ፈልግ

በሞዛምቢክ የጣለው ኃይለኛ ዝናብ ያስከተለው የጎርፍ አደጋ በሞዛምቢክ የጣለው ኃይለኛ ዝናብ ያስከተለው የጎርፍ አደጋ  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጎርፍ አደጋ የተጎዱትን የሞዛምቢክ ሕዝቦች በጸሎታቸው አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቫቲካን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ወቅት በአውዳሚው የጎርፍ አደጋ የተጎዱ የሞዛምቢክ ሕዝቦችን በማስታወስ እንደተናገሩት፥ ተጎጂዎችን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው ገልጸው፥ በአደጋው ምክንያት ለተፈናቀሉት እና ጉዳት ለደረሰባቸው ያላቸውን ቅርበት አረጋግጠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህንን የተናገሩት ረቡዕ ጥር 20/2018 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ታዳሚዎች ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ባቀረቡበት ወቅት በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱትን በማስታወስ ለፖርቱጋልኛ ተናጋሪ ምዕመናን ባደረጉት ንግግር ላይ ነው።

ቅዱስነታቸው በዚህ ንግግራቸው ተጎጂዎቹን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው ገልጸው፥  ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉት እና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በሙሉ ያላቸውን ቅርበት በመግለጽ፥ የእግዚአብሔርን ዕርዳታ እና ቡራኬ ተመኝተውላቸዋል።

ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በሞዛምቢክ በተከሰተው ከባድ ዝናብ ቢያንስ 137 ሰዎች መሞታቸው፥ ወደ 812,000 የሚጠጉ ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ብሔራዊ የአደጋ መቆጣጠሪያ ተቋም (INGD) ማክሰኞ ጥር 19/2018 ዓ. ም. ዘግቦ የአደጋውን የቅርብ ጊዜ አሃዝ ይፋ አድርጓል

የደቡብ ምሥራቅ አፍሪካ አገር ሞዛምቢክ በአሁኑ ወቅት ካለፈው ጥቅምት ወር በጀመረ ከባድ የዝናብ ወቅት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ይህም በመጋቢት ወር ያበቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከፖላንድ ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን ባደረጉት ንግግር፥ በፖላንድ በምትገኝ የላቲን ሥርዓት የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎት በማበርከት ላይ የሚገኝ ወታደራዊ ሀገረ ስብከት የተቋቋመበት ሰላሳ አምስተኛ ዓመት መታሰቢያን በማስታወስ፥ የዚህ ሀገረ ስብከት ተግባር እግዚአብሔርን እና አገርን የሚያገለግል የሰዎች ሕሊናን ማዘጋጀት ነው” ብለዋል።

በዚህ መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለእግዚአብሔር ቃል እና ለቤተ ክርስቲያን ወጎች ታማኝ መሆን ለሐዋርያዊ አገልግሎት በተለይም በፈተና እና አስተማማኝ ባልሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ቅዱሳት ምስጢራትን ለመምራት አቅጣጫን የሚያሳይ ይሁን” ብለዋል።

እንዲሁም ለአረብኛ ተናጋሪ ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፥ ቤተ ክርስቲያንን ወደ እውነት ሙላት የሚመራው መንፈስ ቅዱስ ዘወትር አዕምሮአቸውን እንዲበራላቸው በመለመን፥ የእምነትን አደራ ጠብቀው ለሌሎች እንዲያስተላልፉ አደራ ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ለፈረንሳይኛ ተናጋሪ ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፥ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የቤተ ክርስቲያን ዶክተር የሆነውን የቅዱስ ቶማስ አኩዊናስን መታሰቢያ እንደምታከብር አስታውሰው፥ተወዳጁ ቅዱስ ቶማስ አኩዊናስ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንድንረዳ እና በዚህም እግዚአብሔር ምን ያህል እንደሚወደን እና ድነታችንን እንደሚፈልግ ለማወቅ ያግዘን ዘንድ” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

 

 

 

29 Jan 2026, 11:12