ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ገዳማውያን እና ገዳማውያት በጦርነት ውስጥም የኢየሱስ ምስክሮች ናቸው” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ 30ኛውን ዓለም አቀፍ የቅድስና ሕይወት ቀን መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ አቅርበዋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን ሕይወታቸውን በሙሉ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የሰጡ ወንዶች እና ሴቶች እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ያሳዩትን ጽኑ እምነት በማወደስ፥ የሰላም ፈጣሪዎች እና የተስፋ ምልክቶች እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኢየሱስ ክርስቶስን ባዶነት እና የመንፈስ ቅዱስ ሕይወቱን በመካፈል እርሱን በቅርበት ለመከተል በገቡት ቃል ኪዳን በዓለም ውስጥ ያሉ ግጭቶች የሚሸነፉበትን መንገድ ማሳየት እና ያለ መጠን በሚወዱት እና ይቅር በሚሉ ሰዎች በኩል ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህን ጥብቅ ማሳሰቢያ የሰጡት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1997 ዓ. ም. ያቋቋሙት ዓለም አቀፍ የቅድስና ሕይወት ቀን 30ኛ ዓመት መታሰቢያ በተከበረበት ሰኞ ጥር 25/2018 ዓ. ም. ነው።

ስምዖን እና ሐና ኢየሱስን በቤተ መቅደስ ውስጥ ባገኙት ጊዜ መሲህነቱን አምነው እንዳወጁ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ መተረኩን ቅዱስነታቸው በማስታወስ፥ “ከፊታችን የሚታዩ ሁለት የፍቅር እንቅስቃሴዎች እነርሱም፥ ሕዝቡን ለማዳን የሚመጣ እግዚአብሔር እና የእርሱን መምጣት በንቃት የሚጠባበቅ የሰው ልጅ ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

ይህንን በአእምሯችን ይዘን ዓለም አቀፍ የቅድስና ሕይወት ቀን 30ኛ ዓመት መታሰቢያን ስናከብር፥ በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም ውስጥ የሚገኙት ገዳማውያን እና ገዳማውያት ሕይወታቸውን በሙሉ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የሰጡት ወንዶች እና ሴቶች የተልዕኮው ምስል አድርገው እንዲወስዱት ታስቦ ነው” ብለዋል።

ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ማቅረብ

የማኅበሮቻቸሁ መሥራቾች ለመንፈስ ቅዱስ ተግባር ገሮች በመሆን ይህንን ኃላፊነት በታማኝነት እና በብቃት መወጣት በመቻል አስደናቂ ምሳሌዎች ሆነዋል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በማያቋርጥ ውጥረት ውስጥ በሚገኝ ምድር ላይ የሚኖሩት እነዚህ አገልጋዮች ራሳቸውን በእምነት እና በድፍረት ለመምራት መፍቀዳቸውን ተናግረዋል።

“መንፈሳዊ ጉዞአቸውን ከቅዱስ ቁርባን ገበታ ከጀመሩት መካከል አንዳንዶቹ ዝግ የገዳም ሕይወት፥ ሌሎቹ ወጣ ብለው ሐዋርያዊ አገልግሎትን ለማበርከት፥ አንዳንዶቹ ወደ ትምህርት ቤት፥ ሌሎቹ ደግሞ የጎዳና ላይ አገልግሎት የሚስዮናዊነት ተግባር ጀምረዋል” ብለዋል።

ብዙውን ጊዜ ጨካኝ በሆኑ አካባቢዎች ውስጥ በጸሎት መገኘት

ይህ እምነታቸው እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ምንጭ እና ግብ መሆኑን በማወቅ በትህትና እና በጥበብ ወደ ቅዱስ መስቀሉ ሥር እንዲቀርቡ እና ወደ መንበረ ታቦት ለመመለስ ያነሳሳቸው መሆኑን ገልጸው፥ “በጸጋው ኃይል አማካኝነት አድካሚ እና ለአደጋ የሚያጋልጡ ተግባራትን መጀመራቸውን፣ ብዙውን ጊዜ ጨካኝ እና ግብየለሽነት በሚታይባቸው አካባቢዎች በጸሎት መኖር መጀመራቸውን፣ በውርደት እና በመረሳት ውስጥ ለጋስ እና አጋዥ ኃይል እንዲሁም በዓመፅ እና በጥላቻ ውስጥ የሰላም እና የእርቅ ምስክሮች ናቸው” ብለዋል።

የችግርን ማዕበል ለመጋፈጥ መዘጋጀት

ገዳማውያኑ እና ገዳማውያቱ በጦርነት እና በሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ መዘጋጀታቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚያገኙት ኃይል ክፋትን በመቃወም አንዳንዴም እስከ ሰማዕትነት ለመድረ ዝግጁዎች ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኔዲክቶስ 16ኛ፥ “የእግዚአብሔር ቃል” በሚለው የድህረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር፥ “የእግዚአብሔርን ቃል በእውነት የኖሩትን ሰዎች ማዳመጥ ባያካትት ኖሮ የቅዱስ ቃሉ ትርጓሜ ያልተሟላ ሆኖ ይቀር ነበር” ሲሉ መጻፋቸውን አስታውሰው፥ ይህን በማሰብ፥ “ዛሬ የዚህ ትንቢታዊ ወግ ዋና ተዋናዮች በመሆን ከእኛ በፊት የነበሩትን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በማክበር ከሁሉም በላይ ውርሳቸውን ወደፊት እናራምዳለን” ብለዋል።

የሰውን ልጅ ክብር የሚያሳንሱ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን መጠንቀቅ

ቅዱስ አባታችን በቃለ-ምዕዳናቸው፥ “ዛሬም ቢሆን በወንጌላዊ ምክራቸው እና በሚያከናውኑት በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎች አማካኝነት የሰውን ልጅ ክብር የሚያሳንሱ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን በመጠንቀቅ በእምነት እና በሕይወት መካከል ያለውን ክፍተት በሚያሰፋ ማኅበረሰብ ውስጥ ለሕዝቦች በሙሉ የእግዚአብሔርን ማዳን እንዲመሰክሩ ተጠርተዋል” ብለዋል።

“ወጣቶች፣ አረጋውያን፣ ድሆች፣ ሕሙማን እና እስረኞች በእግዚአብሔር መሠዊያ እና በልቡ ውስጥ ቅዱስ ሥፍራ እንዳላቸው ለመመስከር ተጠርታችኋል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እንደዚሁም እያንዳንዳቸው የማይደፈር የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ናቸው” ብለው፥ ከእርሱ ጋር ለመገናኘት፣ እርሱን ለማምለክ እና ለእርሱ ክብር ለመስጠት በፊቱ እንንበረከካለን” ብለዋል።

በጦርነት መካከል እንኳ ቢሆን ሕዝባቸውን አይተውም

ገዳማውያን እና ገዳማውያት ማኅበራት በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሕዝቦቻቸውን የማይተው መሆናቸውን የሚያሳዩ ምልክቶችን እና በግጭቶች መካከል ባቋቋሙት የወንጌል ምስክርነት ሠፈሮች ውስጥ በርካታ ማረጋገጫዎች  መኖራቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህ ገዳማዊ ማኅበራት ሕዝባቸውን ትተው እንደማይሸሹ እና ብዙውን ጊዜ ለደኅንነታቸው አስጊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሚቆዩ፥ ይህም ከቃላት የበለጠ እና እጅግ ተጋላጭ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የሕይወትን የማይጣስ ቅድስና የሚያስታውስ ሕያው ምስክርነት እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተዋል።

“ጦርነት እና እብሪተኝነት በተስፋፋበት፣ ራስ ወዳድነት እና ዓመፅ የሚያሸንፉ በሚመስሉበት ቦታ መገኘታቸው፥ ‘በሰማያት ያሉ መላዕክት የአባቴን ፊት ዘወትር የሚያዩ በመሆኑ ከእነዚህ ከታናናሽ ልጆች መካከል አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ’ የሚለውን የኢየሱስን ቃል የሚመሰክር ነው” ሲሉ አስረድተዋል። 

ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ፥ “ቤተ ክርስቲያን ፍፁምነቷን የምታገኘው ከሰማያዊ ክብር ብቻ ነው” ማለቱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ “በዚያን ጊዜ ከሰው ዘር ሁሉ ጋር አጽናፈ ዓለሙ ራሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ይሆናል” ብለዋል።

ይህ ትንቢታዊ ራዕይ ገዳማውያንን እና ገዳማውያትንም እንደሚመለከት ገልጸው፥ “በአሁኑ እውነታዎች ላይ በጥብቅ የተተከሉ ቢሆኑም፥ በሰማይ ላሉት ነገሮች ዘወትር ትኩረት የሚሰጥ፥ ሕይወታቸውን ሙሉ በሞት ፍርሃት በባርነት የታሰሩትን ነፃ ለማውጣት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞቶ ተነስቷል” ሲሉ አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው በቃለ-ምዕዳናቸው ማጠቃለያ፥ ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር አገልግሎት የሰጡ ወንዶችን እና ሴቶችን በማግኘቷ ቤተ ክርስቲያን አመስጋኝ መሆኗን በድጋሚ በመግለጽ፥ “እግዚአብሔር በሚመራችሁበት ቦታ ሁሉ የሰላም እርሾ እና የተስፋ ምልክት እንድትሆኑ” በማለት ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

“ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር በመስዋዕትነት ያቀረብንበትን ቃል ኪዳን ስናድስ፥ ሥራችሁን ከማኅበሮቻችሁ ቅዱሳን መሥራቾች ሁሉ ጋር ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በአደራ እንሰጣለን” በማለት ቃለ-ምዕዳናቸውን ደምድመዋል።

03 Feb 2026, 14:04