ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የስፔን ምዕመናን ቅዱሳንን በማየት ኢየሱስን እንዲከተሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከቪላኖቫ የቅዱስ ቶማስ ቁምስና የመጡ ነጋዲያንን በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ ነጋዲያኑ ወደ ሮም ለመድረስ 1,900 ኪ. ሜ. መጓዝቸውንም በማስታወስ የሐዋርያው ጴጥሮስ ተተኪ ለሆኑት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ላደረጉት የጸሎት እና የልግስና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የቁምስናቸው ባልደረባ የሆነውን ቅዱስ ቶማስን በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የቪላኖቫው ቅዱስ ቶማስ ለእግዚአብሔር ተግባር ሕይወቱን ክፍት ያደረገ ነበር” ብለው፥ ይህ ምሳሌው ለቤተ ክርስቲያን እና ለዘመኑ ማኅበረሰብ ብዙ መልካም ነገሮችን ለማድረግ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
አልካላ ደ ሄናሬስ ከተማ በስፔን ውስጥ የቅዱስ አጎስጢኖስ ሕይወትን እና ቅርስን ለመጠበቅ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ከዚያም በቅዱስ ቶማስ ልዩ ባህሪያት ልባቸው መነካቱንም ተናግረዋል።
ለሕይወት የሚሆን ቅርስ
“የቅዱስ ቶማስ ሕይወት እና ጽሑፎች በእያንዳንዱ ቅጽበት በእግዚአብሔር ፊት በማያቋርጥ ጸሎት መቆየትን ያሳያሉ” ብለው፥ ይህም የቅዱስ ቶማስን ጥልቅ የውስጥ ሕይወት ግለጽ በማድረግ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲሰማ አስችሎታል” ብለዋል።
ከዚህም በላይ የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር አባል እና ጳጳስ የነበረው ቅዱስ ቶማስ በአድካሚ ሥራው ይታወቅ እንደ ነበር አስታውሰው፥ ይህም ሁሉንም ነገር በፍጥነት እና በቀላሉ በሚያቀርብ ዓለም ውስጥ የሚፈታተን ገጽታ እንደሆነ አብራርተዋል።
የቅዱስ ቶማስ ሥራ ወዳድነት፣ ድካም፣ ትኅትና፣ ጨዋነት እና ሐዋርያዊ ቅንዓት ሁሉም ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበላቸውን ስጦታዎች እና ተሰጥኦዎች እንዲያውቅ እና እነዚህን ስጦታዎች ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲጠቀሙበት የተጠራ መሆኑን ሊያስታውስ እንደሚችል አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ የስፔኑ ቅዱስ ለድሆች ያለው ፍቅር “ለጋስ የእግዚአብሔር ሰው” የሚል ማዕረግ ያስገኘለት መሆኑን በማስታወስ፥ “ይህ ባህሪ በአልካላ ደ ሄናሬስ ነጋዲያን ሥነ-ምግባር እና ተጨባጭ ምልክት በግልጽ የሚታይ ነው” በማለት ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው ከነጋዲያኑ ጋር ያደረጉትን ስብሰባ ሲዘጉ፥ ነጋዲያኑ የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ እንዲከተሉ በማበረታታት፣ ተነሳሽነታቸውንም ለማሳደግ የቅዱሳንን ምሳሌ እንዲከተሉ ካሳሰቡ በኋላ፥ የቫልኖቫዋ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዘወትር ዕርዳታን በመለመን የእግዚአብሔርን ቡራኬ ሰጥተዋቸዋል።
