ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሰላምታ ሲያቀርቡ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሰላምታ ሲያቀርቡ  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የብርሃነ ልደቱን በዓል የተስፋ እመቤታችን እንድትመራው በጸሎት ጠየቁ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. ለአንድ ዓመት ሲከበር ቆይቶ በብርሃነ ልደቱ ሰሞን በሚጠናቀቅ የኢዮቤልዩ ዓመት መጨረሻ የሚቀርበውን የብርሃነ ልደቱን መስዋዕተ ቅዳሴ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደሚመሩት ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በብርሃነ ልደቱ ወቅት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የሚያቀርቡትን የተስፋ ኢዮቤልዩ ዓመት መዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴን የተስፋ እናት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድታጅበው በማለት በጸሎት ተማጽነዋል።

ቅዱስነታቸው መስዋዕተ ቅዳሴውን በሚመሩበት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከደቡብ ጣሊያን የተላከው የተስፋ እናት የእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ምስል እንደሚኖር የተገለጸ ሲሆን፥ ከእንጨት የተሠራው የተስፋ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል በብርሃነ ልደቱ ሰሞን በሙሉ በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ውስጥ እንደሚሆን ተገልጿል።

የተስፋ እናት የሆነች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል ወደ ቫቲካን የደረሰው ሰኞ ታኅሳስ 13/2018 ዓ. ም. ሲሆን፥ ወደመጣበት ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ቁምስና የሚመለሰው በታኅሳስ 28/2018 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል።

የተስፋ እመቤታችን

የተስፋ እመቤታችን ምስል፥ ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን ኢየሱስ የክርስቶስን በእቅፏ ይዛ መሬት ላይ የተተከለውን የወርቅ መልሕቅ በቀኝ እጇ መያዟን እንደሚያሳይ ተመልክቷል። መንፈሳዊ ምስሉ ከደቡብ ጣሊያን ሳሌርኖ ከተማ ወደ ቫቲካን የተላከው የተስፋ ኢዮልዩ ዓመት በተከፈተበት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. እንደ ነበር ይታወሳል።

የተስፋ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል የተሠራው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ የማርያምን ዓመት ባወጁበት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1954 ዓ. ም. እንደ ነበር የሚታወስ ሲሆን፥ በቅዱስ ማርቆስ ቁምስና ውስጥ በክብር ከመቀመጡ በፊት የአካባቢው ምዕመናን አቀባበል ማድረጋቸውም ይታወሳል።

በበጋ ወቅት ጎብኚዎች እጅግ የሚወደድ ምስል ነው

አንድ ከአርባ አምስት ሜትር ቁመት ያለው ይህ የእመቤታችን ምስል በበጋ ወቅት ወደ ቅዱስ ማርቆስ ቁምስና በሚመጡ በርካታ የአገር ጎብኚዎች ጥልቅ አክብሮት የሚሰጠው እንደሆነ ታውቋል።

የተስፋ እናት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በነሐሴ ወር የመጨረሻ እሁድ የሚከበር ሲሆን፥ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በተስፋ እመቤታችን ማርያም ስም የሚከበር ብቸኛው በዓል እንደ ሆነ ታውቋል።

ከሩቅ አካባቢ የመጣ መንፈሳዊ ምስል

የተስፋ እናት እመቤታችን ቅድስት ማርያም ምስል የመጣው በደቡብ ጣሊያን ውስጥ በሲሌንቶ እና በቫሎ ዲ ዲያኖ ብሔራዊ ፓርክ መካከል ከሚገኝ አካባቢ ሲሆን፥ ይህ አካባቢ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ከሚገኝበት እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ዘወትር ማግኘት ከማይቻልበት ክልል እንደሆነ ታውቋል።

ከአንድ ዓመት በፊት በወቅቱ የቅዱስ ማርቆስ ቁምስና መሪ ካኅን አባ ፓስኳሌ ጋርጆኔ የተስፋ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ምስል ወደ ቫቲካን ለማምጣት ሃሳብ አቅርበው እንደ ነበር እና በበርካታ የጣሊያን ማኅበረሰቦች ሕይወት ብርሃን ለማብራት መንገድ እንዲከፍት በማሰብ እንደሆነ ታውቋል።

አካባቢው ብቸኝነት የሚሰማቸው አረጋዊያን ያሉበት እና የኑሮ አለመመጣጠን እየፋት የመጣበት ክልል እንደሆነ ታውቋል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተስፋ ተምሳሌት ሆና መከራዎችን በመሸከም በእናትነት ጥበቃዋ መጽናናትን እንደምትሰጣቸው ታውቋል።

22 Dec 2025, 15:51