ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ የሚያገለግል እንጂ የሚተካ ሊሆን አይገባም” ሲሉ ተናገሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ “መልክ እና ድምጽ የእያንዳንዱ ሰው ልዩ ባህሪያት ሲሆኑ የማንነት እና የግንኙነት መሠረት ሆነው ይቀጥላሉ” በሚለው እውነት ላይ በማሰላሰል እሑድ ግንቦት 8/2018 ዓ. ም. ለሚከበረው 60ኛ ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ መገናኛ ቀን መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በዲጂታል ግንኙነት እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ባተኮረው የዘንድሮው መልዕክታቸው፥ የቴክኖሎጂ ፈጠራ እያደገ በመጣበት ዘመን የሰውን ልጅ ክብር መጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።
የሰው ልጆች በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ እና በቃሉ አማካኝነት ወደ እርስ በርስ መገናኘት የተጠሩ መሆናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ “መልክን እና ድምጽን መጠበቅ ማለት በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያለውን መለኮታዊ አሻራ መጠበቅ እና የእያንዳንዱን የሰው ልጅ ሕይወት የማይተካ ጥሪ መጠበቅ ማለት ነው” ብለዋል።
የቴክኖሎጂ ሥነ-ማኅበራዊ ፈተና
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በተለይም ድምጾችን፣ መልኮችን እና ስሜቶችን ማስመሰል የሚችሉ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓቶች፥ የሰው ልጅ የእርስ በርስ ግንኙነት አስፈላጊ ገጽታዎች በመቀየር አደጋ ላይ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀዋል።
“ችግሩ በዋናነት ቴክኖሎጂያዊ ሳይሆን ሥነ-ማኅበራዊ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ሰብዓዊ ማንነትን እና ትክክለኛ ግንኙነቶችን መጠበቅን የሚመለከት እንደሆነ አስረድተዋል።
ቅዱስነታቸው ከማሰላሰል ይልቅ ለፈጣን ስሜታዊ ምላሾች ቅድሚያን የሚሰጡ፣ ወሳኝ አስተሳሰብን የሚያዳክሙ እና ማኅበራዊ ልዩነትን በሚያበረታቱ የማኅበራዊ ሚዲያ ስልተ ቀመሮች ተጽዕኖ ላይ ትኩረት አድርገዋል።
በመረጃ፣ በፈጠራ እና በውሳኔ አሰጣጥ ዙሪያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት በኩል እየጨመረ የመጣው ጥገኝነት የትንታኔ ክህሎቶችን፣ ምናባዊ ግንኙነትን እና የግል ኃላፊነትን የመቀነስ አደጋን እንደሚያስከትል አክለዋል።
እውነታ፣ ማስመሰል እና ማኅበራዊ ተጽእኖ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በዲጂታሉ ዓለም በእውነታ እና በማስመሰል መካከል ያለውን ልዩነት የመለየት ችግርን በማስታወስ እንደተናገሩት፥ “አውቶማቲክ” ወኪሎች እና “ቻትቦቶች” በሕዝብ ክርክሮች እና በግል ምርጫዎች ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ስሜታዊ ምላሾችን እና የግል ግንኙነቶችን ሊቀርጹ እንደሚችሉ ተናግረው፥ እንደነዚህ ያሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ሕይወትንም ሊነኩ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
ኃላፊነት፣ ትብብር እና ትምህርት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት ኃላፊነትን መውሰድ፣ ትብብርን ማሳደግ እና ትምህርት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፥ የቴክኖሎጂ ባለሞያዎች፣ የፖለቲካ ባለስልጣናት፣ የሚዲያ ሰዎች እና አስተማሪዎች በመካከላቸው ግልጽነትን እንዲያዳብሩ አሳስበው፥ እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሰውን ክብር እንዲጠብቁ እና የመረጃን ትክክለኛነትን እንዲያረጋግጡ የተጠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
“የዲጂታል ፈጠራን ወደ ጋራ ጥቅም ለመምራት በተቋማት እና በዘርፎች መካከል ትብብር ያስፈልጋል” ሲሉ ተናግረዋል።
የሚዲያ እውቀት እና የዲጂታል ግንዛቤ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመልዕክታቸው መጨረሻም፥ በሚዲያ፣ በመረጃ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዙሪያ ትምህርት በመስጠት አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት ሰጥተው፥ ግንዛቤን ማሳደግ፣ የግል ማንነትን መጠበቅ እና ኃላፊነት የሚሰማው የመገናኛ ባሕልን መደገፍ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።
ለመልክ እና ለድምጽ ሊሰጥ በሚገባው አዲስ እንክብካቤ ላይ በማትኮር፥ የሰው ልጅ የመገናኛ ገጽታን ለመጠበቅ እና የቴክኖሎጂን ዕድገት ለሰው ልጅ አገልግሎት ለማዋል ማዕከላዊ ሆኖ እንደሚቀጥ አስረድተዋል።
