ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የቫቲካን ከተማ የደህንነት አስከባሪዎችን በቫቲካን ሲቀበሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የቫቲካን ከተማ የደህንነት አስከባሪዎችን በቫቲካን ሲቀበሉ   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የቫቲካን ከተማ የደህንነት አስከባሪዎችን ከልብ አመሰገኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የጣሊያን የደህንነት አስከባሪዎች እና የፖሊስ መኮንኖች በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀብር ሥነ-ሥርዓት እና በካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት እንዲሁም በኢዮቤልዩ ዓመት የመንፈሳዊ ነጋዲያን ደህንነት ለማረጋገጥ ላበረከቱት ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቫቲካን ከተማ ደህንነት አስከባሪዎችን ሰኞ ጥር 11/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ንግግር ባደረጉበት ወቅት፥ “በተለይም የራሴን፣ የባልደረቦቼን፣ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካን፣ የበርካታ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና አገር ጎብኚዎች ደህንነትን ለማረጋገጥ ላበረከታችሁት ተግባር ልባዊ ምስጋናዬን አቅርባለሁ” ብለው አድናቆታቸውንም ገልጸውላቸዋል።

የቫቲካን ከተማ የሕዝብ ደህንነት አስከባሪ አካል የጣሊያን የመንግሥት ፖሊስ ክፍል ሲሆን፥ ከቫቲካን ዘብ ጠባቂዎች እና  ከስዊዘርላንድ ጳጳሳዊ የጥበቃ አካል የተለየ መሆኑ ይታወቃል።

የጣሊያን መንግሥት የፖሊስ አባላት የሕዝብን ደህንነትን ለማስጠበቅ እና ሥርዓት ለማስከበር ሃላፊነት የተሰጣቸው ሲሆን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን እና ተባባሪዎቻቸውን፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዙሪያ ያሉትን መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎችን እንዲሁም በመላው ጣሊያን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝት ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች ደህንነትን ያረጋግጣሉ።

ርዕሠ ቅዱስ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለደህንነት አስከባሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ንግግራቸውን የጀመሩት ለጎርጎሮሳውያኑ 2026 ዓ. ም. በእግዚአብሔር ስም መልካም ምኞታቸውን በማድረስ ሲሆን፥ በቅርቡ በተጠናቀቀው የኢዮቤልዩ ዓመት ውስጥ እና እንዲሁም በሟቹ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀብር ሥነ-ሥርዓት እና በብጹዓን ካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ያበረከቷቸውን ተግባራት በሙሉ አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው፥ “ጥንካሬን በሚፈታትኑ በእነዚያ ከባድ ቀናት ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እርስ በርስ በመገናኘት፥ አንዳንድ ጊዜ በታቀዱ እና ባልተጠበቁ ጊዜያት ውስጥ የሚከሰቱ ክስተቶችን መከተል ችላችኋል” ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በዓመቱ ውስጥ ማለቂያ የሌለው ሕዝብ ድኅንነት ማስጠበቅ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የደኅንነት አስከባሪዎቹ ሁሉንም ነገር በሥርዓት በማከናወን እንደ ሁልጊዜው መስዋዕትነትን፣ የሙያ ብቃትን እና የጥንቃቄ መንፈስን አሳይተዋል” ሲሉ አስረድተው፥  በቅርብ ወራት ውስጥ ብቻ ከ33 ሚሊዮን በላይ መንፈሳዊ ነጋዲያን ሮምን በተለይም የኢዮቤልዩ በዓል ቦታዎችን መጎብኘታቸውን አስታውሰው፥ ከእነዚህም መካከል በዋናነት በቫቲካን የሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ እና አካባቢው እንደሚገኝበት ተናግረዋል።

“የደህንነት አስከባሪዎቹ አመቺ ባልሆኑ እና መጥፎ የአየር ሁኔታ እንዲሁም ብዙውን ጊዜ አድካሚ በሆኑ የጊዜ ሠሌዳዎች ውስጥ ማለቂያ የሌላቸው የበርካታ ሰዎች ሰልፎችን መቆጣጠር፣ እንቅስቃሴዎቻቸውን ማጀብ እና የደህንነት ቦታዎችን መጠበቅ ነበረባችሁ” ብለዋል።

በዚህ ረገድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የፖሊስ መኮንኖቹን እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በተዘዋዋሪ መንገድ በሥራው የተሳተፉት በሙሉ ከቃል ኪዳናችሁ እና ልዩ የሥራ ፍላጎቶች ጋር በሚስማ፣ ብዙውን ጊዜ ትብብራችሁን በሚጠይቁ ቦታዎች ላይ ተገኝታችኋል” ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለደህንነት አስከባሪዎች እና የፖሊስ መኮንኖች ንግግር ሲደርጉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለደህንነት አስከባሪዎች እና የፖሊስ መኮንኖች ንግግር ሲደርጉ   (@Vatican Media)

ባልደረባው ቅዱስ ሚካኤል የመላዕክት አለቃ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሥርዓት እና ደህንነት ዋስትናን ከሚሰጡ ሰዎች እና መስዋዕትነት ከሚያስፈልጉ ስጦታዎች የሚገኙ መሆናቸውን አፅንዖት ሰጥተው፥ “ለሁሉ ሰው ጥቅም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ” ብለዋል።

“ደህንነቱ የተጠበቀ ሥፍራ ለጸሎት ትልቅ እገዛ አለው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “በቅርብ ወራት ውስጥ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ጎብኚዎች፥ ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ረጅም መንገድ በመጓዝ አካላዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስዋዕትነት ከከፈሉ በኋላ ወደ ሮም ደርሰው መንፈሳዊነትን መለማመድ የቻሉት በእናንተ ምክንያት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው የፖሊሶች ጠባቂ የሆነውን ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሚካኤልን በማስታወስ፥ ፖሊሶች በእርሱ በመሳብ በአገልግሎታቸው ወቅት ዕርዳታ ለማግኘት ወደ እርሱ እንዲጸልዩ አሳስበዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ምክር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2013 ዓ. ም. በወቅቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩ ቤነዲክቶስ 16ኛ የተናገሯቸውን ቃላት በማስታወስ፥ “ውድ ወዳጆቼ የእናንተ መኖር መልካም ሥርዓትን እና ሰላማዊ ማኅበራዊ ሕይወትን ለመገንባት መሠረታዊ ከሆኑት የቅዱስ ወንጌል መልዕክት በተጨማሪ የእውነተኛ ሥልጣኔ ምልክት የሆነውን ጸጥታ የበለጠ ለማረጋገጥ ትክክለኛ ዋስትና ይሁን” በማለት፥ የደህንነት አስከባሪዎችን እና ሥራዎቻቸውን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ለሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሚካኤል በአደራ በመስጠት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለደህንነት አስከባሪዎች እና የፖሊስ መኮንኖች ቡራኬያቸውን ሲሰጡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለደህንነት አስከባሪዎች እና የፖሊስ መኮንኖች ቡራኬያቸውን ሲሰጡ   (@Vatican Media)
20 Jan 2026, 15:42