ኮሚሽነር ባርሃም፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ስደተኞችን በመርዳት ዋና አጋራቸው እንደሆነች ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ (UNHCR) እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. አጋማሽ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በግጭት፣ በዓመፅ፣ በስደት ወይም በሌሎች ክስተቶች ምክንያት ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ የተገደዱት ሰዎች ቁጥር 117.3 ሚሊዮን እንደሚደርስ እና ከእነዚህም መካከል ወደ 42.5 ሚሊዮን የሚጠጉት ስደተኞች እንደሆኑ ዘግቧል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ቀድሞ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጥያቂዎች ያላትን አሳቢነት በድጋሚ ገልጸው፥ ዓለም ይህን ጉዳይ በዝምታ እንዳይመለከተው አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2018 እስከ 2022 ዓ. ም. የኢራቅ ፕሬዝዳንት ከነበሩት እና አሁን በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ከሆኑት አቶ ባርሃም ሳሊህን ጋር ሰኞ ጥር 18/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ተገናኝተዋል። አቶ ባርሃም ሳሊህ ራሳቸው የስደት ሕይወት ያሳለፉ ሲሆን፥ አዲሱን ሥራ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ የጀመሩት ታኅሳስ 23/2018 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር አቶ ባርሃም ሳሊህ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ያደረጉትን ውይይት እና የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲን (UNHCR) በሥራው የሚያጋጥሙትን የተለያዩ ተግዳሮቶችን በማብራራት በርካታ ስደተኞች ከመፈናቀል አደጋ ለመውጣት በሚታገሉበት በዚህ ወቅት የዕርዳታ ድርጅቶች ለድጋፍ እጃቸውን መዘረጋታቸውን አስረድተዋል።
“ቅዱስነታቸውን ማግኘት ለእኔ በእውነት ትልቅ ክብር ነበር” ያሉት አቶ ባርሃም፥ ይህን ዕድል በሥራቸው መጀመሪያ ላይ ለማግኘት ጓግተው እንደ ነበር እና በስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነርነት ቦታ ላይ በቆዩባቸው ከአራት ሳምንታት ባልበለጡ ጊዜያት ውስጥ ከቅዱስነታቸው ጋር ስለ ስደተኞች ችግር መነጋገር ትልቅ ዕድል እንደ ነበር ገልጸዋል።
በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት ስደተኞች በሚያደረጉት የማያቋርጥ ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ባርሃም፥ የቅዱስነታቸው ሞራላዊ ሥልጣን እና ድጋፍ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ (UNHCR) ውስጥ ለሚሠሩት ሥራ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ በዓለም ዙሪያ ስደተኞችን የመርዳት ግዴታቸውን ለማሳካት ሲጥሩ ከቤተ ክርስቲያን እና ከእምነት ተቋማት ጋር ያላቸው አጋርነት አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ድምፅ እና ሞራላዊ ሥልጣናቸው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ስደተኞችን በመርዳት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ አጋርነታቸው እጅግ ጠቃሚ እና ሃብት መሆኑን ኮሚሽነር ባርሃም ሳሊህ አክለው አስረድተዋል።
ኃላፊነቱን የተቀበሉበት ወቅት ፈታኝ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነር ባርሃም ሳሊህ፥ ታይቶ የማይታወቅ መፈናቀል ባለበት፣ የዕርዳታ መስጫ ቦታዎች እየተዘጉ ባሉበት እና ያለባቸውን ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ሃብት ውስን በሆነበት ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል።
ቅድሚያ የሚሰጡት ጥረት በዓለም ዙሪያ ያሉ የስደተኞች ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚረዳ ተጨማሪ ገንዘብ በማግኘት ላይ የሚያተኩር እንደሚሆን እና እንደዚሁም የተጣለባቸውን ኃላፊነት በትክክል ለመወጣት እንደሆነ አስረድተዋል። ይህ ማለት ለስደተኞች ጥበቃ ማድረግ፣ እጅግ ለሚቸገሩ ሰዎች የሕይወት አድን ዕርዳታን መስጠት እና ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማግኘት ጠንክሮ መሥራት ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።
“ለአምስት ዓመታት ወይም ከዚያም በላይ፥ አንዳንድ ጊዜ ለአሥርት ዓመታት የመፈናቀል አደጋ የደረሰባቸውን በርካታ ስደተኞች ማየት ጥሩ አይደለም” ያሉት ኮሚሽነር ባርሃም ሳሊህ፥ እነዚህ ሰዎች በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ ሆነው መጠልያዎች ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸው፥ ይህ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ይበልጥ ወደ ሁሉን አቀፍ ዘላቂ መፍትሄዎች መሄድ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በቅርቡ በቻድ እና በኬንያ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያዎች ጉብኝት ማድረጋቸውን ያስታወሱት ኮሚሽነር ባርሃም ሳሊህ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2003 ዓ. ም. ጀምሮ ላለፉት 25 ዓመታት በመጠለያዎቹ ውስጥ የኖሩ ሰዎችን እና ወደ መጠለያው እየደረሱ የነበሩ ስደተኞችን ማግኘታቸውን ተናግረው፥ “ይህ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የመፈናቀል አደጋ ለደረሰባቸው ሰዎች የበለጠ ማድረግ እንደሚገባ ያሳያል” ብለዋል።
“ይህን ችግር በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ብቻውን ማቃለል አይችልም” ያሉት ኮሚሽነር ባርሃም ሳሊህ፥ ከሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች ጋር እንዲሁም ከአስተናጋጅ አገራት፣ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እና ከልማት ባንኮች ጋር የጋራ ጥረትን እንደሚጠይቅ በማስረዳት በዚህ መንገድ አስተናጋጅ አገራት ስደተኞችን ለማስተናገድ እና በሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ብቻ ጥገኛ እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ ለብሔራዊ እቅዳቸው አስተዋፅዖ አበርካቾች እንዲያደርጓቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚቻል ተናግረዋል።
እንደ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ እና ቻድ የመሳሰሉ አገራት ለስደተኞች የበለጠ ሁሉን አቀፍ ፖሊሲዎችን በማጽደቅ ማረፊያዎችን እያመቻቹ ሲሆን ይህም በብሔራዊ ሥርዓታቸው፣ በጤና አገልግሎቶቻቸው፣ በትምህርት እና በሥራ ዕድሎች፣ በሕግ እና በፋይናንስ አገልግሎቶች ተደራሽነት እንዲሳተፉ የሚያስችላቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ይህ ለአስተናጋጅ አገራት ጠቃሚ እንደሆነ እና በመጠለያ ውስጥ ካለው ሕይወት ባሻገር ስደተኞች በብሔራዊ ዕቅዶች እንዲካተቱ ለማድረግ በልማት ዕርዳታ መበረታታት እንዳለበት አሳስበው፥ በመጨረሻ ስደተኞች ቁጥር ብቻ ሳይሆኑ ነገር ግን የልማት ተሳታፊዎች መሆን እንደሚችሉ አስረድተዋል።
የአሜሪካ መንግሥት ለኤጄንሲው የሚሰጠውን ድጋፍ መቀነሱ በድርጅታቸው ምን ዓይነት ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል የተጠየቁት ኮሚሽነር ባርሃም ሳሊህ፥ አሜሪካ በቅርቡ ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ጋር ለተጣመረው (OCHA) የሁለት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መመደቧን ገልጸው፥ ይህንን ድጋፍ በመልካም ተቀብለው፥ በዚህ መንገድ ተጨማሪ ዕርዳታ እንደሚመጣ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።
በእርግጠኝነት የችግሩን ስፋት ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ በጣም ውስን ከመሆኑ አኳያ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት የበለጠ ንቁ የሆነ ዘመቻ ማካሄድ እንዳለባቸው ተናግረው፥ የስደተኞችን ችግር መቅረፍ የጋራ ዓለም አቀፍ ኃላፊነት እንደሆነ አስረድተዋል። የስደተኞች ቁጥር ከፍላጎቶቻቸው ጋር ፈጽሞ የተለየ በመሆኑ ተጨማሪ ገንዘብ ስለማስፈልጉ ምንም ጥርጥር የለውም ብለዋል።
ከሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች ጋር በመሆን ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ሥርዓቱ የበለጠ ምላሽ ሰጪ እና የበለጠ ወጪ ቆጣቢ መሆኑን ለማረጋገጥ በእነዚህ የማሻሻያ እና የቅልጥፍና ጥረቶች ውስጥ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የስደተኞች እና የተፈናቃዮች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነር ባርሃም ሳሊህ፥ ከግጭት፣ ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና ከአየር ንብረት ቀውሶች የሚሸሹ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ገልጸው፥ ከሱዳን ጎረቤት አገራት ለሚመጡ ስደተኞች በእርግጠኝነት አስቸኳይ የዕርዳታ ጥያቄ መኖሩን የተናገሩት ኮሚሽነሩ፥ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ያለው ሁኔታ የበለጠ አስቸኳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በቬነዙዌላ ያለው ሁኔታ አስቸኳይ ዕርዳታን የሚጠይቅ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነሩ፥ በርካታ ሰዎች በስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የሚኖሩባት ሮሂንጊያን አስታውሰው፥ “በዚህ ሁኔታ አስቸኳይ የዕርዳታ ፍላጎት መኖሩን ከመናገር ውጭ አጣዳፊነቱ የት እንደሚገኝ ለመናገር በጣም አስቸጋሪ ነው” ብለዋል።
እነዚህ የስደተኛ ማኅበረሰቦች በብሔራዊ የሕይወት ዕቅድ ውስጥ እንዲካተቱ እና እራሳቸውን ችለው እንዲኖሩ የሚያስችሏቸውን ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማግኘት ጠንክሮ መሥራት እንዳለባቸው ተናግረው፥ እነዚህ መፍትሄዎች ከመሠረታዊ የደኅንነት እና የክብር መብቶች ጋር የሚጣጣሙ መሆን እንዳለባቸው ለአስተናጋጅ አገራትም ጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ ብዙ ቀውሶች መኖራቸውን የገለጹት ኮሚሽነር ባርሃም ሳሊህ፥ የገንዘብ እጥረት ዋናው እንደሆነ ተናግረው፥ እያንዳንዱ ቀውስ የድርጅታቸውን ድጋፍ ይበልጥ እንደሚጠይቅ በመግለጽ፥ በዚህ ሁኔታ ዓለማችን ግጭቶች እንዳይባባሱ እና ችግሮች እንዲፈቱ የበለጠ እንዲያደርግ መጠራቱን ተናግረው፥ የመፈናቀል ቀውስ አንድ መሠረታዊ መፍትሔ እንዳለው ይህም ሰላም እንደሆነ ገልጸው፥ ሰዎች ወደ ቤታቸው በሰላም እና በክብር የመመለስ ዕድል እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
እንደ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ዕርዳታ መስጠት እና ጥበቃ ማድረግ የድርጅታቸው ሕጋዊ ኃላፊነት መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ባርሃም ሳሊህ፥ ለተፈናቀሉት ሰዎች ዘላቂ መፍትሄዎችን በማግኘት መርዳት ሕጋዊ ኃላፊነት እና የሞራል ግዴታ መሆኑን የጋራ ሰብዓዊነታችን የሚነግረን ሞራላዊ እና ትክክለኛ ነገር ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ከቤተ ክርስቲያን እና ከእምነት ድርጅቶች ዕርዳታን እያገኙ እንደሆነ የገለጹት ኮሚሽነር ባርሃም ሳሊህ፥ይህም ከልዩ ልዩ ድርጅቶች ጋር በግል ያከናወኑት ገንቢ ልምድ እና ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ያላቸው ጠቃሚ አጋርነት መሆኑን በማረጋገጥው፥ የወደፊት ተስፋቸው ከሌሎች የእምነት ድርጅቶች ጋር የበለጠ በመሥራት በሰብዓዊነት ረገድ በእምነታችን ዋና እሴቶች በመታገዝ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖቻችን ዕርዳታን ለማቅረብ የሚረዳ የበጎ አድራጎት ሥራን መሥራት የሚችሉ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር አቶ ባርሃም ሳሊህን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።
