ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እግዚአብሔር ዓለምን ከቅርበት የሚመለከታት መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እሑድ ጥር 3/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አድርሰዋል። ቅዱስነታቸው ከጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ቀድም ብሎ ለምዕመና ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ “ክርስቲያኖች የጥምቀት ስጦታቸውን በማስታወስ በደስታ እና በዘላቂነት ሊመሰክሩ ይገባል” ሲሉ አበረታተዋል።

ክቡራት እና ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! በዛሬው ዕለት የምናከብረው የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል የተለመደው የአምልኮ ወቅት የሚጀምርበትን ጊዜ ይቀድማል። ይህ የአምልኮ ወቅት እግዚአብሔርን አብረን እንድንከተለው፣ ቃሉን አብረን እንድንሰማው እና እርሱ ለሰዎች ያለውን የፍቅር መግለጫን እንድንመስል ይጋብዘናል። ይህን በማድረግ ክርስቲያኖች የሚያደርገንን፣ ከኃጢአት ነፃ የሚያወጣን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተጠቅመን የእግዚአብሔር ልጆች የሚያደርገንን የጥምቀት ምስጢር እናረጋግጣለን እና እናድሳለን።

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ይህ ውጤታማ የጸጋ ምልክት እንዴት እንደሚመጣ ይተርክልናል። ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ፥ ‘የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ሲወርድ ተመለከተ’ (ማቴ 3፡16)። በተመሳሳይ ጊዜ ከተከፈተው ሰማይ ‘ይህ የምወደው ልጄ ነው’ (ቁ. 17) የሚል የአብ ድምፅ ተሰማ ይላል። በዚህ ቅጽበት እግዚአብሔር አብ በታሪክ ውስጥ ይገባል። ወልድ ወደ ዮርዳኖስ ውሃ ሲገባ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ ይወርዳል። በእርሱም በኩል የመዳን ኃይል ሆኖ ተሰጥቶናል።

ውድ ወዳጆቼ ሆይ! እግዚአብሔር ዓለምን ከቅርብ ይመለከታታል። ስለ ሕይወታችን፣ ስለ ችግሮቻችን ወይም ስለምንጠብቀው ነገር ይጨነቃል። ሥጋን በፈጠረበት ቃሉ በጥበብ ወደ እኛ ይመጣል። ለሰው ልጆች በሙሉ ወዳለው አስደናቂ የፍቅር ዕቅድ ይጠራናል።

መጥምቁ ዮሐንስ በመገረም ኢየሱስ ክርስቶስን ‘አንተ ወደ እኔ ትመጣለህን?’ ሲል የጠየቀው ለዚህ ነው (ቁ. 14)። አዎ! በቅድስናው የእግዚአብሔርን ማለቂያ የሌለውን ምሕረት ለመግለጥ ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን እንደ ኃጢአተኛ አድርጎ ለመጠመቅ ፈለገ። ሁላችን ወንድማማቾች እና እህትማማቾች የሆንንበት አንድያ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመግዛት ይልቅ ለማገልገል፣ ከመፍረድ ይልቅ ለማዳን ወደ እኛ ይመጣል። እርሱ ቤዛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኃጢአታችንን በጫንቃው ይሸከማል። የእርሱ የሆነውን የአዲስ እና የዘላለም ሕይወት ጸጋን ይሰጠናል።

የጥምቀት ምስጢር ይህንን ክስተት በእያንዳንዱ ጊዜ እና ቦታ እንዲገኝ፣ እያንዳንዳችንን ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በመቀበል በመንፈሱ እንደገና የተወለዱትን ወንዶች እና ሴቶች የእግዚአብሔር ሕዝብ ያደርጋቸዋል።

ስለዚህ ይህን ቀን ታላቅ ስጦታን የተቀበልንበት ቀን አድርገን በማሰብ በደስታ እና በእውነት ለመመስከር ራሳችንን እናዘጋጅ። በዛሬው ዕለት በእምነት አዲስ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ሆነው የተወለዱ በርካታ ሕጻናትን አጥምቄአለሁ። እንደ አንድ ቤተሰብ በስም የሚጠራንን እና ከክፉ ሁሉ የሚያድነንን የእግዚአብሔርን ፍቅር ማክበር ምን ያህል ደስ የሚያሰኝ ነው! ይህ ከምስጢራት ሁሉ የመጀመሪያ የሆነው ሥነ-ሥርዓት ዘወትር አብሮን የሚጓዝ ቅዱስ ምልክት ነው። የጥምቀት ምስጢር በጨለማ ጊዜ ብርሃናችን ነው። በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ እርቃችን ነው። በሞት ሰዓት ወደ ሰማይ የሚያስገባን በር ነው።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እምነታችንን እና የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ በየቀኑ እንድትጠብቅልን አብረን እንጸልይ።”

 

12 Jan 2026, 16:35