ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከፊንላንድ የክርስቲያኖች አንድነት ልዑካን ቡድን ጋር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከፊንላንድ የክርስቲያኖች አንድነት ልዑካን ቡድን ጋር   (@VATICAN MEDIA)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ፊንላንድ በተስፋ ላይ የተመሠረተ የክርስቲያኖች አንድነት ተምሳሌት ናት ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለክርስቲያኖች አንድነት በተዘጋጀ ሁለተኛ የጸሎት ሳምንት ላይ የፊንላንድ የክርስቲያኖች አንድነት ልዑካንን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ለልዑካኑ ባደረጉት ንግግር በፊንላንድ ውስጥ በሉተራን፣ በኦርቶዶክስ እና በካቶሊክ ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ትብብር አወድሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከፊንላንድ የክርስቲያኖች አንድነት የልዑካን ቡድን ጋር ሰኞ ጥር 11/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ተገናኝተው የቅዱስ ሄንሪክን ዓመታዊ በዓልን በኅብረት አክብረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለክርስቲያኖች አንድነት በተመደበው የጸሎት ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከፊንላንድ የመጡት የሉተራን፣ የኦርቶዶክስ እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት ተወካዮችን በቫቲካን ተቀብለው ባደረጉት ንግግር፥ በፊንላንድ የቱርኩ ሀገረ ስብከት 750ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በማስታወሳቸው ሊቀ ጳጳስ ሉኦማን አመስግነዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “እንደ ጥሪአችሁ ለአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካል እና አንድ መንፈስ አለ” በሚለው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ጭብጥ ላይ በማሰላሰል መልዕክት አስተላልፈዋል። 

ተስፋችን በጋራ የክርስትና እምነታችን ላይ የተመሠረተ ነው” በማለት አብራርተው፥ ይህም ለሁሉም ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት እና ለኃጢአት ይቅርታ መሠረት በሆነው በአንድ ጥምቀት ላይ የተመሠረተ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

“ዛሬ ብዙ ሰዎች በተስፋ መቁረጥ ስሜት እየተፈተኑ ይገኛሉ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እንደ ክርስቲያኖች እና የተስፋ መልዕክተኞች የእግዚአብሔርን ብርሃን ወደ ዓለማችን ጨለማ ማዕዘኖች የማምጣት ተልዕኮ አለብን” ብለዋል።

“የኢዮቤልዩ በዓል የተስፋ ዓመት ቢጠናቀቅም እንኳን የክርስቲያናዊ ተስፋ መጨረሻ እና ገደብ የለውም” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው፥ ክርስቲያኖች በሙሉ ይህንን ተስፋ በቃላት ብቻ ሳይሆን ተስፋ ስጋን ከለበሰው ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይልን በማግኘት ተጨባጭ በሆኑ በበጎ ተግባራት እንዲመሰክሩ አበረታተዋል።

በተለይም ፊንላንድን በማስታወስ እንደተናገሩት፥ “በዚያች አገር ውስጥ የክርስቲያኖች አንድነት የትብብር ምልክቶች ናቸው” በማለት አድናቆታቸውን ገልጸው፥ አገሪቱ ለክርስቲያኖች አንድነት ዋና ምሳሌ የሆነችበትን ዝና በደስታ ተቀብለዋል።

ይህም የኦርቶዶክስ፣ የሉተራን እና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት የተስፋ፣ የሰብዓዊ ክብር እና የርህራሄ ባሕልን ለማስፋፋት የሚያደርጉት የጋራ ጥረት መሆኑን ገልጸዋል።

“በሞት አፍ አፍ ለሚገኙ ሕሙማን ማስታገሻን በመስጠት፣ እንክብካቤን በማሳደግ እና ሕይወትን እስከ ፍጻሜው ለማቆየት የሚደረግ ጥረት መቀጠል አለበት” ለሚለው የአብያተ ክርስቲያናቱ የጋራ መርህ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የስካንዲኔቪያን አገራት ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የተቀበለውን “በጋራ ማደግ” የሚለውን ሠነድ ጠቅሰው፥ “ሠነዱ በክርስቲያኖች አንድነት የኅብረት ጉዞ ላይ ጠቃሚ ምዕራፍ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ እንዲህ ያሉት ተነሳሽነቶች ለረጅም ጊዜ ከቆየው የቅዱስ ሄንሪክ ቀንን በጋራ ከማክበር ባሕል ጋር ተዳምረው “ተግባራዊ እና ፍሬያማ የሆኑ የክርስቲያኖች አንድነት መልካም ምልክቶች ናቸው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ዓለም አቀፉ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና የሉተራን ኅብረት የጋራ ውይይት ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ለመግባት በሚዘጋጅበት በዚህ ወቅት ልዑካኑን አበረታተዋል።

የጋራ ውይይታቸውን ለቅዱስ ጴጥሮስ፣ ለቅዱስ ጳውሎስ እና ለቅዱስ ሄንሪክ አማላጅነት በአደራ በመስጠት፥ የልዑካን ቡድኑ “የአባታችን ሆይ!” ጸሎትን በኅብረት እንዲያቀርብ ጋብዘው፥ ጸሎቱ የጋራ እምነታቸው እና ኅብረታቸው ምልክት እንደሆነ ገልጸዋል።

20 Jan 2026, 15:37