ካርዲናል ጉጄሮቲ ዓለምን በእሳት ከምያቃጥሉት ጋር ከመተባበር እንቆጠብ ማለታቸው ተገለጸ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
በእየአመቱ በስቅለተ ዐርብ ዕለት ለቅድስት ምድር የታሰቡ የመባ ስጦታ ስብስቦች ይኖራሉ - ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቤተክርስቲያን ለአብያተ ክርስቲያናት እና ለክርስቲያን ማህበረሰቦች ድጋፍ የምታደርገው አስፈላጊ የአንድነት ተነሳሽነት ነው።
በዚህ ዓመት፣ የሚሰበሰበው መባ ወይም ምጽዋዕት የሚካሄደው በፍጥነት እየተስፋፋ ባለ ጦርነት ውስጥ ሲሆን በክልሉ ውስጥ ላሉ ሁሉ አስደናቂ ውጤቶችን ያስገኛል። ለባህላዊው የCollecta pro Terra Sancta (የስቅለተ ዐርብ የመባ ማሰባሰብ) አስተዋጽኦ ለማበረታታት ለመላው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጻፉት ደብዳቤ፣ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናትን የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት ዋና ጸኃፊ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ የማያቋርጥ የጦር መሳሪያ ድምጽ አውግዘው ዓለምን በእሳት እያቃጠሉ ካሉት ጋር እንዳይተባበሩ ሁሉም ሰው እንዲያስብ ጋብዘዋል።
“አብዛኛው የዓለም ክፍል ስልጣኔያችንን እያጠቃ ያለውን ጥፋት እንደማያውቅ ይሰማኛል። ዛሬ ጦርነትን የሚያበረታቱ ሰዎች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የተገነቡትን ነገሮች ሁሉ እያወደሙ ነው” ሲሉ ካርዲናሉ አፅንዖት ሰጥው የተናገሩ ሲሆን “እኔ የምናገረው ስለ ሀሳቦች ብቻ ሳይሆን ስለ ሰዎች እና ነገሮችም ጭምር ነው - እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ታሪካዊ ሐውልቶችም ጭምር እየወደሙ ነው" ብለዋል።
