ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በኢስታንቡል የመንፈስ ቅዱስ ካቴድራል ቅጥር ግቢ ከምዕመናን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በኢስታንቡል የመንፈስ ቅዱስ ካቴድራል ቅጥር ግቢ ከምዕመናን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኢስታንቡል ከምእመናን ጋር ሰላምታ ተለዋወጡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኢስታንቡል በሚገኘው በመንፈስ ቅዱስ ካቴድራል ውስጥ ከተሰበሰቡት የቱርክ ካቶሊክ ምዕመናን ጋር ሰላምታ ተለዋውጠዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በአሜሪካ ቴክሳስ ከተማ ውስጥ የሚታነጽ ካቶሊካዊ የቁምስና ቤተ ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይን ባርከዋል። የመሠረት ድንጋዩን ወደ ቅዱስነታቸው ያደረሱት በቱርክ መንፈሳዊ ንግደት በማድረግ ላይ የሚገኙት ካኅን መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢስታንቡል በሚገኘው የመንፈስ ቅዱስ ካቴድራል ቅጥር ግቢ ውስጥ ዓርብ ኅዳር 19/2018 ዓ. ም. ጠዋት የተሰበሰቡት ምዕመናን “ረጅም ዕድሜ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ!” በማለት ለቅዱስነታቸው መልካምን ተመኝተውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኢስታንቡል የመንፈስ ቅዱስ ካቴድራል ቅጥር ግቢ በተዘጋጀው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ከጳጳሳት፣ ከካኅናት፣ ከዲያቆናት፣ ከገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ከተቀረው ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ጋር የተገናኙት በቱርክ እና በሊባኖስ በማድረግ ላይ ባሉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሁለተኛ ቀን ላይ እንደ ነበር ተገልጿል።

በቱርክ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1934-1945 ዓ. ም. በሐዋርያዊ እንደራሴነት ያገለገሉ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ 23ኛ ምስል ከሚገኝበት ዝቅ ብሎ በሚገኘው የካቴድራሉ ዋና መግቢያ በር ፊት ለፊት የነበሩ የበርካታ አገራት እንግዶች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

ምንም እንኳን በቱርክ የሚገኙ የካቶሊክ ምዕመናን ቁጥር ከጠቅላላው ሕዝብ ቁጥር 0.05% እና ብዙዎቹ የውጭ ዜጎች ቢሆኑም በካቴድራሉ የተገኙት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኢስታንቡል ከምዕመናን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኢስታንቡል ከምዕመናን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ   (@Vatican Media)

በካቴድራሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከተገኙት ምዕመናን መካከል በኢሳትንቡል የምትገኝ ልጇን ለመጎብኘት ከካሜሩን የመጡት ማሪ-ፍራንሷ እና ከፖላንድ ሼቼሲን ለትምህርት የመጣ የ21 ዓመቱ ተማሪ ማቴውስዝ ዛጅዴኪ ይገኙበታል።  

የመሠረት ድንጋይ ቡራኬ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ካቴድራሉ ሲደርሱ በአሜሪካ ዳላስ ከተማ አዲስ የሚገነባ ቤተ ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይን ባርከዋል። በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ የሚገኝ የዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ለማክበር ከቁምስናቸው ምዕመናን ጋር ወደ ኢስታንቡል የመጡት በዳላስ ቴክሳስ የሚገኝ የቅዱስ አጎስጢኖስ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ ካኅን አባ ፓውሎ ካፕራ በከተማዋ አዲስ የሚገነባ ቤተ ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ በቅዱስነታቸው አስባርከዋል።

ከፖላንድ ለትምህርት ከመጣ ተማሪ ማቴውስዝ ዛጅዴኪ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ
ከፖላንድ ለትምህርት ከመጣ ተማሪ ማቴውስዝ ዛጅዴኪ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ

አባ ፓውሎ ካፕራ ከቴክሳስ ይዘው የመጡት ድንጋይ አዲስ ሊገነቡት ያሰቡት ቁምስና የመሠረት ድንጋይ እንደ ሆነ ተናግረው፥ አሁን ያለው ቤተ ክርስቲያናቸው በቁጥር በርካታ የስደተኛ ማኅበረሰብ በሚገኝበት አካባቢ ያለ እና 500 ሰዎችን ብቻ የመያዝ አቅም ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚመጡት በርካታ ምዕመናን በቦታ ጥበት ምክንያት አገልግሎቱን ከውጭ ሆነው ለመከታተል እንደሚገደዱ ግልጸው፥ ከዚህ የተናሳ ዕቅዳቸው እስከ 900 የሚደርሱ ምዕመናንን ማስተናገድ የሚችል ቤተ ክርስቲያን መገንባት እንደ ሆነ አስረድተዋል።

አባ ፓውሎ ካፕራ  የመሠረት ድንጋይ ይዘው
አባ ፓውሎ ካፕራ የመሠረት ድንጋይ ይዘው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ወደ ካቴድራሉ ሲደርሱ ለጳጳሳት፣ ለካኅናት፣ ለዲያቆናት፣ ለገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ለምዕመናን ሰላምታቸውን አቅርበው የመሠረት ድንጋዩን ከባረኩ በኋላ ምዕመናኑም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸውላቸዋል።

በቦታው ከነበሩት ካኅናት መካከል አንዱ የሆኑት አባ ሉካ፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በዚህ ወቅት ወደ ቱርክ መምጣታቸው ለእኛ ትልቅ ስጦታ እና ትልቅ በረከት ነው” ሲሉ ገልጸው፥በእርግጥም ቱርክ የክርስትና እምነታችን ብዙ ሥሮች ያሉባት ቅድስት ምድር ናት” በማለት አስረድተዋል።

አባ ሉካ አክለውም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቅርብነት የተሰማቸው መሆኑን ተናግረው፥ “ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ እና በተጨማሪም ሚስዮናዊ በመሆናቸው የቤተ ክርስቲያኖቻችንን እውነታ ያውቃሉ” ብለው፥ “ይህም የአዲስ አማኒያን ሕይወት አባል የሆኑ ካህናት ጥሪ አካል ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

አባ ፓውሎ ካፕራ ከዳላስ ከመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን ጋር
አባ ፓውሎ ካፕራ ከዳላስ ከመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን ጋር

 

01 Dec 2025, 14:42