ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ   (@VATICAN MEDIA)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የእግዚአብሔርን ጊዜ እመኑ፣ ወንጌልን በየቦታው አዳርሱ አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዘወትር እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደምያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በጥር 17/2018 ዓ.ም ባደርጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ኢየሱስ አገልግሎቱን በይፋ የጀመረበትን ሁኔታ በማስታወስ ክርስቲያኖች በፍርሃት ወይም በመጥፎ ሁኔታዎች እንዳይሸነፉ፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጊዜ እንዲታመኑ አሳስበዋል። እንዲሁም ምእመናን ወንጌልን በእያንዳንዱ የሰው ልጅ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንዲያውጁ ጥሪ አቅርበዋል፣ ይህም የወንድማማችነትና የሰላም ኃይል ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶችችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በወቅቱ ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አርፈዳችሁ!

ከተጠመቀ በኋላ፣ ኢየሱስ ይፋዊ ስብከቱን ሲጀምር የመጀመሪያዎቹን ደቀ መዛሙርቱን መረጠ ፤ እነሱም ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን፣ ወንድሙ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ (ማቴ 4:12-22) ነበሩ። ከዛሬው ወንጌል ስለዚህ ትዕይንት በቅርበት ስናስብ፣ ሁለት ጥያቄዎችን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። የመጀመሪያው የኢየሱስን ተልዕኮ ጊዜ የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለመስበክና ሐዋርያቱን ለመጥራት የመረጠውን ቦታ ይመለከታል። ልንጠይቅ እንችላለን፡- መቼ ጀመረ? የትስ ጀመረ?

በመጀመሪያ፣ ወንጌል ኢየሱስ ስብከቱን የጀመረው “ዮሐንስ እንደታሰረ በሰማ ጊዜ” (ማቴ 4፡12) እንደሆነ ይነግረናል። ስለዚህ፣ ይፋዊ ስብከቱ ያለጊዜው የመጣ ነበረ። መጥምቁ ዮሐንስ ገና እንደ ታስረ ነበር፣ የሕዝቡ መሪዎችም የመሲሑን አዲስነት ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበሩም። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ጊዜ ነበር። ሆኖም፣ ኢየሱስ የምሥራቹን ብርሃን ማምጣት የጀመረው በዚህ ጨለማ ሁኔታ ውስጥ ነበር፡- “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” (ማቴ 4፡17)።

በሕይወታችን፣ በግልም ሆነ በቤተ ክርስቲያን፣ ውስጣዊ ትግሎች ወይም መጥፎ ነገሮች ወንጌልን ለማወጅ፣ ውሳኔ ለማድረግ፣ ምርጫ ለማድረግ ወይም ሁኔታን ለመለወጥ ትክክለኛው ጊዜ እንዳልሆነ እንድናምን ሊያደርጉን ይችላሉ። በዚህ መንገድ ግን፣ ውሳኔ ባለማድረግ ሽባ ወይም ከልክ በላይ ጥንቃቄ በማድረግ ልንታሰር እንችላለን፣ ወንጌል ግን እንድንታመን ያደፋፍረናል። እግዚአብሔር ሁልጊዜ በሥራ ላይ ነው፤ ዝግጁ ባንሆንም ወይም ሁኔታው ​​መጥፎ በሚመስልበት ጊዜም እንኳ እያንዳንዱ ጊዜ “የእግዚአብሔር ጊዜ” ነው።

ቅዱስ ወንጌሉ ኢየሱስ ሕዝባዊ ተልእኮውን የጀመረበትን ትክክለኛ ቦታ ግንዛቤ ይሰጠናል። “ናዝሬትን ትቶ በቅፍርናሆም መኖሪያውን እንዳደረገ” ሲል ተናግሮናል  (ማቴ 4፡13)። ይህን ለማድረግ፣ በገሊላ ኖረ - በአብዛኛው አረማዊ ክልል - ንግድ ወደ መስቀለኛ መንገድ እና የመገናኘት ቦታ የተለወጠ ሥፍራ ነበር። የተለያየ አመጣጥ እና የሃይማኖት ትስስር ባላቸው ሰዎች የሚዘዋወርበት የባህል ብዝሃነት ክልል ብለን ልንገልጸው እንችላለን። በዚህ መልኩ፣ ወንጌል መሲሑ ከእስራኤል ሲመጣ የምድሩን ድንበር አልፎ ለሁሉም የሚቀርብ አምላክን እንደሚያውጅ ያሳያል። እርሱ ማንንም የማያገል፣ ለንጹሐን ብቻ ሳይሆን ወደ ሰው ሁኔታዎችና ግንኙነቶች ውስብስብነት ሙሉ በሙሉ የሚገባ አምላክ ነው። ስለዚህ፣ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን፣ እኛም የመገለልን ፈተና ማሸነፍ አለብን። ወንጌል በሁሉም ቦታ መታወጅና መኖር አለበት፣ በሁሉም ግለሰቦች፣ ባህሎች፣ ሃይማኖቶችና ሕዝቦች መካከል የወንድማማችነትና የሰላም እርሾ ሆኖ ያገለግላል።

ወንድሞችና እህቶች፣ እንደ መጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት፣ የጌታን ግብዣ በደስታ እንድንቀበል ተጠርተናል፣ የእርሱ መገኘትና ፍቅሩ በሕይወታችን ውስጥ በእያንዳንዱ ጊዜና ቦታ እንደሚንሰራፋ እናውቃለን። ድንግል ማርያም ይህንን ውስጣዊ እምነት እንድታስገኝልንና በጉዟችን እንድትረዳን እንጸልይ።

26 Jan 2026, 08:57