ር.ሊ.ጳ ሊዮ በኮንጎ ከ200 በላይ በሚሆኑ ሰዎች ሞት የተነሳ ማዘናቸውን ገለጹ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ረቡዕ ዕለት ጥር 20/2018 ዓ.ም በዲሞክራቲክ ኮንጎ ምስራቃዊ ሰሜን ኪቩ ግዛት ውስጥ አንድ ትልቅ የኮልታን ማዕድን ማውጫ ሥፍራ በመደርመሱ በርካታ የማዕድን አውጪ ሰራተኞች ሕይወት ማለፉ ተገልጿል። ቢያንስ 200 ሰዎች በሩባያ ማዕድን ማውጫ ሥፍራ በደረሰው የመደርመስ አደጋ ሕይወታቸውን አጥተዋል ሲሉ የሰሜን ኪቩ ግዛት ገዥ አካባቢውን የሚቆጣጠሩት አላፊ ተናግረዋል።
እሁድ ዕለት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አድርገው፣ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ባደረጉት ንግግር ለአደጋው ሰለባዎች እና ለቤተሰቦቻቸው ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል።
“በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ በሰሜን ኪቩ በሚገኝ ማዕድን ማውጫ ሥፍራ በደረሰው አደጋ ለተጎዱት ብዙ ሰዎች ጸሎቴን አረጋግጣለሁ” ብለዋል። “እግዚአብሔር ብዙ የሚሰቃዩትን ሰዎች ይርዳቸው!” ሲሉ ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።
በኤም 23 አማፂያን የተሾሙ መሪዎች ከጎማ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በሩባያ አቅራቢያ የእጅ ቁፋሮ በሚከናወንበት የማዕድን ማውጫ ሥፍራ መደርመስ የተነሳ በደረሰው አደጋ፣ ሥራው ለጊዜው አቁመዋል።
የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መንግሥት ለተጎጂዎቹ አጋርነቱን ገልጾ ነበር፣ ነገር ግን የM23 አማፂያን የክልሉን የተፈጥሮ ሀብት በሕገ-ወጥ መንገድ እና ደህንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ እየበዘበዙ ነው ሲል ከሷል።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ስማርት ስልኮችን፣ ኮምፒውተሮችን እና የአውሮፕላን ሞተሮችን ለማምረት የሚያገለግሉ ማዕድናትን የያዘ ኮልታን የተባለ የብረት ማዕድን ዋና አቅራቢ ስትሆን እ.አ.አ በ2023 ዓ.ም ከዓለም አቅርቦት 40 በመቶውን እንደ ምታመርት ተገልጿል።
ከአካባቢው የሚገኙ የቀድሞ የማዕድን ቆፋሪዎች ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገሩት ማዕድን ማውጫዎች በእጅ የሚቆፈሩ እና በደንብ ጥንቃቄ የማይደረግባቸው ትላልቅ ጉድጓዶችን ያቀፉ ናቸው። ብዙዎቹ እርስ በእርስ ትይዩ ስለሚሄዱ፣ በአንዱ ውስጥ በሚደርሰው መፈራረስ ሌሎች በርካታ ሰዎችን ሊያሳጣ ይችላል።
በሞዛምቢክ፣ በፖርቱጋል እና በጣሊያን የጎርፍ ሰለባዎች ጸሎቶች
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቅርቡ በፖርቹጋል፣ በደቡባዊ ጣሊያን እና በሞዛምቢክ በተከሰቱት አውሎ ነፋሶች ለተጎዱ ሰዎች ጸልየዋል።
በዚህ ሳምንት ከባድ አውሎ ነፋሶች ሞዛምቢክን ሲመቱ ቢያንስ 150 ሞዛምቢካዊያን ሲሞቱ፣ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በከባድ ዝናብ እና በጎርፍ ተጎድተዋል።
በማዕከላዊ ፖርቱጋል፣ ክሪስቲን በተባለው አውሎ ነፋስ ምክንያት ቢያንስ 6 ሰዎች ሞተዋል፣ ይህም በሰዓት እስከ 202 ኪሎ ሜትር የሚደርስ አውሎ ነፋስ አስከትሏል፣ ይህም አውሎ ነፋስ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል።
