ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለ20 ሕጻናት ምስጢረ ጥምቀት መስጠታቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1981 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የተጀመረውን እና ለ45 ዓመታት የዘለቀውን ሥርዓት በመከተል በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ለ20 ሕጻናት የጥምቀት ምስጢርን አድለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለ45 ዓመታት የዘለቀውን ባሕል ተከትለው በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ለ20 የቫቲካን ሠራተኞች ልጆች ጥር 3/2018 ዓ. ም. የጥምቀት ምስጢርን አድለዋል።

የቀድሞው ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ፈለግ የተከተለ የምስጢረ ጥምቀት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት የተፈጸመው የጎርጎሮሳውያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ የብርሃነ ጥምቀቱ መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ በቀረበበት ጥር 3/2018 ዓ. ም. እንደ ነበር ታውቋል።

አዲስ የይቅርታ ምልክት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ እግዚአብሔር ወደ ምድር በመምጣት በተከፈተ እና ትሑት በሆነ ልቡ እያንዳንዳችንን ሊያገኘን በመምጣት ወደ ታሪክ እንደገባ እና በእይታችን ውስጥ የመዳንን ቃል የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለእኛ ለመግለጥ መፈለጉን አስታውሰዋል። 

“የእግዚአብሔር ልጅ የሰውን ሥጋ በመልበስ ለሁሉም ሰው አስገራሚ ዕድል ይሰጣል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ለነቢያትም ቢሆን አዲስ እና ያልተጠበቀ ጊዜን አምጥቶላቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል። መጥምቁ ዮሐንስ ይህንን ወዲያውኑ ተገንዝቦ “እኔ በአንተ መጠመቅ አለብኝ እንጂ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህ ወይ?” ሲል መጠየቁን አስታውሰዋል።

“በዚህ መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በማናስበው ቦታ በማስቀመጥ በኃጢአተኞች መካከል ቅዱስ እንደሆነ፥ የሰውን ነገር በሙሉ እያሰበ በመካከላችን ሊኖር የሚፈልግ ቅዱስ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ለ20 ሕጻናት የጥምቀት ምስጢር በሰጡበት ወቅት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ለ20 ሕጻናት የጥምቀት ምስጢር በሰጡበት ወቅት   (@Vatican Media)

ኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅን ለመፈጸም በዮሐንስ እጅ መጠመቅ እንደነበረበት ያብራሩት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን ጽድቅ ምንድነው ብለው ላቀረቡት ጥያቄ፥ ጽድቅ የሞት እና የትንሣኤ፣ የይቅርታ እና የኅብረት አዲስ ምልክት እንደሆነ በማስረዳት፥ “በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀው በኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቃን ሆነናል” ሲሉ ተናግረዋል።

“በእግዚአብሔር ሕይወት ድነትን ታገኛለች”

ይህ ምስጢረ ጥምቀት እነዚህ 20 ሕጻናት ከተቀበሉት ምስጢር ጋር ተመሳሳይ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ምክንያቱም በዚህ ምስጢር አማካይነት በእግዚአብሔር የተወደዱ አዲስ ክርስቲያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ይሆናሉ” ብለዋል።

“ሕይወትን ከወላጆቻቸው እንደተቀበሉ ሁሉ አሁን ደግሞ በሕይወት የመኖር ትርጉም የሆነውን እምነትን በዚህ ምስጢር አማካይነት ይቀበላሉ” ሲሉ ተናግረው፥ አንድ ነገር አስፈላጊ መሆኑን ስናውቅ ለምንወዳቸው ሰዎች መስጠት እንደምንፈልግ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ሆኖም ከምግብ ወይም ከልብስ የሚበልጥ ለሕይወት አስፈላጊ የሆነው እምነት የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተው፥ “ሕይወት በእግዚአብሔር ዘንድ ድነትን ታገኛለችና” ሲሉ ገልጸው፥ እግዚአብሔር ለልጆቹ ያለው ፍቅር ለልጆቻቸው እምነትን በሚጠይቁ ወላጆች አማካኝነት በተጨባጭ የሚታይ እና የሚዳሰስ ይሆናል” ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ሕጻናትን ሲያጠምቁ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ሕጻናትን ሲያጠምቁ   (@Vatican Media)

ወደፊት ልጆቻቸውን በእቅፋቸው ለመሸከም የሚከብዳቸው ቀን እንደሚመጣ ነገር ግን እነርሱ የሚደግፏቸው ቀናት እንደሚመጡ ቤተሰቦችን በማበረታታት፥ አንድ የሚያደርግ ጥምቀት ለቤተሰቦች ጥንካሬን እና ጽናትን እንዲሰጥ በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

የምስጢረ ጥምቀት ምልክቶች ለዚህ ምስክር መሆናቸውን ተናግረው፥ የተባረከ ውሃ በመንፈስ ቅዱስ መታጠብን እና ከኃጢአት መንጻትን እንደሚያመላክት፥ ነጭ ልብስ እግዚአብሔር በሰማይ የሚያለብሰውን አዲስ ልብስ እንደሚያመላክት፥ የሚበራው ሻማ ከብርሃነ ትንሳኤው ሻማ የሚመጣ ከሞት የተነሣው የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃን የሚያመላክት መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ ሕጻናቱ በመጪዎቹ ዓመታት እና በሕይወት ዘመናቸሁ ሁሉ ይህን ጉዞ በደስታ እንዲቀጥሉ ጸሎታቸውን በማቅረብ፥ እግዚአብሔር ዘወትር አብሮአቸው እንደሚጓዝ እርግጠኞች ሊሆኑ ይገባል” ሲሉ ቃለ-ምዕዳናቸውን ደምድመዋል።

በቫቲካን ውስት የተፈጸመው የብርሃን ጥምቀቱ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት

 

12 Jan 2026, 16:41