የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሞናኮን የጎበኙት እምነትን እና ግንኙነትን ለማጠናከር መሆኑ ተነገረ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሞናኮ ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀደም ብሎ ከቫቲካን ሬዲዮ ዳይሬክተር አቶ ማሲሚሊያኖ ሜኒኬቲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ትንሿ የግዛት ከተማ ሞናኮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ለመቀበል ዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ገልጸው፥ ትናንሽ አገራት የብዙ ወገንተኝነት መገለጫነታቸውን እንደሚያረጋግጡ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከጣሊያን ውጭ በአውሮፓ የሚያደርጉት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ጉብኝት ለትንሿ ካቶሊካዊ መንግሥት ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች በሙሉ የቀረበ የእምነት ማበረታቻ ተጨባጭ ምልክት ሆኖ እንደሚታሰብ አስረድተዋል። “ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለአካባቢው ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ አዲስ ማበረታቻ እንደሚሆን፥ እጅግ ተጋላጭ የሆኑትን ሳይዘነጉ የፍጥረት እንክብካቤ፣ የሕይወት ጥበቃ እና ዓለም አቀፍ አንድነትን ማጠናከር በሚሉ አስቸኳይ ጉዳዮች ላይ ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያጠናክር ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከጣሊያን ውጭ የሚያደርጉት የመጀመሪያው የአውሮፓ ሐዋርያዊ ጉብኝት በታሪክ ውስጥ ልዩ ጥቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በሞናኮ የመጨረሻ ጉብኝት ያደረጉት በ16ኛው ክፍለ ዘመን እንደ ነበር ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ይህም በቻርለስ 5ኛ እና በፍራንሲስ 1ኛ መካከል የሰላም ድርድር በተደረገበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 3ኛ ያደረጉት ጉብኝት እንደ ነበር፣ እንዲሁም በቅድስት መንበር እና በሞናኮ መካከል በርካታ ግንኙነቶች መኖራቸውን በማስታወስ፥ የካቶሊክ እምነት የመንግሥት ሃይማኖት ሆኖ በቀጠለበት ይህም በዛሬው የአውሮፓ ሁኔታ ውስጥ በተለይም የሕይወት ጥበቃን እና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮችን በሚመለከት ውይይት የተደረገበት እና በመጨረሻም ከከተማዋ 40,000 ነዋሪዎች መካከል 10,000 የሚሆኑት የሞናኮ ዜጎች ወጎቻቸውን፣ አምልኮዋቸውን፣ ማንነታቸውን፣ አንድነታቸውን እና የተቋማትን ዘላቂነት በሚገባ የሚያስቀጠሉ መሆናቸውን በመግለጽ፥ “በመሆኑም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተቋማዊ ጉብኝት ከቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ሐዋርያዊ ጉብኝት ጋር ፍጹም የሚስማማ ነው” ሲሉ ካርዲናል ፓሮሊን አስረድተዋል።

ዓለም አቀፍ ሕግ በኃይል አመክንዮ የተዳከመ በሚመስልበት፣ የሕግን ጥንካሬ ወደ ኃይል ለመቀየር የሚያስችሉ ጦርነቶች ባሉበት እና ይህን የሚደግፉ ንድፈ ሐሳቦች አደጋን ባንዣበቡበት ወቅት ትናንሽ አገራት የብዙ ወገንተኝነት ምሳሌ መሆናቸውን አስረድተዋል። የሕግ ደንቦች ለትናንሽ መንግሥት ሸክም ሳይሆኑ ትልቅ የህልውና እና የነፃነት ዋስትና እንደሆኑ አስረድተዋል። “ዛሬ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ የሚለካው በወታደራዊ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን በሥነ ምግባር ተዓማኒነት እና የእርቅ ድልድዮችን በመገንባት ችሎታ ነው” ብለው፥ “እንደ ሞናኮ ያሉ እውነታዎች እንደሚያሳዩት እውነተኛ ደህንነት የሚገኘው በጦር መሣሪያዎች ሳይሆን በእርስ በርስ ግንኙነቶች ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ዘላቂ ሰላም በቅድሚያ ፍትሃዊ መሆን እንዳለበት ያሳሰቡት ብጹዕነታቸው፥ ዘላቂ ሰላም በሰብዓዊ ክብር ላይ መመሥረት እንዳለበት ተናግረው፥ እንደ ውቅያኖስ ጥበቃ እና ዘላቂ ልማት፣ ከጂኦግራፊያዊ ድንበሮች ባሻገር የሚገኙ የጋራ ኃላፊነትን በሚጠይቁ የህልውና ተግዳሮቶች ላይ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎችን የሚመሩት ብዙውን ጊዜ ትናንሽ መንግሥታት እንደሆኑ አስረድተዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሞናኮ ሐዋርያዊ ጉብኝት ከቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ባህል ጋር የሚጣጣም ስትራቴጂያዊ አመክንዮ አካል ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሜዲትራኒያን አካባቢ አገራት በመካከላቸው ያሉ ልዩነቶችን በማክበር የሰላም መሣሪያዎች መሆናቸውን ከሚገልጹ ከቀደሙት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝቶች ጋር ቀጣይነት እንዳለው ማወቅ እንደሚቻል ገልጸው፥ በ1950ዎቹ ጆርጆ ላ ፒራ “የድርድር እና የሰላም ጥረት ለመላው ዓለም ሕዝቦች ይደርሳል!” በሚል የሜዲትራኒያን አካባቢ አገራት ለጂኦፖለቲካዊ ሚና ለዓለም ሰላም ራሳቸውን ወሳኝ ነጥብ አድርገው ማየታቸውን እንደተረዳ ገልጸው፥ ነገር ግን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሕዝቦች መካከል የሚመጣ የሰላም ቅድመ ሁኔታ ከእግዚአብሔር እና ከራሳችን ጋር አንድነት አለው” ሲሉ በጥብቅ መናገራቸው አስታውሰው፥ “ሰላምን መግባት የሚችል እና በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የእርቅ መልዕክተኛ መሆን የሚችል የታረቀ ሰው ብቻ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ከባድ ጦርነት እና ስደት ባለበት በዚህ ወቅት፣ በአዲሱ የጎርጎሮሳውያኑ 2026 ዓ. ም. የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ ከ600 በላይ ሰዎች በሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ሕይወታቸውን ባጡበት ወቅት የአውሮፓ አገራት የሥልጣኔ እና የሰብዓዊነት ምልክት እንዲሆኑ ተጠርተዋል” ብለው፥ በእነዚህ ማለቂያ በሌላቸው ግጭቶች እና ጦርነቶች መካከል የውይይት መንገዶችን በመገንባት በድፍረት እና በትዕግስት የሰላም እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል።

አውሮፓ በመሥራች አባቶቿ መነሳሳት በመታገዝ ከጠባብ የብሔርተኝነት ፍላጎቶች እና በደህንነት ላይ ከተመሠረቱ ራስ ወዳድነት ወደ እውነተኛ አንድነት እና የጋራ ዕቅድ በመሸጋገር የሰውን ክብር በሁሉም የፖሊሲ ዘርፎች ላይ ማስቀመጥ እንደሚገባ አሳስበዋል

ዓለም አቀፍ ደንቦች ሲሸረሸሩ የአውሮፓ አገሮች ለዓለም አቀፍ ሕግ ቅድሚያን በመስጠት የጋራ እውነትን ለመገንባት እና ፍትሃዊ ሰላምን ለማምጣት ድርድርን ብቸኛው መሣሪያ አድርገው እንዲጠቀሙ መጠራታቸውን አስረድተዋል። የስደት ተግዳሮትን በተመለከተ፥ ስደት ድንበርን በመዝጋት ወይም ግድግዳዎችን በማቆም ሊፈታ እንደማይችል ገልጸው፥ ነገር ግን ሕዝብ ከትውልድ አገሩ እንዲወጣ የሚያደርጉ ዋና ዋና ምክንያቶችን በመፍታት እና በትውልድ አገራት መረጋጋትን እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በማምጣት ሊለወጥ እንደሚችል አስረድተዋል።

ከአደጋ ጊዜ ዕርዳታ አቅርቦት ሥራ ስደተኞችን ወደ መቀበል፣ የመብት ጥበቃን እና ውህደትን የሚያጣምር ስትራቴጂያዊ ራዕይ በመሸጋገር የአውሮፓን ሰብዓዊነት እና ክርስቲያናዊ ጥሪን እንደገና ማግኘት እንደሚገባ አሳስበዋል። “እውነተኛ የአውሮፓ ደህንነት በተናጥል የተገነባ አይደለም” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ በወጣቶች ላይ ለመሥራት እና በሜዲትራኒያን ዳርቻዎች ላይ የጋራ ማኅበራዊ ፍትህን ለማስፋፋት ቁርጠኛ መሆን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

“የሜዲትራኒያን ባሕር ጂኦግራፊያዊ መጋጠሚያ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ እና ባሕላዊ መስቀለኛ መንገድ ታሪክ የሰጠን የአደራ ጥሪ ነው” ብለው፥ ይህ ጥሪ በቀሞ ጊዜ በራሱ የመጣ ውርስ ሳይሆን በየቀኑ በሚገናኝ ባሕል አማካኝነት የሚታደስ ቁርጠኝነት እንደሆነ አስረድተዋል። “ሰላም ብዙውን ጊዜ ከድንበር ጀምሮ የሚገነባ በመሆኑ የዚህ ባሕር ዳርቻዎች ዛሬ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት እና የፖለቲካ ትብብር ቋሚ ቦታዎች እንዲሆኑ ተጠርተዋል” ብለዋል። ውጥረቶች ቢኖሩም በርካታ የሰላም መሣሪያዎች የሆኑ ወጣቶች፣ ማህበረሰቦች እና የቤተ ክርስቲያን እውነታዎች፥ ልዩነት ስጋት ሳይሆን የጋራ ሃብት እንዲሆን ለማድረግ እየሠሩ መሆኑን አስረድተዋል። ዲፕሎማሲያዊም ሆነ ሐዋርያዊ ጥረታቸው ይህ ብርሃን እንደገና እንዲቀጣጠል የሚፈልግ መሆኑን ተናግረው፥ ሜዲትራኒያን አሁንም አብሮ መኖር ለእውነተኛ የሰው ልጅ የወደፊት ሕይወት ብቸኛ መንገድ መሆኑን ለዓለም ማስተማር እንደሚችል አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ሞናኮ የሄዱት በኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው የሆኑትን በእምነት ለማፅናት እንደሆነ ገልጸው፥ የጠንካራ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ምስክርነት ለጋራ ጥቅም የእምነት እና የሕይወት ምስክርነት እና ተመሳሳይ መሠረት ላላቸው ሌሎች የአውሮፓ አገሮች የአክብሮት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል። በተጨባጭ የቅዱስ አባታችን ጉብኝት እውነትን በመፈለግ የእምነትን ሕይወት በማሳደግ እና የውስጥ ሕይወት ፍላጎትን ለማደስ ግብዣ የሚያቀርብ የማበረታቻ ጉብኝት እንደሚሆንም አስረድተው፥ ከዚህም በላይ ዓለም አቀፍ የካቶሊካዊ ገጽታ ለባህል እና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ልዩነት ራስን ለመክፈት እውነተኛ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሞናኮ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ ዲፕሎማሲያዊ ተግባር ብቻ ሳይሆን ጥልቅ የቤተ ክርስቲያን ጠቀሜታ ያለው ታሪካዊ ወቅት እንደሆነ ብጹዕነታቸው ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በምንገኝበት ዘመን ሞናኮን የጎበኙ የመጀመሪያው እንደሆኑ ተናግረው፥ በቅድስት መንበር እና በሞናኮ መካከል ፍሬያማ የወዳጅነት አዲስ ገጽን ለመጻፍ እንደሆነ አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ለዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝት የመረጡት፥ “እኔ መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት ነኝ” (ዮሐ. 14:6) የሚለው ጭብጥ፥ ሊያቀርቡት የሚፈልጉትን የቤተ ክርስቲያን መሪነት ልብ እንደሚገልጽ እና ይህም ውስብስብ ፈተናዎች እና እርግጠኛ ያልሆኑ ሁኔታዎች በተከሰቱበት ዘመን የኢየሱስ ክርስቶስን ቀዳሚነት እንደገና ለማረጋገጥ እንደሆነ አስረድተዋል። ወደ ሞናኮ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አጭር ቢሆንም፣ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ በሕማማት ሳምንት ዋዜማ ትንቢታዊ እሴት እንዳለው ተናግረዋል።

በሞናኮ ውስጥ የካቶሊክ እምነት የመንግሥት ሃይማኖት ቢሆንም አብሮ መኖርን ሳያደናቅፍ ለሁሉም ብርሃን እንደሚሆን አስረድተዋል። “ስለዚህ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በቤተ ክርስቲያን እና በመንግሥት መካከል ያለው ትብብር ካለፈው የተገኘ ውርስ ብቻ ሳይሆን ካቶሊካዊ መሠረቱን ሳያጣ ከዘመናዊነት ጋር ለመተባበር የሚያስችል ሕያው ኃይል ያለበት ‘ጤናማ ዓለማዊነትን’ መገንባት የሚቻል መሆኑን ያሳያል” ብለዋል። ይህ ጉዞ ለአካባቢው ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ አዲስ ግፊት እንደሚሰጥ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ይህም በአስቸኳይ ጉዳዮች ላይ የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያጠናክር፣ የፍጥረት ጥበቃን፣ የሕይወት እንክብካቤን እና እጅግ ተጋላጭ የሆኑትን የማይረሳ ዓለም አቀፍ አንድነትን ሊያበረታታ እንደሚችል ተናግረው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በእውነት ጎዳና ላይ በመራመድ ብቻ እውነተኛ እና ዘላቂ ሰላም ሊገነባ እንደሚችል ሊያስታውሱን መጥተዋል” ሲሉ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ቃለ ምልልሳቸውን ደምድመዋል።

 

28 Mar 2026, 16:20