ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በስዊዘርላንድ በእሳት አደጋ የተጎዱትን በጸሎት አስታወሱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ያለፈው ሐሙስ በስዊዘርላንድ ክራንስ-ሞንታና በሚገኘው የአልፕስ ባር በተነሳው የእሳት አደጋ በተጎዱት ሰዎች የተሰማቸውን ሐዘን የገለጹ ሲሆን፥ በአደጋው 40 ሰዎች ሲሞቱ ከ110 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተነግሯል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በፈረንሳይኛ ቋንቋ በተጻፈው እና የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በሆኑት በብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በተላከው የቴሌግራም መልዕክታቸው ላይ በአደጋው ለተጎዱት እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ወዳጆቻቸው ያላቸው ቅርበት እና ርህራሄ ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመልዕክታቸው የሟቾችን ነፍስ ወደ ሰላሙና ወደ ብርሃን መኖሪያው እንዲቀበል፥ በልብ ሐዘን እና በሥጋ መቁሰል ለሚሰቃዩ ሰዎች እግዚአብሔር ድጋፋቸው እንዲሆናቸው በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
“የእግዚአብሔር እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በርኅራኄዋ፥ በአሳዛኝ ሁኔታ ለተጎዱት ሁሉ መጽናናትን እንድትሰጣቸው፣ በተስፋም ትጠብቃቸው” ሲል፥ አደጋው ለተከሰተበት የጽዮን ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ዣን-ማሪ ላቪ የተላከው መልዕክት ገልጿል።
በስዊዘርላንድ፣ ክራንስ-ሞንታና በሚገኝ ተራራማ አካባቢ በሚገኝ ባር ውስጥ የጎርጎሮሳውያኑን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ ድግስ ላይ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ወደ 40 ለሚጠጉ ሰዎች ሞት እና ለሌሎች 115 ለሚሆኑ መቁሰል ምክንያት ሆኗል። የአካባቢው ባለስልጣናት አደጋው የተከሰተው ከእኩለ ሌሊት በኋላ ከሁለት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደሆነ እና መንስኤውም ምን እንደ ለመለየት ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የጣሊያን እና የፈረንሳይ ዜጎችን ጨምሮ በርካታ ተጎጂዎች እስካሁን ድረስ የደረሱበት ያልታወቀ ሲሆን፥ ከጉዳተኞቹ አንዳንዶቹ እስከ 16 ዓመት ዕድሜ ያላቸው እንደ ሆኑ ተነግሯል።
ሀገረ ስብከቱም ሐዘኑን ገልጿል
በስውዘርላንድ የጽዮን ሀገረ ስብከት ታኅሳስ 23/2018 ዓ. ም. በተከሰተው አሳዛኝ አደጋ የተሰማውን ድንጋጤ እና በአደጋው ለተጎዱት፣ ለሚወዷቸው እና ለቤተሰቦቻቸው ያለውን አሳቢነት እና ርህራሄ ገልጿል። “የበዓል ምሽት መሆን የነበረበት በመቶዎች ለሚቆጠሩት አስከፊ አደጋ ሆኗል” ሲል የገለጸው የሀገረ ስብከቱ መግለጫው፥ የአደጋው ሰለባዎችን በጸሎት የሚያስታውሳቸው መሆኑን አክሏል።
ሀገረ ስብከቱ “በቦታው ላይም ሆነ በልዩ ልዩ ሆስፒታሎች ውስጥ የሕክምና ድጋፋቸውን ላቀረቡ የጤና ባለሙያዎች፣ የፖሊስ አባላት፣ የሲቪል እና የፍትህ አካላትን ጨምሮ ተጎጂዎችን ለመርዳት በተለያዩ መንገዶች ለተሳተፉ በሙሉ ድጋፉን እና ምስጋናውን ገልጿል።
ሀገረ ስብከቱ በአደጋው የተጎዱትን እና ቤተሰቦቻቸውን በሙሉ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አደራ በመስጠት፥ በዚህ አሳዛኝ ወቅት ርኅራኄን እና ድጋፍን እንደሚያገኙ ተስፋ ማድረጉን ገልጿል።
የስዊዘርላንድ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ መንፈሳዊ ተነሳሽነቶችን ማዘጋጀት
የስዊዘርላንድ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ዓርብ ታኅሳስ 24 ቀን ባወጣው መግለጫ፥ ለተጎጂዎቹ እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ከአደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ጋር ያላውን አጋርነት ገልጿል።
“የስዊዘርላንድ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አባላትም በአደጋው እጅግ ደንግጠዋል” ያለው መግለጫው፥ የጉባኤው ፕሬዝዳንት አቡነ ቻርለስ ሞሮድ በጉባኤው ስም ባወጡት መግለጫ፥ “ቤተ ክርስቲያኖቻችን በሙሉ በዚህ አስከፊ ጊዜ የድጋፍ፣ የመጽናኛ እና የጸሎት ቦታዎች ሊሆኑ ይችላሉ” ብለዋል።
መግለጫው ዓርብ ከሰዓት በኋላ በ12 ሰዓት ላይ በጽዮን ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ደወሎች በሙሉ የሐዘን፣ የአብሮነት እና የጽሞና ጸሎት ምልክት ሆነው እንደሚሰሙ ገልጾ፥ ሁሉም የስዊዘርላንድ ቁምስናዎች በዚህ የመቀራረብ እና የተሳትፎ ምልክት ላይ ምዕመናን እንዲሳተፉ አሳስቧል።
መግለጫው በጉባኤው የተጀመሩ የተወሰኑ መንፈሳዊ ተነሳሽነቶችን እንዳሉ ዘርዝሮ፥ ከእነዚህም ውስጥ ዓርብ ዕለት በሞንታና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የቅዱስ ቁርባን ስግደት ሥነ-ሥርዓት እንደሚከናወን፣ በማግሥቱ የመቁጠሪያ ጸሎት እና እሁድ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት የሚፈጸም መሆኑን አስታውቋል።
የመስዋዕተ ቅዳሴውን ጸሎት የሚመሩት የጽዮን ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ዣን-ማሪ ሎቪ ሲሆኑ፥ ከእርሳቸው ጋርም የስዊዘርላንድ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት አቡነ ሞሮድ እንደሚተባበሩ ታውቋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ የስዊዘርላንድ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች በተለይም የሞንታና ሐዋርያዊ መጋቢ፣ የቫሌይስ ሲኖዶሳዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እስጢፋኖስ ክሮንቢችለር እና የስዊዘርላንድ ሲኖዶስ ፕሬዝዳንት ጊልስ ካቪን እንደሚገኙ ታውቋል።
