንደሚገናኙ እና በ “ጃማ ኤል ጃዛየር” የስብሰባ ማዕከል ለሚሰበሰቡት ባለስልጣናት፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ለዲፕሎማሲ አባላት ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቀጥለውም እስከ 120,000 የሚደርሱ ምእመናንን ማስተናገድ በሚችል እና በዓለም ላይ ካሉ ትላልቅ መስጊዶች መካከል አንዱ የሆነውን የአልጄርስ ታላቁን መስጊድ የሚጎበኙ ሲሆን፣ ከዚያም በአቅራቢያው በምትገኘው ባብ ኤል ኦውድ ከተማ በሚገኘው የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር ሚስዮናውያን እህቶችን ከጎበኙ በኋላ በወዳጅነት ማዕከል የግል ጉብኝት እንደሚያደርጉ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ማብቂያ በአልጀርስ ከተማ በሚገኘው የአፍሪካ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ ለአልጄሪያ ማኅበረሰብ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ቅዱስነታቸው በሰሜን አፍሪካ አገር በሚያደርጉት ሁለተኛ የጉብኝት ቀናቸው ማለትም ማክሰኞ ሚያዝያ 6/2018 ዓ. ም. ከጥንታዊቷ የሂፖ ከተማ የተገኘች እና በሰሜናዊ ምሥራቅ ወደምትገኝ የቅዱስ አጎስጢኖስ መኖሪያ የወደብ ከተማ አናባ በአውሮፕላን እንደሚጓዙ ታውቋል። ቅዱስነቸው የሂፖን አርኪኦሎጂያዊ አካባቢን እና በዚያው የሚገኘውን የትናንሽ እህቶች ማኅበር የድሆች መንከባከቢያ ማዕከልን እንደሚጎበኙ ታውቋል።
ቅዱስነታቸው በመቀጠልም በቅዱስ አጎስጢኖስ የማኅበር ቤት ከማኅበሩ አባላት ጋር የግል ስብሰባ ካደረጉ በኋላ በቀኑ መጨረሻ ወደ አልጀርስ በረራ ከማድረጋቸው በፊት በቅዱስ አጎስጢኖስ ባዚሊካ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚቀርቡ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል።
በካሜሩን ከሚያዝያ 7 እስከ ሚያዝያ 10/2018 ዓ. ም. ድረስ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ረቡዕ ሚያዝያ 7/2018 ዓ. ም. ከአልጀርስ ወደ ካሜሩን ዋና ከተማ ያውንዴ የሚጓዙ ሲሆን በዚያው የሪፐብሊኩን ፕሬዝዳንት ፖል ባርቴሌሚ ቢያን በፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት ጎብኝተው የመካከለኛው አፍሪካ አገር ጉብኝታቸውን ይጀምራሉ። ከዚያም በአገሪቱ የስብሰባ ማዕከል ለሚገኙ ባለስልጣናት፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ለዲፕሎማሲያዊ አባላት ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ቅዱስነታቸው ቀጥለውም የንጉል ዛምባ ወላጅ አልባ ሕፃናት ማሳደጊያን ጎብኝተው ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ሠራተኞች ጋር ከተገናኙ በኋላ በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ዋና ጽሕፈት ቤት ከካሜሩን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር በግል እንደሚገናኙ ታውቋል።
በማግስቱ ሐሙስ ሚያዝያ 8/2018 ዓ/ ም. ከዋና ከተማዋ ያውንዴ ወደ ሰሜን ምዕራብ ባሜንዳ ከተማ ተጉዘው እዚያም ንግግር እንደሚያደርጉ እና በቅዱስ ዮሴፍ ካቴድራል ውስጥ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ለሰላም የተዘጋጀውን ስብሰባ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። ቅዱስነታቸው ወደ ያውንዴ ከመመለሳቸው በፊት በባሜንዳ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚያሳርጉ ታውቋል።
ዓርብ ሚያዝያ 9/2018 ዓ. ም. እንደገና ወደ ደቡብ ምዕራብ የባሕር ዳርቻ ከተማ ዱዋላ በረራ በማድረግ እዚያም በጃፖማ ስታዲየም መስዋዕተ ቅዳሴን ካቀረቡ በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ ካቶሊክ ሆስፒታልን ከጎበኙ በኋላ ወደ ካሜሩን ዋና ከተማ ያውንዴ እንደሚመለሱ መርሃ ግብሩ አመልክቷል። ወደ ያውንዴ ሲመለሱ ከካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ፕሮፌሰሮች ጋር ተገናኝተው እዚያም ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በአፍሪካ አህጉር የሚያደርጉትን ሦስተኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው በፊት ቅዳሜ ሚያዝያ 10/2018 ዓ. ም. በያውንዴ-ቪሌ አየር ማረፊያ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚያቀርቡ ታውቋል።
በአንጎላ ከሚያዝያ 10 እስከ ሚያዝያ 13/2018 ዓ. ም. ድረስ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሚያዝያ 10/2018 ዓ. ም. ወደ አንጎላ ዋና ከተማ ሉዋንዳ ከደረሱ በኋላ ከሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት ጆአኦ ሎሬንሶን ጋር በፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት ተገናኝተው በአገሪቱ ውስጥ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ይጀምራሉ። በመቀጠልም ከባለስልጣናት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲያዊ አካላት ጋር ከተገናኙ በኋላ ከአንጎላ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር የግል ስብሰባ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
እሑድ ሚያዝያ 11/2018 ዓ. ም. በአቅራቢያው በምትገኘው ኪላምባ ከተማ መስዋዕተ ቅዳሴን ካቀረቡ በኋላ ከዚያም በሄሊኮፕተር ወደ ሙክሲማ ከተማ እንደሚጓዙ ታውቋል። እዚያም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት በሚገኘው ሥፍራ ላይ የመቁጠሪያ ጸሎት ካቀረቡ በኋላ በቀኑ መጨረሻ ወደ ሉዋንዳ እንደሚመለሱ መርሃ ግብሩ ያመልክታል።
በማግስቱ ሰኞ ሚያዝያ 12/2018 ዓ. ም. እንደገና በረራ በማድረግ በሰሜን ምሥራቅ ወደምትገኝ ሳዩሪሞ ከተማ ይጓዛሉ። እዚያም የአረጋውያን መጦሪያ ቤትን ከጎበኙ በኋላ በሳውሪሞ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓትን ይፈጽማሉ።
ከዚያም ወደ ሉዋንዳ ተመልሰው በፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ቁምስና ውስጥ ለብጹዓን ጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለገዳማውያን እና ገዳማውያት እና እንዲሁም ለሐዋርያዊ ሥራ ተባባሪዎች ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በኢኳቶሪያል ጊኒ ከሚያዝያ 13 እስከ ሚያዝያ 15/2018 ዓ. ም. ድረስ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ማክሰኞ ሚያዝያ 13/2018 ዓ. ም. ጠዋት ከሉዋንዳ ወደ ቀድሞዋ የኢኳቶሪያል ጊኒ ዋና ከተማ ወደ ማላቦ በረራ በማድረግ እዚያም የሪፐብሊኩን ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጌማ ምባሶጎን ከተገናኙ በኋላ በፕሬዚዳንታዊው ቤተ መንግሥት ውስጥ ለባለስልጣናት፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ለዲፕሎማሲ አባላት ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ከዚያም በብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኝ በሊዮን 14ኛ ካምፓስ ውስጥ ከባሕል ተወካዮች ጋር ተገናኝተው ንግግር እንደሚያደርጉ ታውቋል። የዣን ፒየር ኦሊ የአእምሮ ህክምና ሆስፒታል ሠራተኞችን እና ታካሚዎችን ከጎበኟቸው በኋላ ቀኑን የሚያጠናቅቁት ከኢኳቶሪያል ጊኒ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር በሚያደርጉት የግል ስብሰባ እንደሚሆን ታውቋል።
ረቡዕ ሚያዝያ 14/2018 ዓ. ም. ሦስት በረራዎችን በማድረግ በመጀመሪያ በምሥራቅ ድንበር ላይ ወዳለችው የሞንጎሞ ከተማ ተጉዘው እዚያ በምትገኝ የወደብ ከተማ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ያቀርባሉ። ወደ ባታ የወደብ ከተማ ሁለተኛ በረራ ከማድረጋቸው በፊት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስም የተገነባውን የቴክኖሎጂ ትምህርት ቤትን ይጎበኛሉ።
በባታ ከተማ የሚገኘውን እስር ቤት ጎብኝተው ከታራሚዎች ጋር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ በካቲት 28/2013 ዓ. ም. በወታደራዊ ሠፈር ላይ በተፈፀመው ፍንዳታ የሞቱትን ለማስታወስ የተሠራውን ሐውልት ይጎበኛሉ። በአደጋው ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸው እና ወደ 500 የሚጠጉ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ሲነገር ቅዱስነታቸው በሥፍራው ተገኝተው እነዚህን ሰዎች በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው ይጠበቃል።
ከዚያም በባታ ስታዲየም ከወጣቶች እና ከቤተሰቦች ጋር ተገናኝተው ንግግር ካደረጉ በኋላ ወደ ማላቦ ይመለሳሉ። በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጨረሻ ቀን በሆነው ሐሙስ ሚያዝያ 15/2018 ዓ. ም. በማላቦ ስታዲየም መስዋዕተ ቅዳሴን ካቀረቡ በኋላ ወደ ሮም እንደሚመለሱ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያመለክታል።
