ር.ሊ.ጳ ሊዮ የገና በዓል ደስታ መንፈሳዊ ጉዞአችንን እንዲቀጥል ያድርግልን ማለታቸው ተገለጸ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በገና ሁለተኛ እለተ ሰንበት ላይ በታኅሣስ 26/2018 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረጉት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ባደረጉት አስተንትኖ ምእመናን ወደ ክርስቶስ ልጅ እንዲቀርቡ ይጋብዛሉ እና እያንዳንዱ እውነተኛ የእግዚአብሔር አምልኮ ለሰው ልጅ እንክብካቤ እንደሚያስፈልግ ያስታውሳሉ።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
"የገና ደስታ ጉዞአችንን እንድንቀጥል ያበረታታናል" ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቫቲካን በቀትር ሰዓት በተከናወነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ የገለጹ ሲሆን ቅዱስ አባታችን በገና በዓል ሰሞን በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምእመናን የገናን ምኞቶች በማደስ እና የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ዘንድ በጥር 27/2018 ዓ.ም በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ የኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት የቅዱስ ጴጥሮስ ባሲልካ ቅዱስ በር መዘጋት እንደሚጠናቀቅ በማስታወስ በዚህ አውድ ውስጥ፣ ቅዱስ አባታችን አሁንም የተጠመቅንበት የገና ምሥጢር "የተስፋችን መሠረት የእግዚአብሔር ልጅ ሥጋ መልበሱ የሚከበርበት ምስጢረ ሥጋዌን ያስታውሰናል" ሲሉ አስታውሰዋል።
በእለቱ በተከናወነው ሥርዓተ አምልኮ ላይ ከቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ተወስዶ በተነበበው የእግዚአብሔር ቃል ላይ “ቃል ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ” (ዮሐ. 1:14) ሲል የተናገራቸውን ቃላት በማስታወስ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የክርስቲያን ተስፋ የተመሠረተው በተስፋ ትንበያዎች ወይም በሰው ስሌት ላይ ሳይሆን፣ በሕይወት ስንጓዝ ብቻችንን እንዳንሆን እግዚአብሔር ጉዟችንን ለማካፈል ባደረገው ውሳኔ ላይ ነው” ብለዋል።
ተስፋችን በሕይወታችን ውስጥ በእግዚአብሔር ሥራ እንደገና ይነቃቃል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ መሆኑን አስረድተዋል። “በኢየሱስ” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስታውሰዋል፣ “በኢየሱስ” እግዚአብሔር “ከእኛ አንዱ ሆነ፣ ከእኛ ጋር ለመቆየት መረጠ፣ እናም ለዘላለም ከእኛ ጋር ለመሆን ፈለገ” ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደተናገሩት ተስፋችን በኢየሱስ መምጣት በሰው ሥጋ ድክመት “እንደገና ይነቃቃል” ብለዋል። በተመሳሳይ ጊዜ፣ ለእግዚአብሔርም ሆነ ለባልንጀሮቻችን “ሁለት እጥፍ ቁርጠኝነት” እንደሚሰጠን አፅንዖት ሰጥተዋል።
ወደ እግዚአብሔር ቁርጠኝነት በመመለስ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሥጋ ስለነበረ፣ የሰው ልጅ ድክመቶችን እንደ መኖሪያ ቦታው ከመረጠ በኋላ፣ “ስለ እርሱ እንዴት እንደምናስብ፣ ከኢየሱስ ሥጋ ጀምሮ፣ ረቂቅ አስተምህሮ ሳይሆን፣ እንደገና እንድናስብ ተጠርተናል” ብለዋል።
መንፈሳዊነታችንን እና የእምነት መግለጫዎቻችንን ሲመረምሩ
“ስለዚህ በእውነት ሥጋ መሆናቸውን ለማረጋገጥ መንፈሳዊነታችንን እና እምነታችንን የምንገልጽባቸውን መንገዶች ዘወትር መመርመር አለብን” ሲሉ አጥብቀው ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው ይህንን ሲናገሩ፣ “በኢየሱስ የሚገናኘንን” አምላክ በትክክል ማሰላሰል፣ ማወጅ እና መጸለይን ይጠይቃል ብለዋል።
“እሱ ከእኛ በላይ ባለው ፍጹም ሰማይ ውስጥ የሩቅ አምላክ አይደለም” ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ “ነገር ግን በአቅራቢያው ያለ እና ደካማ በሆነው ምድራችን የሚኖር፣ በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ፊት የሚገኝ እና በዕለት ተዕለት ሕይወት ሁኔታዎች ውስጥ ራሱን የሚገልጥ አምላክ ነው” ሲሉ አክለው ተናግረዋል።
እውነተኛ የእግዚአብሔር አምልኮ ለሰው ልጅ እንክብካቤ ይጠይቃል
ለወንዶችና ለሴቶች ሁሉ ያለን ቁርጠኝነትም ወጥነት ያለው መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። “እግዚአብሔር ከእኛ አንዱ ስለሆነ”፣ ቅዱስ አባታችን እያንዳንዱ የሰው ልጅ ፍጡር የእሱን ምስል የያዘ እና “የብርሃኑን ብልጭታ የያዘ” መሆኑን አስታውሰዋል።
"ይህ የእያንዳንዱን ሰው የማይናወጥ ክብር እንድንገነዘብ እና እርስ በርስ በመዋደድ ራሳችንን እንድናቀርብ ይጠይቀናል" ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለው የገለጹ ሲሆን "የወንድማማችነት እና የኅብረት መስፋፋትን ለማበረታታት ተጨባጭ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል"፤ ይህም አንድነት "የሁሉም የሰው ልጅ ግንኙነቶች መስፈርት" እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።
የገና ደስታ መንገዳችንን የሚመራው
"እግዚአብሔር ሥጋ ለበሰ፤ ስለዚህ ለሰው ልጅ ግድየለሽ መንፈስ ካለን እውነተኛ የእግዚአብሔር አምልኮ የለንም" ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አስጠንቅቀዋል።
በመጨረሻም፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ "የገና ደስታ በጉዟችን እንድንቀጥል ያበረታታናል" ያሉ ሲሆን "ድንግል ማርያም እግዚአብሔርንም ሆነ ባልንጀራችንን ለማገልገል የበለጠ ዝግጁ እንድንሆን እርሷን እንለምን" ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው አስተንትኖዋቸውን አጠናቀዋል።
