ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ማርያ ኮሪና ማቻዶን በሐዋርያዊ መንበራቸው ሲቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ማርያ ኮሪና ማቻዶን በሐዋርያዊ መንበራቸው ሲቀበሉ  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የቬነዙዌላ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ማርያ ኮሪናን በቫቲካን ተቀብለው አነጋገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቬነዙዌላ ፖለቲከኛ እና የማኅበረሰብ አንቂ ማርያ ኮሪና ማቻዶን በሐዋርያዊ መንበራቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2025 ዓ. ም. የኖቤል ሽልማት አሸናፊ እና የቀድሞ የቬነዙዌላ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ማርያ ኮሪና ማቻዶን ሰኞ ጥር 4/2018 ዓ. ም. በሐዋርያዊ መንበራቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የፕሬዝደንት ማዱሮ መያዝ

ቅዱስነታቸው ማሪያ ኮሪና ማቻዶን በሐዋርያዊ መንበራቸው ተቀብለው ያነጋገሯቸው፥ የቬነዙዌላ  ፕሬዝደንት የነበሩት አቶ ኒኮላስ ማዱሮ እና ከባለቤታቸው ሲሊያ ፍሎሬስ ጋር በቬነዙዌላ ዋና ከተማ ካራካስ ውስጥ “የመፍትሄ ፍፁማዊ ኦፕሬሽን” በመባል በሚታወቅ የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ ከተያዙ ከ10 ቀናት በኋላ ነው።

በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እና ከዚህ ጋር በተያያዘ የሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሱት ማዱሮ በአሁኑ ጊዜ በሰሜን አሜሪካ ብሩክሊን በሚገኘው የሜትሮፖሊታን ማቆያ ማዕከል ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል።

ቬነዙዌላዊ ፖለቲከኛ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማርያ ኮሪና ማቻዶ የማዱሮን መንግሥት ዘወትር የሚቃወም እና “ቬንቴ ቬንዙዌላ” በመባል የሚታወቀውን የሊበራል-ወግ አጥባቂ የፖለቲካ ፓርቲን መርተዋል። በዚህ ምክንያት አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የተገደዱ ማርያ ማቻዶ በታኅሳስ ወር የኖቤል የሰላም ሽልማት ለመቀበል ወደ ኦስሎ ተጉዘው እንደ ነበር ይታወሳል።

ቬነዙዌላ በምክትል ፕሬዝደንቷ ዴልሲ ሮድሪጌዝ በጊዜያዊነት እየተመራች ባለችበት እና በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የተደገፈ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ሥራ እየተሠራ ባለበት በዚህ ጊዜ ማርያ ማቻዶ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በዋሽንግተን እንደሚገናኙ በያዝነው ሳምንት ውስጥ በፕሬዝደንቱ የተሰጠ መግለጫ አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ሊዮ 14ኛ ለቬነዙዌላ ያቀረቡት ጥሪ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ሊዮ 14ኛ ፕሬዝደንት ማዱሮ በተያዙ ማግሥት ማለትም እሑድ ጥር 3/2018 ዓ. ም. ለመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባደረጉት ንግግር፥ ሲቪሎችን ጨምሮ ወደ 80 የሚጠጉ የቬነዙዌላ እና የኩባ ወታደሮች የተገደሉበትን ክስተት በጥልቅ አሳቢነት እየተከታተሉት እንደሚገኙ መናገራቸው ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፥ “የተወደደው የቬነዙዌላ ሕዝብ ጥቅም ከሌሎች ጉዳዮች ሁሉ በላይ መቅደም እንደሚገባ፥ ይህም ዓመፅን ለማሸነፍ እና የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የፍትህ እና የሰላም መንገዶችን ለመከታተል ሊያግዝ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው በዚህ ማሳሰቢያቸው “የእያንዳንዱ ሰው ሰብዓዊ እና ሲቪል መብቶች እንዲከበሩ፣ በአስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ድሃ ማኅበረሰቦች ልዩ ትኩረት በመስጠት የሰላም የትብብር፣ የመረጋጋት እና የመግባባት መልካም የወደፊት ጊዜ ለመገንባት በጋራ እንዲሠሩ” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅድስት መንበር እውቅና ከተሰጣቸው የዲፕሎማሲ አካላት ጋር ጥር 1/2018 ዓ. ም. ስብሰባ ባደረጉት ወቅት ጥሪያቸውን በማደስ ስለ ቬንዙዌላ ሲናገሩ፥ “በፍትህ፣ በእውነት፣ በነፃነት እና በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ ማኅበረሰብ ለመገንባት እና በዚህም አገሪቱ ለብዙ ዓመታት ካጋጠማት ከባድ ቀውስ እንድትወጣ ጥረቶች ይደረጉ” ሲሉ አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው እንዲሁም “የቬነዙዌላ ሕዝብ ፍላጎት እንዲከበር እና የሁሉም ሰው ሰብዓዊ እና ሲቪል መብቶች እንዲጠበቁ፣ የተረጋጋ እና መስማማት ያለበት የወደፊት ሁኔታ እንዲረጋገጥ” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

13 Jan 2026, 15:38