ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የዘንድሮውን የኢየሱስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት እና የገና ዛፍን ለቫቲካን ከለገሱት ቡድኖች ጋር ተገናኝተዋል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የዘንድሮውን የኢየሱስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት እና የገና ዛፍን ለቫቲካን ከለገሱት ቡድኖች ጋር ተገናኝተዋል  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሲድኒ የአሸባሪዎች ጥቃት የተጎዱትን በጸሎታቸው አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የዘንድሮውን የኢየሱስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት እና የገና ዛፍን ለቫቲካን በስጦታነት ለለገሱት ቡድኖች ንግግር ባደረጉበት ወቅት፥ የፀረ-ሴማዊነት ጥቃት እንዲያበቃ አሳስበው፥ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን ቅርበት በማስረዳት በጦርነት እና በዓመፅ ምክንያት የሚሰቃዩትን እና በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ በአይሁድ ማኅበረሰብ ላይ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት የተጎዱትን በጸሎት እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንቶች እና የገና ዛፎች የእምነት እና የተስፋ ምልክቶች ናቸው” ሲሉ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሰኞ ታኅሳስ 6/2018 ዓ. ም. ምእመናን እግዚአብሔር የሰላም እና የወንድማማችነት ስጦታ በውስጣቸው እንዲያድስ በጸሎት እንዲጠይቁ አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም በጦርነት እና በዓመፅ ምክንያት የሚሰቃዩትን በሙሉ በተለይም እሁድ ዕለት በአውስትራሊያ ሲድኒ ውስጥ በአይሁድ ማኅበረሰብ ላይ በተፈጸመው የሽብር ጥቃት የተጎዱ ሰዎችን ለእግዚአብሔር በአደራ በማቅረብ፥ ፀረ-ሴማዊ ጥቃት እንዲያበቃ እና ጥላቻ ከሰው ልብ ውስጥ እንዲወገድ ጥሪ አቅርበዋል።

የትሕትና እና የፍቅር ምስጢር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጥሪያቸውን ያቀረቡት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የተዘጋጀውን የኢየሱስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት እና የገና ዛፍን ለቫቲካን ለለገሱት የማኅበረሰቦች ተወካዮች በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ ሰኞ ታኅሳስ 6/2018 ዓ. ም. በቀረበው የኢየሱስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት ላይ እንደ ነበር ታውቋል።

በደቡብ ጣሊያን ከኖሴራ ኢንፌሪዮር-ሳርኖ ሀገረ ስብከት የተላከው እና በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የተዘጋጀው የኢየሱስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት “ከመላው ዓለም የሚመጡ ምዕመናንን፥ እግዚአብሔር ወደ ሰው ልጅ እንደሚቀርብ፣ ከእኛ አንዱ እንደሚሆን እና በሕጻንነቱ ወደ ታሪካቸው መግባቱን ያስታውሳቸዋል” ብለዋል።

“በቤተልሔም የነበረው ድህነት የትሕትና እና የፍቅር ምስጢር ላይ እናስተነትናለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ይህም ወደ ራሳችን እንደገና ተመልሰን ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት እንድንመሠርት ይጋብዘናል” ብለዋል።

የሕይወት እና የተስፋ ምልክት

በሰሜን ጣሊያን ለቦልዛኖ ውብ ክፍለ ሀገር ተወካዮችን ሰላምታቸውን በማቅረብ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የተዘጋጀውን የኢየሱስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት እና የገና ዛፍ በማስታወስ፥ በክረምት ወቅት የገና ዛፍ የሕይወት ምልክት እና የማይጠፋ ተስፋን ያስታውሰናል” ብለዋል።

እንዲሁም “በዛፉ ላይ ያሉት መብራቶች ኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአትን ጨለማ ለማስወገድ እና መንገዳችንን ለማብራት የመጣው የዓለም ብርሃን መሆኑን ያስታውሱናል” ብለው፥ በቫቲካን ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የታሰቡ ሌሎች የዛፍ ችግኞች ከደቡብ ጣሊያን የመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሕይወትን ከፅንስ ጀምሮ መጠበቅ እንደሚገባ የቀረበ ጥሪ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ የተዘጋጀውን የኢየሱስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት ላበረከቱት የኮስታሪካ ተወካዮች ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ይህም “የደስታ ልደት” የተሰኘው የኮስታሪካ አርቲስት የፈጠራ ሥራ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

ትዕይንቱ በ28,000 ሪባን የተጌጠ ሲሆን እያንዳንዱ ሪቫን በካቶሊክ ድርጅቶች ጸሎት እና ድጋፍ ከፅንስ ማስወረድ የተረፈ ሕይወትን የሚወክል እና ለተቸገሩ እናቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ የሚገልጽ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በብርሃነ ልደቱ በዓል ወቅት የሰላም መልዕክት ከፅንስ ጀምሮ ሕይወትን መንከባከብ እንደሚገባ ጥሪ በማቅረባቸው አርቲስቶችን አመስግነዋል።

“የሕጻኑ ክርስቶስ ርኅራሄ ሕይወታችንን ያብራልን”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመጨረሻም፥ በቫቲካን ውስጥ እና በዙሪያው ያሉ ቦታዎችን በብርሃነ ልደቱ ወቅት ለማስጌጥ ጥረት ያደረጉት የቫቲካን ሠራተኞችን አመስግነው፥ በመጨረሻ “ሁሉም ሰው የሕፃኑ ኢየሱስ ርኅራሄ ሕይወታችንን እንዲያበራ እና የእግዚአብሔር ፍቅር እንደ ዛፍ ቅጠል ለምልሞ በውስጣችን ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

 

16 Dec 2025, 16:29