ፈልግ

ዓለም አቀፍ የገዳማውያት ጠቅላይ አለቆች ኅብረት ዓለም አቀፍ የገዳማውያት ጠቅላይ አለቆች ኅብረት   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በዓለም ዳርቻ በወንጌል ምስክርነት ተልዕኮ ላይ የሚገኙ ገዳማውያትን አመሰገኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የተመሠረተበትን 60ኛ ዓመቱን በማክበር ላይ ለሚገኝ ዓለም አቀፍ የገዳማውያት ጠቅላይ አለቆች ኅብረት መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው የምሥረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በጻፉት መልዕክት፥ ገዳማውያት እህቶች የሚያገኟቸውን ሰዎች ቁስል መፈወስ ይችሉ ዘንድ “የተስፋ ነጋዲያን እና ሚስዮናዊ ደቀ መዛሙርት” እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ ተከትሎ የገዳማውያን እና ገዳማውያት ሕይወት በዘመናዊው ዓለም ውስጥ እንዲታደስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ማሳሰባቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ገዳማውያቱ ተልዕኳቸውን በታማኝነት እና በድፍረት ያከናወኑ በመሆናቸው ዓለም አቀፍ የገዳማውያት ጠቅላይ አለቆች ኅብረት አባላትን አመስግነዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የዓለም አቀፍ ገዳማውያት ጠቅላይ አለቆች ኅብረት ፕሬዝደንት ለሆኑት እህት ኦና ኦሼ በላኩት መልዕክት፥ “እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሳስ 8/1965 ዓ. ም. የተመሠረተው ኅብረታቸው የምሥረታውን 60ኛ ዓመት በሚያከብርበት በዚህ ወቅት ኅብረቱ ተልዕኮውን ላሳካባቸው በርካታ መንገዶች ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የገዳማውያት ጠቅላይ አለቆች ኅብረት (UISG) በስልሳ ዓመታት ውስጥ ከስድስቱ አህጉራት የተወጣጡ ጠቅላይ አለቆች በመካከላቸው የውይይት መድረክን በማመቻቸት የጥሪያቸው ሃብት እና የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ለቤተ ክርስቲያን እና ለዓለም ጥቅም ማካፈሉን አስታውሰዋል።

የተስፋ ሚስዮናውያን ደቀ መዛሙርት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ዘመኑ በፈጣን ለውጥ ውስጥ እንደሚገኝ እና በበርካታ አንገብጋቢ ፍላጎቶች የተሞላ መሆኑን ገልጸው፥ ገዳማውያቱ ለመተባበር እና ለሚስዮናዊነት ባላቸው ቁርጠኝነት ጠንካራ የወንጌል መስካሪዎች እንደሚሆኑ ተናግረው፥ “የምሥረታ በዓላቸው ከኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት ጋር የሚገጣጠም ልዩ ጸጋ ነው” ብለዋል።

“በዚህ በተቀደሰ ጊዜ እያንዳንዷ የኅብረቱ አባል መንፈሳዊ ተጓዥ እና የተስፋ ሚስዮናዊት ደቀ መዛሙርት እንድትሆን የተጠራች፥ ይህ ጥሪ ገዳማውያቱ በቅድስና ላይ የተመሠረቱ፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ፣ እምነትን ለማሳደግ፣ ቁስሎችን ለመፈወስ እና የእግዚአብሔርን ሕዝብ በርኅራኄ እና በደስታ ልብ ለማገልገል ያላቸው ምኞት እንዲታደስ አድርጓል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መልዕክታቸውን፥ የገዳማውያቱን ሐዋርያዊ አገልግሎት የቤተ ክርስቲያን እናት እና የታማኝ ደቀ መዝሙርነት ምሳሌ ለሆነችው ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአደራ በመስጠት ደምድመዋል።

ታሪክ ገና ይጻፋል

ከስልሳ ዓመታት በፊት ዓለም አቀፍ የገዳማውያት ጠቅላይ አለቆች ኅብረት (UISG) የተመሠረተበት ዋና ዓላማ በአንድነት ለመጓዝ፣ ለመደማመጥ እና ኅብረትን ለመገንባት መሆኑን የኅብረቱ ፕሬዝደንት እህት ኦና ኦሼ በመግለጫቸው ተናግረው፥ “ዛሬ የምናከብረው በዓል ኅብረቱ ዘወትር የሚሻሻል፣ ወደ ፊት የሚመለከት እና ለአዳዲስ አድማሶች ክፍት በመሆን ታሪክ ገና የሚጻፍ መሆኑን የሚገልጽ ነው” ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የገዳማውያት ጠቅላይ አለቆች ኅብረት (UISG) 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ፥ “የገዳም ሕይወት የሚለወጥ ተስፋ” በሚል ርዕሥ አዲስ ዘጋቢ ፊልም መዘጋጀቱን ገልጸው፥ ዘጋቢ ፊልሙ የልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ የገዳማውያት ማኅበራት ትስስርን የሚከታተል እና የምንኩስና ሕይወት በታሪኮች፣ በባህሎች እና በአህጉራት ዘንድ ያለውን ዘመናዊ ገጽታን የሚያሳይ መሆኑን አስረድተዋል።

17 Dec 2025, 14:10