ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ   (@Vatican Media)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስለ ቬንዙዌላ 'ዓመፅን አስወግዱ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ጠብቁ' ማለታቸው ተገለጸ

እሁድ ታኅሳስ 26/2018 ዓ.ም የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረጉ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለዓለም ባስተላለፉት መልእክት የቬንዙዌላ ሕዝብ ጥቅም እንዲጠበቅ፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር እና የሁሉም ሰብዓዊ እና የሲቪል መብቶች እንዲከበሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሁድ ዕለት በቬንዙዌላ በተከሰቱት የቅርብ ጊዜ ክስተቶች ላይ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል፣ የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎች ቅዳሜ ዕለት በካራካስ ኒኮላስ ማዱሮን ከያዙት እና ወደ ኒውዮርክ ለፍርድ ካመጡት በኋላ ሁኔታው እንዳሰጋቸው ገልጸዋል።

“የተወደደው የቬንዙዌላ ሕዝብ መልካምነት ከሌሎች ጉዳዮች ሁሉ በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሲሆን ዓመፅን እንድናሸንፍ እና የፍትህ እና የሰላም ጎዳናዎችን እንድንከተል፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንድንጠብቅ፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተደነገገውን የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ፣ የእያንዳንዱን ሰው እና የሁሉም ሰው ሰብዓዊ እና የሲቪል መብቶችን ማክበር እና በአስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ ምክንያት ለሚሰቃዩ ድሆች ልዩ ትኩረት በመስጠት የትብብር፣ የመረጋጋት እና የስምምነት የወደፊት ሕይወት ለመገንባት መሥራት አለባቸው” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቀትር ላይ ካደርጉት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ባስተላለፉት መልእክት ገልጸዋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ንግግር ሲያደርጉ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሁሉም ሰው ለቬንዙዌላ ሕዝብ እንዲጸልይ፣ የራሳቸውን ጸሎቶች እንዲያረጋግጡላቸው ጋብዛቸዋል።

እንዲሁም ሁሉንም ቬንዙዌላውያን የኮሮሞቶ እመቤታችን፣ የቬንዙዌላ ጠባቂ፣ የቅዱስ ሆሴ ግሬጎሪዮ ሄርናንዴዝ እና የቅዱስ ካርመን ሬንዲልስ አማላጅነት እንዲማጸኑ አደራ ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “በሰላም አምላክ ላይ እምነት ማሳደራችንን እንቀጥል” ሲሉ አሳስበዋል። “በጦርነት ምክንያት ከሚሰቃዩት ሕዝቦች ጋር እንጸልይ እና በአንድነት እንቁም” ሲሉ ተናግረዋል

የቬንዙዌላ ጳጳሳት ልመና

ታኅሳስ 25/2018 ዓ.ም ማለዳ ላይ የአሜሪካ ልዩ ኃይሎች ካራካስ ገብተው በዋና ከተማዋ ውስጥ በርካታ ወታደራዊ ቦታዎችን በመምታት የአገሪቷን ፕሬዚዳንት ማዱሮን እና ባለቤታቸውን ሲሊያ ፍሎሬስን በመኖሪያ ቤታቸው ከያዟቸው በኋላ በኒውዮርክ ወደ ሚገኘው እስር ቤት ገብተው በበርካታ ወንጀሎች ተከሰዋል።

እሁድ ዕለት የቬንዙዌላ ጳጳሳት ኮንፈረንስ ለክስተቶቹ ምላሽ በመስጠት የቤተክርስቲያኗን ከቬንዙዌላውያን ጋር ያላትን ቅርበት የሚገልጽ መልእክት አውጥተዋል።

“ዛሬ እያጋጠሟት ካሉት ክስተቶች አንጻር፣ እግዚአብሔር ለሁሉም ቬንዙዌላውያን መረጋጋት፣ ጥበብ እና ጥንካሬ እንዲሰጣቸው እንለምን” ብለዋል። “ከቆሰሉት እና ከሞቱት ቤተሰቦች ጋር በመተባበር እንቆማለን። ለሕዝባችን አንድነት በጸሎት እንጽና” ሲሉ አክለው ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

ጳጳሳቱ ለቬንዙዌላውያን ጥቅም ሲባል ውሳኔዎች እንዲወሰኑ ጥሪ አቅርበዋል። “የእግዚአብሔር ሕዝብ በልባችን እና በኅብረተሰቡ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የበለጠ ተስፋ እና ልባዊ ጸሎት እንዲኖር እንጠይቃለን፤ ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት እንቃወማለን” ብለዋል። “እጃችን ለመገናኘት እና ለመረዳዳት ክፍት ይሁን፣ የሚወሰኑ ውሳኔዎችም ሁልጊዜ ለሕዝባችን ጥቅም ሲባል እንዲወሰኑ እንጠይቃለን" ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

05 Jan 2026, 11:19