ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ከሮም ሀገረ ስብከት ወጣቶች ጋር በቫቲካን ሲገናኙ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ከሮም ሀገረ ስብከት ወጣቶች ጋር በቫቲካን ሲገናኙ  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ወጣቶች ለምናባዊ ግንኙነቶች ሳይሆን ለእውነት የተፈጠሩ መሆናቸውን አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቅዳሜ ጥር 2/2018 ዓ. ም. ከሮም ሀገረ ስብክለት ወጣቶች ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል። ቅዱስነታቸው በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ለተሰበሰቡት የሮም ከተማ ወጣቶች ባስተላልፉት መልዕክት፥ እውነተኛ ባልሆነ ከአንገት በላይ ግንኙነቶች መርካት እንደሌለባቸው ነገር ግን እግዚአብሔርን እና ባልንጀራን ከማግኘት በሚመነጭ እውነት፣ መልካምነትን እና ኅብረት እንዲፈልጉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቫቲካን ወደሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ሲደርሱ ከሮም ሀገረ ስብከት የመጡ ወጣቶች በደስታ ተቀብለው ልባዊ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በካኅናት፣ በገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም በአስተማሪዎች ታጅበው ወደ ቫቲካን ከመጡት በሺዎች ከሚቆጠሩ ወጣቶች ጋር የተገናኙት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. የተከበረው የኢዮቤልዩ ዓመት ከተጠናቀቀ ከጥቂት ቀናት በኋላ ማለትም ቅዳሜ ጥር 2/2018 ዓ. ም. እንደ ነበር ታውቋል።

ከስብሰባው ጥቂት ቀደም ብሎ ከወንድማቸው ልጅ መልዕክት እንደደረሳቸው የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ይህም በዓለም ላይ ያሉትን በርካታ ችግሮች እንዴት መቋቋም እንደቻለ እና ብቸኝነት እንደሚሰማው መጠየቃቸውን ተናግረዋል። መልሱንም በፊታቸው ከነበሩት በርካታ ወጣቶች ማግኘታቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ተናግረዋል።

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ከሮም ሀገረ ስብከት ወጣቶች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ
ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ከሮም ሀገረ ስብከት ወጣቶች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ   (@VATICAN MEDIA)

በምናባዊው ዓለም ውስጥ የሚገኝ ድብቅ ብቸኝነት

የብዙ ወጣቶችን ጭንቀት ችላ ማለት ያልፈለጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሕዝብ መካከል ቢሆኑም ብቸኝነት፣ ግራ መጋባት እና መሰልቸት ወጣቶችን እየጎዳቸው እንደሆነ በማስታወስ፥ “ይህም ሕይወታቸውን የሚያደበዝዝ እና መገለልን የሚያስከት መሆኑን እናያለን” ሲሉ ተናግረው፥ “አንድ ሰው በበርካታ አስተያየቶች ውስጥ ሲገኝ እና በተከፋፈሉ ምስሎች ሲደነቅ ብቸኝነት ይሰማዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

ፈጽሞ የማይጠፋ ብርሃን

ስለ ግጥም የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ስለ ሰው ብቸኝነት የሚናገረውን የሳልቫቶሬ ኩዋዚሞዶ ጥቅሶችን በእምነት ብርሃን እንደገና በመተርጎም፥ ልብን ሰንጥቆ የሚያልፍ ጨረር እንደገና ለመውጣት ብቻ የሚጠልቅ ብቻ ብልጭልጭ ብርሃን እንዳልሆነ በማስረዳት ነገር ግን ልባችንን የሚያሞቅ እና በፍቅሩ የሚያበራል የፍትህ ፀሐይ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በማከልም፥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስንገናኝ የራስን እና የኅብረተሰብን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንደሚገኝ፣ የወንጌል ብርሃን ግንኙነቶችን እንደሚያበራ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለ በመሆኑ በዕለት ተዕለት ቃላት እና ምልክቶች አማካኝነት ደብዛዛ እና ስም-አልባ ዓለምን ለሰው ልጅ ወደሚስማማ ቦታ የሚለውት መሆኑን አስረድተዋል።


እውቅናን ሳይፈልጉ መመስከር

ቅዱስነታቸው፥ ወጣቶች በሚኖሩባቸው ቁምስናዎች፣ በመዝሙር አገልግሎቶች እና በበጎ አድራጎት ሥራቸው በሚቀስሙ እውነተኛ ልምዶች አማካይነት ደስታን ሊያገኙ እንደሚችሉ ገልጸው፥ ነገር ግን በሚያበረክቷቸው በእነዚህ ቀላል ሥራዎች እውቅናን እንዳይጠብቁ እና ዓለምም እጆችዋን ከፍታ እንደምትቀበል አትጠብቁ” ብለው፥ ምርትን ዘወትር ለመሸጥ የሚፈልግ ማስታወቂያ ከምስክርነት የበለጠ ትኩረትን እንደሚስብ እና ይህም ቅን ደንበኝነትን ለመገንባት የሚፈልግ መሆኑን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ስለዚህ ወጣቶች ኅብረተሰብን ከመለወጣቸው በፊት በቅድሚያ ራሳቸውን መለወጥ እንዳለባቸው በማወቅ በደስታ እና በጽናት እንዲሠሩ አሳስበዋል።

ጸሎት ሰንሰለቶችን ይሰብራል

የሚያስሯቸውን ሰንሰለቶች ለመስበር ምን ማድረግ እንደሚችሉ ማወቅ ለሚፈልጉት ወጣቶች ምላሽ የሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ከሁሉ በፊት መጸለይ ያስፈልጋል” ብለዋል። ጸሎት ጥልቅ እና እውነተኛ የለውጥ መሣሪያ እንደሆነ እና “አንድ ክርስቲያን በዙሪያው ላሉ ሰዎች፣ ለራሱ እና ለመላው ዓለም ጥቅም የሚያከናውነው እጅግ ተጨባጭ ተግባር ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14፥ “ጸሎት የመሰልቸትን፣ የኩራትን እና የግዴለሽነትን ሰንሰለት የሚሰብር የነፃነት ተግባር ነው” ሲሉ አክለው፥ በተለይም ክርስቲያኖች ራሳቸውን ወደ ቅዱስ ቁርባን፣ ወደ ቅዱስ ቃሉ እና ወደ መዝሙራት በሚያቀርቡበት ወቅት በልባቸው ውስጥ እሳትን የሚያቀጣጥለው እግዚአብሔር እንደሆነ እና “ይህም ‘የዓለም ብርሃን እና የምድር ጨው’ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል” ብለዋል።

12 Jan 2026, 16:21