ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ “ጦርነት ባለበት እና ሰብዓዊ ክብር በጠፋበት ዘመን ለሰላም እንጸልይ” ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው “በታሪክ ውስጥ ሰብዓዊ ክብር እየቀነሰ ባለበት እና ጦርነትም እየተለመደ በመጣበት በዚህ ወቅት ለሰላም እንጸልይ” ሲሉ አሳስበዋል።
ቅዱስነታቸው ይህን ጥሪያቸውን ያቀረቡት ረቡዕ ጥር 13/2018 ዓ. ም. በጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ለተገኙት ምዕመናን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ባቀረቡበት ወቅት ነው።
ከትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው በመቀጠል ለፖርቱጋልኛ ተናጋሪ ምእመናን ባቀረቡት ሰላምታ፥ “እግዚአብሔር አብን ሥጋን ለብሶ የገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ የፍትህ እና የእርቅ መንገዶችን ለማግኘት ይርዳን” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
ከጥር 10-17/2018 ዓ. ም. ድረስ በመከበር ላይ ባለው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ውስጥ ምእመናን ለክርስቲያኖች አንድነት እና ለዓለም ሰላም እንዲጸልዩ አደራ ብለዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሕማማቱ አስቀድሞ ደቀ መዛሙርቱ አንድ እንዲሆኑ መጸለዩን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ለጀርመንኛ ተናጋሪ ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት “ለክርስቲያኖች አንድነት ጸሎት በሚደረግበት በዚህ ሳምንት ተከታዮቹ በሆንን በእኛ መካከል አንድነት እንዲኖር፣ ዓለምም በእርሱ መገለጡ ያምን ዘንድ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በጸሎት እንተባበር” ሲሉ አሳስበዋል።
“ለአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካል እና አንድ መንፈስ አለ” (ኤፌ 4፡4) የሚለው የዘንድሮውን የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ጭብጥ በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ “በዓለም ዙሪያ በሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ላይ እግዚአብሔር የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን እንዲሰጥ፣ በስጦታውም በመታገዝ ክርስቲያኖች መለያየትን አሸንፈው ጠንካራ የአንድነት ትስስር ለመፍጠር እንዲጸልዩ” በማለት አበረታተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት፥ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ማኅበረሰቦች በክርስቲያኖች መካከል ሙሉ እና የሚታይ አንድነት እንዲመጣ ጸሎታቸውን እንዲያጠናክሩ አደራ ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቅዱስ ጳውሎስ መለውጥ ለማስታወስ በሮም በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ ውስጥ ረቡዕ ጥር 13/2018 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ የተዘጋጀውን የጸሎት ሥነ-ሥርዓትንም መርተዋል።
