ፈልግ

በሲስቲን ጸሎት ቤት የተዘጋጀ የብርሃነ ልደቱ ኮንሰርት በሲስቲን ጸሎት ቤት የተዘጋጀ የብርሃነ ልደቱ ኮንሰርት   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የሲስቲን ጸሎት ቤት የገና ኮንሰርት ሰላምን ላጡ ሕጻናት እንዲሆን አሳሰቡ

በቫቲካን የሲስቲን ጸሎት ቤት መዘምራን ለብርሃነ ልደቱ በዓል ያዘጋጁትን የገና ኮንሰርት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተገኙበት ሥነ-ሥርዓት ላይ አቅርበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቤተልሔም የተሰማውን የመላዕክት ዝማሬ በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የዓለምን ሕጻናት በሙሉ ለዝማሬው ጸሎት አደራ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በዝግጅቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “ያለ መዝሙር የሚከበር የብርሃነ ልደቱ በዓል የለም” ካሉ በኋላ ቅዳሜ ታኅሳስ 25/2018 ዓ. ም. ምሽት በሚካኤል አንጄሎ ምስሎች ሥር የተካሄደውን የሲስቲን ጸሎት ቤት መዘምራን የገና ኮንሰርት ተካፍለዋል።

የሙዚቃ ቋንቋ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኮንሰርቱ ላይ ለተገኙት በሙሉ ሰላምታቸውን ሰጥተው፥ መዘምራኑ የገናን ምስጢር ለአእምሮ ብቻ ሳይሆን ለልብም የመናገር ችሎታ ባለው የሙዚቃ እና የመዝሙር ቋንቋ ለአድማጮች በማቅረባቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

“ሙዚቃ ለብርሃነ ልደቱ በዓል ማሳመሪያ እንዲሆን የሚታከል ጌጥ ሳይሆን ነገር ግን የበዓሉ አካል ነው” ሲሉ ገልጸው፥ በዓለም ውስጥ በየትኛውም ቦታ፣ በእያንዳንዱ ቋንቋ እና ሀገር ውስጥ በቤተልሔም የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ በሙዚቃ እና በመዝሙር እንደሚከበር ተናግረው፥ “ቅዱስ ወንጌልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አዳኝ ኢየሱስን ስትወልድ በሰማይ ያሉት መላእክት ‘ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን! ሰላምም ደስ በሚሰኝባቸው ሰዎች መካከል በምድር ይሁን!’ ብለው እንደዘመሩ ይነግረናል” ብለዋል።

የመጀመሪያቸው የሆነውን የዘንድሮን የገና ኮንሰርት በማስታወስ እንደተናገሩት፥ እረኞችን ጨምሮ በዚያች ሌሊት በቤተልሔም የነበሩ የዓይን ምስክሮች እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወደ መጡበት መመለሳቸውን አስታውሰው፥ “ምናልባትም ዋሽንታቸውን እየተጫወቱ በመዝሙር እንዳመሰገኑ መገመት እወዳለሁ” ሲሉ አክሏል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፣ ሰማያዊ ሙዚቃ የሚሰማበት ሌላ እጅግ ቅርብ፣ ጸጥ ያለ እና የተከበረ ቦታ እርሱም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልብ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ እግዚአብሔር በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ለኛ ያለውን ድርሻ በታማኝነት መከተልን በጸጥታ ማዳመጥ ቤተ ክርስቲያን የምትማረው ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለመንፈሳዊ ሙዚቃ የሰጡት ምስል በጸሎት መካከል ለሙዚቃ ያላቸውን ፍቅር የሚገልጽ እና ጸሎትን በመዝሙር ለሚሰሙት በሙሉ ግልጽ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት እንደሆነ እና ቅዱስነታቸው ቅዳሜ ምሽት በላቲን ቋንቋ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” የሚለው ጸሎት በመዝሙር እንዲቀርብ መጋበዛቸው ከዚህ የተለየ እንዳልነበር ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሲስቲን ጸሎት ቤት መዘምራን ዳይሬክተር ለሆኑት ሞንሲኞር ማርኮስ ፓቫን እና ለሚሼል ማሪኔሊ እንዲሁም ለ1,500 ዓመታት ያህል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶችን በመዝሙር ማገልገልን ለቀጠለው የመዘምራን ቡድን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ብርሃነ ልደቱን በሰላም እጦቶ ለሚያከብሩት ልጆች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ኮንሰርቱ በቀረበበት ምሽት ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር፥ ሙዚቃን በዓለም ውስጥ እጅግ አስቸኳይ ከሆነ ጥሪ ጋር በማዛመድ፥ የምሽቱ ኮንሰርት የዓለምን ስቃይ የምታዳምጥ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከት ቢሆንም፥ በብዙ የዓለም ክፍሎች ብርሃነ ልደቱን ያለ መዝሙር በጨለማ ውስጥ ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆነውን ሰላም ሳያገኙ ለሚያሳልፉት ልጆች መስጠት እፈልጋለሁ” ብለዋል።

“በዛሬው የውዳሴ መዝሙሮቻችንን ከፍ ልናደርገው የምንፈለገው እግዚአብሔር የእነዚህን ሕጻናት ጩኸት ይሰማ” ሲሉ በመጸለይ፥ በእናቱ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ለዓለማችን ፍትህን እና ሰላምን ይስጠን” በማለት ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በብርሃነ ልደቱን ኮንሰርት ላይ
ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በብርሃነ ልደቱን ኮንሰርት ላይ   (@Vatican Media)

 

05 Jan 2026, 15:53