ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ወጣቶች በብርሃነ ልደቱ ወቅት ከቅርብ ሰው ጋር ሰላም እንዲፈጥሩ አሳሰቡ
[ Photo Embed: ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከማኅበሩ አባላት ጋር ሲገናኙ]የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የ “ጣሊያን ካቶሊክ ተግባር” ማኅበር ወጣት አባላት ከብርሃነ ልደቱ በዓል በፊት ከቅርብ ሰው ጋር ሰላም እንዲፈጥሩ አሳስበው፥ ሰላም ከማንኛውም ስጦታ የበለጠ ውድ መሣሪያ መሆኑን አስረድተዋል።
“ሁላችንም በጦርነት ለተጎዱ አገራት ሰላም እንመኛለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን ስምምነት እና አክብሮት የሚጀምረው በዕለት ተዕለት ግንኙነቶቻችን፣ በቤቶቻችን፣ በቁምስናዎቻችን፣ ከትምህርት ቤት ጓደኞች ጋር፣ በስፖርት ማዕከላት ውስጥ በምንለዋወጥባቸው ምልክቶች እና ቃላት መሆኑን እናስታውስ” ሲሉ ዓርብ ታኅሳስ 10/2018 ዓ. ም. ከቡድኑ አባላት እና መሪዎቻቸው ጋር በቫቲካን በተገናኙበት ወቅት ተናግረዋል።
በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ. 9 ላይ “ክርስቶስ የሰላም ልዑል” የሚለውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ይህ ጥቅስ የዚህን ቃል ትክክለኛ ትርጉም የጦርነት አለመኖር ብቻ ሳይሆን በፍትህ ላይ የተመሠረተ በሰዎች መካከል የሚገኝ ወዳጅነትን ነው” ብለዋል።
“ሰላም በእውነት በልብ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ስጦታ ነው” የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ይህንንም ማስተዋወቅ “የካቶሊክ ተግባር” እጅግ የላቀ ደረጃ እንደሆነ፥ ምክንያቱም የዓለም ቤዛ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች የሚያደርግ ምልክት ነው” ብለዋል።
ሰላምን ለመፍጠር በብርሃነ ልደቱ ትዕይንት ፊት መጸለይ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፥ ወጣቶች በቤቶች፣ በትምህርት ቤቶች እና በቁምስናዎች ውስጥ የተዘጋጁ ልዩ ልዩ የብርሃነ ልደቱ ትዕይንቶችን ሲመለከቱ፣ እኛን ለማዳን ሰው ለሆነው እግዚአብሔር ቦታ እንዳለው ሁሉም ሰው ማየት የሚችል መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።
“‘ለሁሉም ሰው ቦታ አለ’ የሚለው የካቶሊክ ተግባር ወጣቶች ቡድኖች እንደ ጎርጎርሳውያኑ የ2025 ዓ. ም. ጭብጥ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእያንዳንዱ ሰው፣ ለእያንዳንዱ ልጅ፣ ለታዳጊ፣ ለወጣት እና ለአረጋዊ ሰው ቦታ ይሰጣል” ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል።
“የእግዚአብሔር ልጅ ወደ ዓለም ሲመጣ በቤት ውስጥ ቦታ አላገኘም፤ ነገር ግን ሁሉንም ሰው በፍቅር ለመቀበል ልቡን እንደሚከፍት ሁሉ ልባችንንም ያንኳኳል” ብለዋል።
ወደ ቅዱስ ካርሎ አኩቲስ እና ወደ ቅዱስ ፒየር ጆርጂዮ ፍራሳቲ መመልከት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የካቶሊክ ተግባር ማኅበር ወጣቶችን በብርሃነ ልደቱ ትዕይንቶች ፊት ቀርበው ሲጸልዩ ለሁሉም ሰው የእግዚአብሔርን ክብር እና ሰላም የሚያውጁ መላዕክትን እንዲመስሉ አደራ ብለዋል።
“ይህ ሰላም የእያንዳንዱ መልካም ፈቃድ ያለው ሰው እና በተለይም እኛ ክርስቲያኖች መልካም ለመሆን ብቻ ሳይሆን በየቀኑ የተሻለ ለመሆን የተጠራንበት ቁርጠኝነት ነው” ተናግረው፥ የካቶሊክ ተግባር ማኅበር አባል የነበሩትን የቅዱስ ፒየር ጆርጂዮ ፍራሳቲን እና የቅዱስ ካርሎ አኩቲስን ምሳሌ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
“እነርሱን በመምሰል የሰላም አብሳሪነታችህ ብሩህ እንደሚሆን፥ ምክንያቱም ከኢየሱስ ጋር አብራችሁ ስትሆኑ በእውነት ነፃ እና ደስተኛ፥ ለጎረቤቶቻችሁ በተለይም ለተቸገሩት ለመድረስ ዝግጁዎች ትሆናላችሁ” ብለዋል።
