ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ፍትህ እና በጎነት በእግዚአብሔር ምስጢር አንድነትን እንደሚያገኙ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰኞ ጥር 18/2018 ዓ. ም. ግብዣቸውን ያቀረቡት በጎርጎሮሳውያኑ አዲሱ ዓመት የፍርድ አሰጣጥ ሥራቸውን ለሚጀምሩ የቅድስት መንበር ፍርድ ቤት ዳኞች መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደ ነበር ታውቋል።
የቅድስት መንበር ፍርድ ቤት በተለምዶ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ መብቶችን ለመጠበቅ ሲባል በሐዋርያዊ መንበር ውስጥ እንደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሆኖ የሚያገለግል፣ የሕግ አንድነትን የሚያበረታታ እና በውሳኔዎቹ ለዝቅተኛ ፍርድ ቤቶች እገዛን የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል።
የፍርድ ቤቱ የጋብቻ ሁኔታዎችን እና በፍትሃዊ ጉዳዮች ላይ ፍርድ የመስጠት ሥልጣን ያለውን ቢሮንም የሚያካትት ሲሆን፥ እንደየ ዓለም አቀፍ ሕግ እና ደንብ መሠረት የክኅነት ሹመትን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳዮችን ለመዳኘት ብቃት ያለው እንደሆነ ታውቋል። ፍርድ ቤቱ የአንድነት መዋቅር ያለው በመሆኑ ከልዩ ልዩ የዓለም አካባቢዎች በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የተመረጡ የተረጋገጠ አስተምህሮ፣ ብቃት እና ልምድ ያላቸው የተወሰኑ ዳኞችን ያቀፈ እንደሆነ ታውቋል።
የተከበረ አገልግሎት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “የዳኞቹ አገልግሎት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሚገባ እና የዚህ አገልግሎት ተካፋዮች እንዲሆኑ እግዚአብሔር የጠራቸው ውድ ዓለም አቀፍ የዳኝነት ተግባር ነው” በማለት ለሥራቸው ምስጋናቸውን አቅርበው፥ “ ‘ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየተናገርን በነገር ሁሉ ራስ ወደሚሆን ወደ እርሱ ወደ ክርስቶስ እንደግ’ (ኤፌ 4:15) የሚለው አገላለጽ በፍትህ አስተዳደር ውስጥ በዕለታዊ ተልዕኮአችሁ ሊተገበር ይችላል” በማለት አስታውቀዋል።
ቅዱስነታቸው በቦታው የተገኙትን እና በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ፍርድ ቤቶች ውስጥ ለሚሠሩት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ “እንድለማመድ ዕድል ያገኘሁበት የዳኝነት አገልግሎት ተሞክሮዬን በጥልቀት እንድረዳ እና ሥራዬ ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ጠቀሜታ እንድገነዘብ ያስችለኛል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለቅድስት መንበር ፍርድ ቤት ዳኞች ባደረጉት ንግግር ማዕከላዊ ወደ ሆነው መሠረታዊ ጭብጥ በመመለስ ሲናገሩ፥ “እንቅስቃሴያችሁ ለፍትህ ዋና መሠረት ከሆነው እውነት ጋር ግንኙነት አለው” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ “በዚህ አጋጣሚ በፍትህ እውነት እና በበጎ አድራጎት መካከል ስላለው የጠበቀ ትስስር አንዳንድ አስተያየቶችን ልሰጣችሁ እፈልጋለሁ” ብለው፥ “ሁለት ተቃራኒ መርሆዎች ሳይሆኑ ወይም በተግባራዊ መስፈርቶች መሠረት ሚዛናዊ መሆን ያለባቸው እሴቶች ሳይሆኑ ነገር ግን በፍቅር እና በእውነት በእግዚአብሔር ምስጢር ውስጥ ጥልቅ ስምምነትን የሚያገኙ ሁለት ገጽታዎች ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።
በማከልም “ይህ ትስስር በፍትህ እንቅስቃሴ ውስጥ በተጨባጭ እውነት እና በበጎ አድራጎት ጉዳዮች መካከል አልፎ አልፎ የሚከሰት የ “ዲያሌክቲክ” ውጥረት የሚፈጠር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ጥንቃቄን የሚጠይቅ ሚዛን
“አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ከሆኑ የምዕመናን ጉዳዮች ጋር ከመጠን በላይ መተዋወቅ ወደ አደገኛ የእውነት አንጻራዊነት ሊያመራ ይችላል” ብለው፥ “በእርግጥ የተሳሳተ ርህራሄ በሐዋርያዊ ቅንዓት በመነሳሳት ለዳኝነት ሥራ ተገቢ የሆነውን እውነት የማረጋገጥ አስፈላጊውን በመደበቅ አደጋን ሊያስከትል ይችላል” ብለዋል።
“ይህ በትዳር ውስጥ ባዶነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ እና ተጨባጭ መሠረት ወደ ሌላቸው ሐዋርያዊ ውሳኔዎች ሊያመራ ይችላል” ብለው ነገር ግን በማንኛውም ዓይነት ሂደት ውስጥ ሊከሰት እንደሚችል እና ጥብቅነቱን እና ፍትሃዊነቱን ሊያዳክም ይችላል” ብለዋል።
በሌላ በኩል አንዳንድ ጊዜ ለሰዎች ፍቅር የሚጠይቀውን ሁሉ ግምት ውስጥ ሳያስገባ ቀዝቃዛ እና የተገለለ እውነትን ሊያረጋግጥ እንደሚችል፥ ይህም በአክብሮት እና በምህረት የተደነገጉትን ስጋቶች ችላ በማለት በእያንዳንዱ የፈተና ደረጃ ላይ ሊገኝ ይችላል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በእውነት እና በበጎ አድራጎት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ በማሰላልሰል እንደተናገሩት፥ “ ‘ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየተናገርን በነገር ሁሉ ራስ ወደሚሆን ወደ እርሱ ወደ ክርስቶስ እንደግ’ (ኤፌ 4:15) የሚል ግልጽ መመሪያ እንደሚሰጥ አጥብቀው ተናግረዋል።
በተቃራኒ ፍላጎቶች መካከል ያለ ውጥረት ሳይሆን የማስተዋል መሣሪያ ነው
“ሂደቱ አንዳንድ ጊዜ በስህተት እንደሚታሰበው በተቃራኒ ፍላጎቶች መካከል ውጥረት መፍጠር ሳይሆን በአንድ ጉዳይ ላይ እውነትን እና ፍትህን ለመለየት የማይተካ መሣሪያ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በፍርድ ሂደቶች ተቃራኒ ባህሪ ላይ ውይይት በማድረግ እና እነዚህን ጥንቃቄ የሚያሻቸው ሁኔታዎችን በአግባቡ ለመገምገም እና እውነቱን በአግባቡ ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉት ጥብቅ ነገሮች ዘርዝረዋል።
“እነዚህን መሠረታዊ የፍትህ መርሆዎችን አለማክበር እና ተመሳሳይ ሁኔታዎችን በማከም ረገድ ፍትሃዊ ያልሆኑ ልዩነቶችን ማሳደግ በቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ የሕግ ገጽታ ላይ ከባድ ጉዳት ያስከትላል” ብለው፥ በተጨማሪም ጋብቻን ለማቋረጥ የሚሰጥ ፍርድ በሀገረ ስብከት ጳጳስ ፊት የሚሰጥ ብይን አጭር ሂደት መሆኑን ተመልክተው እንደተናገሩት፥ ይህን ሂደት እውን የሚያደርግ ግልጽ የሆነ ጋብቻን የመሰረዝ ውሳኔ በታላቅ ጥንቃቄ መገምገም እንዳለበት አሳስበዋል።
ዳኞቹ ይህንን ሁሉ በአእምሯቸው በመያዝ ቀኖናዊ የጋብቻ ሕግ ጥናት እና አተገባበር በሳይንሳዊነት ለሕግ አስከባሪነት ታማኝ መሆንን ያረጋግጣል” ሲሉ ቅዱስነታቸው አፅንዖት ሰጥተው፥ የክርስትና ሕግ እውነተኛ ጥበብ እንዲገለጥ ጸሎት በማቅረብ፥ ለሥራቸው በበጎ አድራጎት ሥራዋ የእውነት ምሳሌ የሆነች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ለምነዋል።
