ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የተጠመቁት በሙሉ ለተልዕኮ የተጠሩ ናቸው” ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የወንጌል ምስክርነት አመጽ እየጨመረ በመጣበት ዓለም ውስጥ አንድነትን ማሳደግ የሚችል ሰላማዊ ልብን እና እርቅን ይጠይቃል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህን መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ አሥራ አንደኛ ከመቶ ዓመት በፊት ያወጁት ዓለም አቀፍ የተልዕኮ ቀን ከመከበሩ ቀደም ብሎ ሲሆን፥ “በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ በመሆን በተልዕኮ መተባበር” በሚል ጭብጥ የሚከበረው የዘንድሮ በዓል እሑድ ጥቅምት 8/2019 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል።
ክርስትና የተግባር ስብስብ ሳይሆን የአንድነት ሕይወት ነው
በተልዕኮው ውስጥ “ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ የመሆን ምስጢር አለ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የቤተ ክርስቲያን ማንነት ከቅድስት ሥላሴ ፈልቆ በቅድስት ሥላሴ ድጋፍ የሚቀጥል ኅብረት ነው” ብለው፥ በሁሉም የሰው ልጆች መካከል ወንድማማችነትን ማሳደግ እና ከፍጥረት ሁሉ ጋር መስማማት ነው” ብለዋል።
“በተልዕኮ ላይ ያለች ቤተ ክርስቲያን ዋና ኃላፊነት በአባሎቿ መካከል ያለውን መንፈሳዊ እና ወንድማዊ አንድነትን ማደስ ነው” በማለት፥ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል አንድነትን ለማሳደግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ማንኛውም የተጠመቀ ሰው ከተልዕኮው የተገለለ አይደለም
ይህ አንድነት በራሱ የመጨረሻ ግብ ሳይሆን ነገር ግን በኅብረት ውስጥ ተልዕኮን ያተኮረ እንደሆነ ገልጸው፥ የወንጌል ምስክርነት ከዚህ ኅብረት ሙሉ ኃይሉን ያገኛል” ብለዋል።
ማንኛውም የተጠመቀ ሰው ከተልዕኮው ነፃ ወይም ግድየለሽ አይደለም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እያንዳንዱ ሰው እንደየጥሪው እና የኑሮ ሁኔታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያኑ በአደራ በሰጠው ታላቅ ሥራ ውስጥ እንደሚሳተፍ ተናግረው፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ደጋግመው እንዳስታወሱን፥ “ወንጌልን ማወጅ ሁልጊዜ የስምምነት፣ የጋራ እና የሲኖዶሳዊነት ተግባር ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ፍቅር ዋና የወንጌላዊነት መሠረት ነው
“አንድነት የተልዕኮው ቅድመ ሁኔታ ከሆነ ፍቅር ደግሞ ዋናው መሠረቱ ነው” ሲሉ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የሚታወጀው መልካም ዜና ረቂቅ ሃሳብ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ አምሳል እና ሕይወት የተገለጠ የእግዚአብሔር ታማኝ ፍቅር ነው” ብለዋል።
በዘመናት ሁሉ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ክርስቲያኖች፣ ሰማዕታት፣ ኑዛዜ ሰሚዎች እና ሚስዮናውያን ይህንን መለኮታዊ ፍቅር ለዓለም ለማሳወቅ ሲሉ መሰዋነት መክፈላቸውን ገልጸው፥ ዓለም አሁንም እነዚህ ደፋር የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች ስለሚያስፈልጋት እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቦችም አዳዲስ የሚስዮናዊነት ጥሪ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ዘወትር ወደ እግዚአብሔር መጸለይ እንደሚገባ በማሳሰብ፥ “ሁሉን ነገር ትተው ኢየሱስ ክርስቶስን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ በወንጌላዊነት ለመከተል ፈቃደኛ የሆኑ ወጣቶችን እና ጎልማሶችን ይስጠን!” በማለት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ያቀረቡት ጸሎት
“ቅዱስ አባት ሆይ! በሚያስተባብር እና በሚያድስ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር አንድ አድርገን! ምዕመናን በሙሉ በተልዕኮ እንዲተባበሩ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ታማኞች እንዲሆኑ፣ ለፍጥረታት በሙሉ ያለህን ታማኝ ፍቅር እያወጁ ወንጌልን በየቀኑ የሚመሰክሩበትን ድፍረት ስጣቸው። ሚስዮናውያን ወንድሞችን እና እህቶችን ሁሉ ባርካቸው፣ ጥረታቸውንም ደግፋቸው፣ በተስፋም ጠብቃቸው! የተልዕኮ ንግሥት የሆንሽ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በምድር ዳርቻ ሁሉ የምንሰጠውን የወንጌል አገልግሎታችንን ደግፊ። የሰላም መሣሪያዎች አድርጊን። መላውን ዓለም የሚያድነውን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃንን እንዲያውቅ እርጂ። አሜን!”
