ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 'የሌላውን ህመም በመሸከም ሕሙማንን ውደዱ' ማለታቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
"የሳምራዊው ርህራሄ፡ የሌላውን ህመም በመሸከም መውደድ" የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እ.አ.አ በየካቲት 11/2026 ዓ.ም ለሚከበረው የዓለም የሕሙማን ቀን መታሰቢያ ያስተላለፉት መልእክት ጭብጥ ነው።
እ.አ.አ በጥር 13/2026 ዓ.ም የተፈረመው እና ማክሰኞ ዕለት ይፋ በሆነው መልእክታቸው፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በሚቀጥለው ወር በቺክላዮ፣ ፔሩ በሚከበረው የዓለም የሕሙማን ቀን በፊት በመልካም ሳምራዊው ምስል ላይ እንደገና ማሰላሰልን አበረታተዋል።
ይህ ምስል "የበጎ አድራጎትን ውበት እና የርህራሄን ማህበራዊ ገጽታ እንደገና ለማግኘት ሁልጊዜ ተገቢ እና አስፈላጊ ነው፣ ትኩረታችንን ወደ ችግረኞች እና ለሚሰቃዩ ሁሉ፣ በተለይም ለታመሙት ሁሉ ለማዞር" እንደሚረዳ አስታውቀዋል።
በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል መሠረት፣ የሕግ መምህሩ ኢየሱስን፦ “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ፤ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት፤ ደበደቡትም፤ በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። እንደ አጋጣሚም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ፤ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን በጉዞ ላይ ሳለ እርሱ ወደ ነበረበት መጣ አይቶትም አዘነለት፤ ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፤ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደሪያ ወሰደው፤ ተንከባከበውም። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ማደሪያው ባለቤት ሰጠና፦ ‘ተንከባከበው፤ ከዚህም በላይ የምታወጣውን ወጪ ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ፤’ አለው። እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል?” እርሱም፦ “ምሕረት ያደረገለት፤” አለ ኢየሱስም፦ “ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ! አለው" (ሉቃስ 10፣29-37)፣ በማለት ቅዱስ ወንጌል እንደሚነግረን እኛም ለሕሙማን እንክብካቤ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ በንፍስኤር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ.አ.አ በ2020 ዓ.ም ስለ ሰው ልጅ ወንድማማችነትና ማህበራዊ ጓደኝነት እይታ ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለማሰላሰል መርጠዋል ሲሉ አስታውሰዋል። በዚያም፣ ለተቸገሩ ሰዎች ርኅራኄና ምሕረት ማድረግ በግለሰባዊ ጥረት ብቻ የተገደበ አይደለም፣ ነገር ግን የሚከናወነው በግንኙነቶች ነው፡- ከተቸገሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር፣ ከሚያስቡላቸው እና በመጨረሻም ፍቅሩን ከሚሰጠን ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ በመሆን ነው ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ መልእክታቸውን በሦስት መንገዶች በመገናኘት ስጦታ በማስቀመጥ ጀመሩ፡- "የቅርብነትና የመገኘት ደስታ"፤ "የታመሙትን የመንከባከብ የጋራ ተልእኮ"፤ እና "ሁልጊዜም በእግዚአብሔር ፍቅር የሚመራ፣ ራሳችንንና ባልንጀሮቻችንን የመገናኘት" ደስታ እንደ ሆነ አስፍረዋል።
ለሰዎች ቅርብ በመሆን የሚገኝ ደስታ
"በምሳሌው ውስጥ፣ ሳምራዊው ሰው የቆሰለውን ሰው ሲያይ 'አላለፈም፣ ይልቁንም፣ በግልጽና በትኩረት ተመለከተው፣ የኢየሱስ እይታ - እርምጃ እንዲወስድ አድርጎታል" ያሉ ሲሆን ይህንን በአእምሯቸው ይዘው፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ፍቅር ግድየለሽ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን ከሌላው ጋር ለመገናኘት እንደሚወጣ አጉልተው ገልጸዋል። ባልንጀራ መሆን የሚወሰነው በአካላዊ ወይም በማህበራዊ ቅርበት ሳይሆን በፍቅር ውሳኔ ነው። ለዚህም ነው ክርስቲያኖች ለተጎዱ ሰዎች ባልንጀራ የሚሆኑት፣ ለቆሰለው የሰው ልጅ ቅርብ የሆነውን እውነተኛ መለኮታዊ ሳምራዊ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ልንኖር ይገባል ብለዋል።
"የመገናኘት ስጦታ የሚመነጨው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ካለን አንድነት ነው» በማለት አፅንዖት በመስጠት የተናገሩት ቅዱስነታቸው "እርሱ ዘላለማዊ መዳን ያመጣልን ደጉ ሳምራዊ እንደሆነ እናውቀዋለን፣ እናም የቆሰለ ወንድም ወይም እህትን በምንረዳበት ጊዜ ሁሉ እናገኘዋለን" ብለዋል።
"በፍጥነት፣ በአፋጣኝ እና በችኮላ ባህል ውስጥ እንደተዘፈቅን - በመንገድ ላይ ቆም ብለን በዙሪያችን ያሉትን ፍላጎቶች እና ስቃዮች እንዳናውቅ የሚያግደን የመጣል እና የግዴለሽነት ባህል" እየኖርን እንደምንገኝ አምነዋል፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሌሎችን በመርዳት ደስታን ማግኘት የምንችለው በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ ገልጸዋል።
የታመሙትን የመንከባከብ የጋራ ተልእኮ
ርህራሄን እንድናሳይ የሚያስገድደን ጥልቅ ስሜት እንደሆነ፣ "ከውስጥ የሚመነጭ እና ለሌላ ሰው ስቃይ ቁርጠኛ ምላሽ የሚያስገኝ" ነው ሲሉ የገለጹት ቅዱስነታቸው "በፔሩ ሚስዮናዊ እና ጳጳስ በነበርኩበት ወቅት በነበረኝ ልምድ፣ "በሳምራዊው እና በእንግዳ ማረፊያ ቤቱ መንፈስ ምሕረትና ርኅራኄ የሚያሳዩ ብዙ ሰዎችን በግሌ አይቻለሁ" ብለዋል፤ ይህም በቤተሰብ አባላት፣ በጎረቤቶች፣ በጤና አጠባበቅ ሠራተኞች፣ ለታመሙ ሰዎች በሚደርገው ሐዋርያዊ እንክብካቤ ላይ በተሰማሩ እና ሌሎችም ሰዎች ላይ ለመጠጋት፣ ለመፈወስ፣ ለመደገፍ እና ችግረኞችን ለመከተል በመንገድ ላይ በሚቆሙ ሰዎች ላይ ታይቷል ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።
"ያላቸውን በማቅረብ፣ ርኅራኄን ለማኅበራዊ ገጽታ ይሰጣሉ፣ እናም ይህ ተሞክሮ በግንኙነቶች መረብ ውስጥ የሚፈጸመው ከግለሰብ ቁርጠኝነት በላይ ነው ሲሉ ለ34ኛው የዓለም የሕሙማን ቀን ባስተላለፉት መልእክት የገለጹት ቅዱስነታቸው በዚህ ምክንያት፣ በቅርቡ ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ምክር ላይ፣ ለታመሙ ሰዎች እንክብካቤ ማድረግ የቤተክርስቲያኒቱ ተልዕኮ “አስፈላጊ ክፍል” ብቻ ሳይሆን እውነተኛ “የቤተክርስቲያን እርምጃ” እንደ ሆነ መጥቀሳቸው ይታወሳል።
ከዚህም በላይ፣ ቅዱስ አባታችን ቅዱስ ችፕሪያንን ጠቅሰው "ይህ ገጽታ የኅብረተሰቡን ጤና መለኪያ እንዴት እንደሚያገለግል" ለማሳየት አስታውሰዋል። “በአንድነት መሆን” ማለት የጌታን ርኅራኄ ለሁሉም ሰዎች ስቃይ የሚያመጣ የአንድ አካል አባላት መሆናችንን በእውነት መገንዘብ ማለት ነው፣ ይህም የጌታን ርኅራኄ ለእያንዳንዱ ሰው እንደየራሳችን ጥሪ ያመጣል ሲሉ ተናግረዋል።
ሁልጊዜ ለእግዚአብሔር ባለን ፍቅር በመነሳሳት፣ ራሳችንን እና ባልንጀራችንን መገናኘት።
በሁለት ትእዛዛት ማለትም “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኃይልህ፣ በፍጹም አሳብህ፣ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” (ሉቃስ 10:27) በሚሉት ትዕዛዛት ላይ ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር ቀዳሚነት እና ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ ፍቅር እና ግንኙነት ቀጥተኛ ውጤቶችን እንደምያስገኝ እንገነዘባለን ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን “ለባልንጀራችን ፍቅር፣ ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ትክክለኛነት የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው” ሲሉ ቅዱስነታቸው የገለጹ ሲሆን አክለውም “ባልንጀራን ማገልገል እግዚአብሔርን በሥራ መውደድ ነው” ብለዋል።
በዚህ ረገድ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ “እንደ መንፈሳዊ ፍጡር፣ የሰው ልጅ ፍጡር የሚገለጸው በግለሰባዊ ግንኙነቶች ነው” ሲሉ ተናግረው እንደ ነበረ አስታውሰዋል፣ እናም “ሰው የራሱን ዋጋ የሚያረጋግጠው በማግለል ሳይሆን ራሱን ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት እና ከእግዚአብሔር ጋር በማስቀመጥ ነው” ብለዋል።
ለዚህ 'ሳምራዊ' መንፈስ መጸለይ
ቅዱስ አባታችን "ለሰው ልጅ ቁስሎች እውነተኛው መድኃኒት በወንድማማችነት ፍቅር ላይ የተመሠረተ የሕይወት ዘይቤ ሲሆን ይህም ሥር የሰደደው በእግዚአብሔር ፍቅር ላይ ነው" በማለት አጥብቀው ተናግረዋል፤ ምክንያቱም "ክርስቲያናዊ የአኗኗር ዘይቤያችን ይህንን የወንድማማችነት "ሳምራዊ" መንፈስ ሁልጊዜ እንደሚያንፀባርቅ" ተስፋቸውን ገልጸዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ምእመናንን ለቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በአደራ የሰጡ ሲሆን ለታመሙት ጤና፣ ለሚሰቃዩ ርህራሄ፣ መጽናኛ እና የሚያዳምጥ ጆሮ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ጆሮ እንድንሰጥ ማርያም በአማላጅነቷ እንድትረዳን የተማጸኑ ሲሆን እንዲረዳቸው ይህም ብዙውን ጊዜ በቤተሰብ ውስጥ በህመም እና በስቃይ ለሚኖሩ ሰዎች የሚደርገውን የሚከተለውን ጥንታዊ ጸሎት አቅርበዋል፦
"ውዴ እናቴ ማርያም፣ ከእኔ አትለይ። ዓይኖችሽን ከእኔ አትሰውር። በእያንዳንዱ ጊዜ ከእኔ ጋር ተመላለሺ እና በፍጹም አትተይኝ፣ ሁልጊዜ የምትጠብቂኝ፣ እንደ እውነተኛ እናት፣ የአብ፣ የወልድ እና የመንፈስ ቅዱስ በረከትን ለእኔ አስገኝልኝ"።
በመጨረሻም፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለታመሙ ሁሉ፣ ለቤተሰቦቻቸው እና ለሚንከባከቧቸው፣ ለጤና ባለሙያዎች እና ሐዋርያዊ አንክብካቤ ለምያደርጉ ሰዎች እንዲሁም በዚህ የዓለም የሕሙማን ቀን ላይ ለሚሳተፉ ሁሉ በልዩ ሁኔታ ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን በመስጠት መልእክታቸውን ደምድመዋል።
