ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፣ አዲሱ ዓመት ‘ሊታወቅ የሚገባ የጉዞ ወቅት’ ነው ማለታቸው ተገለጸ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
“ጌታ ይባርክህና ይጠብቅህ። ጌታ ፊቱን ያብራልህና ይራራልህ። ጌታ ፊቱን ይግለጥልህና ሰላም ያምጣልህ።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እ.አ.አ በ2026 የመጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከዕለቱ የመጀመሪያ ንባብ የተወሰደውን ዘኁልቁ መጽሐፍ ላይ ከላይ በተጠቀሰው የቡራኬ ጸሎ ላይ በማሰላሰል ስብከታቸውን መጀመራቸው ተገልጿል።
ቡራኬው የተነገረው ከግብፅ ባርነት ነፃ ለወጡትና “ዳግም መወለድ” ማለትም “ወደፊት ክፍት መንገድ” ለተሰጣቸው የእስራኤል ሕዝብ ነው ብለዋል። በዚህ መንገድ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደገለጹት የዕለቱ ቅዳሴ “እያንዳንዱ ቀን የእግዚአብሔር ለጋስ ፍቅር፣ ምሕረቱ እና የነፃነታችን ምላሽ ምስጋና ይግባውና የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ ሊሆን ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።
ማርያም እና ‘መሣርያ ያልታጠቀ’ አምላክ
የዕለቱ የአምልኮ ሥርዓት የእግዚአብሔር እናት የሆነችው የማርያምን ክብረ በዓል እና የዓለም የሰላም ቀንን አመላክቷል። በስብከታቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሁለቱ በዓላት መካከል ያለውን ጥብቅ ግንኙነት ዳስሰዋል። በማርያም ትብብር፣ እግዚአብሔር “ራቁቱን እና መከላከያ የሌለው”፣ “በሕፃን ልጅ ውስጥ የተወለደ” እንደመጣ ተናግረዋል።
“ይህንን የሚያደርገው፣ ያለ ስሌት እና ያለፍርሃት ሁሉንም ሰው ለመረዳት፣ ይቅር ለማለት፣ ነፃ ለማውጣት እና ለመቀበል ያለድካም ጥረት” በማድረግ ለማስተማር እንደ ሆነ የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ዓለም በዓመፅ የምትድን ሳይሆን በሰላም እና በመከባበር ብቻ የምትድን እንደ ሆነ አብራርተዋል።
“በማርያም መለኮታዊ እናትነት” ላይ አጽኖት ሰጥተው የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁለት ‘መሳሪያ ያልታጠቁ እውነታዎች’ አንድ ላይ ይመጣሉ፡- “የእግዚአብሔር፣ የመለኮትነቱን እያንዳንዱን መብት የሚክድ፣ እና የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመተማመን እና ሙሉ በሙሉ የሚቀበል የሰው ልጅ” ሲሉ አብራርተዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እ.አ.አ በጥር 6/2026 የሚያበቃውን የ2025 ዓ.ም የኢዮቤልዩ ዓመት ላይ በማሰላሰል ስብከታቸውን አጠናቀዋል።
ይህን ያደረጉት እ.አ.አ በ2000 ዓ.ም የኢዮቤልዩ መዝጊያ ላይ የቀድመው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የተናገሩትን በመጥቀስ ነው፡-“ታላቁ የኢዮቤልዩ ለአማኞች ስንት ያልተለመዱ አጋጣሚዎችን ሰጥቷል! የሰማዕታትን መታሰቢያ በማድረግ፣ የዓለምን ድሆች ጩኸት በማዳመጥ፣ በተቀበሉትና በተሰጡት ይቅርታዎች ልምድ… እኛም በታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔርን የማዳን መገኘት ተመልክተናል። የምድርን ፊት የሚያድስ ፍቅሩን በአካል ተመልክተናል” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን አጠናቀዋል።
