ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ በሰላም አብሮ የመኖር መንገድን እንደሚያስገነዝብ ተናገሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የ“ሴንቴዚመስ አኑስ” ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2026 ዓ. ም. የአውሮፓ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ስብሰባን በሉክሰምበርግ ከተማ ዓርብ ጥር 15/2018 ዓ. ም. አካሂዷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በኩል በላኩት መልዕክታቸው፥ “በአውሮፓ ውስጥ ሰላምን ለመገንባት የካቶሊክ ማኅበራዊ አስተምህሮ እና ዓለም አቀፍ እሴቶች ሚና ምንድነው?” ለሚለው ጭብጡ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የዓለማችን ማኅበረሰቦች ሃይማኖቶች ባቀረቧቸው ሁለንተናዊ እሴቶች እና ለጋራ ጥቅም ባላቸው አስተዋጽኦ ላይ መወያየትን በማይፈልጉበት በዛሬው ዓለም ውስጥ ጭብጡ ተገቢ እና አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።
“ይህ ተቃውሞ ከተለያዩ ምክንያቶች የሚመነጭ ቢሆንም መሠረታዊ ቀውሱ የአንጻራዊነት መስፋፋት እና እውነትን ወደ አስተያየት ደረጃ ማውረድ ነው” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አክለውም፥ ማንኛውም አኅጉር ወይም ማኅበረሰብ “ደንቦቹን እና እሴቶቹን የሚገልጹ የተለመዱ እውነቶች ሳይኖረው በሰላም መኖር እና ማደግ አይችልም” ሲሉ አስረድተዋል።
የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክ እና አምሳል የተፈጠረ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ
14ኛ ቀጥለውም፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “ሴንቴሲመስ አኑስ” በሚል ርዕሥ በጻፉት መጽሐፋቸው ላይ የተናገሩትን በመጥቀስ፥ “እውነትን የማወቅ እና በዚያ እውነት መሠረት የመኖር ተፈጥሯዊ እና መሠረታዊ መብትን ካላከበሩ በስተቀር እውነተኛ ዕድገት ሊመጣ አይቻልም” ማለታቸውን አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን እንደ መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት አድርጎ በገለጠው ቃል እና ተግባር ላይ የተመሠረተ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ ጉዳይ “ድንበር አልፎ የሚሄድ እና የጋራ ፍላጎቶችን እና የአኗኗር ዘይቤን በማመቻቸት በርካታ የሚያቀርባቸው ነገሮች እንዳሉት ከእነዚህም መካከል አንዱ በሰላም አብሮ መኖር እንዲቻል ማድረግ ነው” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ በሉክሰምበርግ የሚካሄደው ጉባኤ የአውሮፓን ጥልቅ የክርስትና መሠረቶችን ለማስታወስ እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እሴቶች ይበልጥ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ የአውሮፓ አህጉርን በመገንባት ረገድ የሚጫወተውን ሚና ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
