ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ አዲሱ ትውልድ ከሰው ሠራሽ አተውሎት ጋር በተገናኘ ሊታገዝ እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን የሚደረግ እንክብካቤ” በሚል ርዕሥ ዓርብ ኅዳር 26/2018 ዓ. ም. የተካሄደውን ጉባኤ ለተካፈሉት አባላት ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፥ “አዲሱ ትውልድ ወደ ብስለት እና ኃላፊነት በሚጓዝበት መንገድ በተለይም ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ መሰናክል ከመሆን ይልቅ ድጋፍ ማድረግ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በንግግራቸው፥ “ከፍተኛ መጠን ያለው መረጃን የማግኘት ችሎታ ትርጉም ዋጋ ያለው መረጃን ከማግኘት ችሎታ ጋር መምታታት የለበትም” ሲሉ አስረድተው፥ “እነዚህ እውነታዎች ብዙውን ጊዜ በባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሞዴሎች ሲገለሉ ወይም ሲያፌዙባቸው ቢታይም፥ ዋጋ ያለው መረጃን ማግኘት የህልውናችንን ምስጢር እና ዋና ዋና ጥያቄዎችን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ መሆንን ይጠይቃል” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ “የኅብረተሰብ ደህንነት የሚረጋገጠው ወጣቶች ተሰጥኦዎቻቸውን በማዳበር የጊዜውን ጥያቄ እና የሰዎችን ፍላጎቶች በልግስና እና በአእምሮ ነፃነት መመለስ ሲችሉ ነው” ብለዋል።
ጉባኤው የተዘጋጀው የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1991 ዓ. ም. “Centesimus Annus” ወይም “መቶኛ ዓመት” ባሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በሚጠራ ጳጳሳዊ ፋውንዲዴሽን እና ስትራቴጂያዊ የምርምር ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ጥምረት (SACRU) እንደ ሆነ ታውቋል።
ጉባኤው ዓርብ ኅዳር 26/2018 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ የተካሄደው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስ፣ በትምህርት እና በመገናኛ መስኮች ላይ ያለውን ተጽእኖ የሚገመግም ሪፖርት ለማቅረብ እንደሆነ ታውቋል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ልማት የጋራ ጥረት መሆን አለበት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ወጣቶች እውነትን ለመፈለግ እና የውሳኔ አሰጣጥ ልምዳቸውን ለማስፋት እነዚህን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በራሳቸው ብልሃት እንዲጠቀሙ ማስተማር እንደሚገባ አሳስበዋል። “ወጣቶች የተለዩ እና የተሻሉ ለመሆን ያላቸውን ፍላጎት እንደግፋለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ከዚህ በፊት ስለ በሳልነት ጥልቅ አቅጣጫን የመቀየስ አስፈላጊነት ግልጽ ሆኖ አያውቅም” ብለዋል።
ከወጣቶች ጋር የወደፊት ሕይወት ለመገንባት እንደ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ያሉ የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ዕድገት መምራት እና በሰው ልጅ ችሎታ ላይ ያላቸውን እምነት የመመለስ እና የማጠናከር አስፈላጊነትን ገልጸው፥ ይህን ዕድገት የማይቻል አድርጎ መመልከት አስፈላጊ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
“ይህም የፖለቲካ፣ የተቋማት፣ የንግድ ማኅበረሰቦች፣ የፋይናንስ፣ የትምህርት፣ የመገናኛ፣ የዜጎች እና የሃይማኖት ማኅበረሰቦች ቅን ፍላጎትን ያካተተ የተቀናጀ እርምጃን ይጠይቃል” ብለው፥ “ከእነዚህ አካባቢዎች የተውጣጡ ተዋናዮች ይህንን የጋራ ኃላፊነት ተቀብለው በቁርጠኝነትን እንዲፈጽሙት ጥሪ አቅርበው፥ ቁርጠኝነቱ የሚመጣው በጥቂቶች እጅ ውስጥ እየጨመረ ከሚሄደው ከማንኛውም የፓርቲ ጥቅም ወይም ትርፍ በፊት መሆን አለበት” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እነዚህን ግቦች ለማሳካት ሰፊ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በጥብቅ ተናግረው፥ በምርምራቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ በጉባኤው ላይ የተገኙትን አመስግነዋል።
ሰዎች በፍጥረት ሥራ ውስጥ ተባባሪዎች ናቸው
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በኅብረተሰቡ ሕይወት ፈጣን እና ጥልቅ ለውጦችን ማምጣቱን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ እነዚህ ለውጦች በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የሚነኩ መሆናቸውን ገልጸው፥ እንዲሁም የሰውን ልጅ አንዳንድ ገጽታዎች ማለትም ወሳኝ አስተሳሰብ፣ ማስተዋል፣ ትምህርት እና ግለሰባዊ ግንኙነቶች ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን አስረድተዋል።
በዚህ መሠረት የእነዚህን ቴክኖሎጂዎች ተጽእኖ በመገምገም ሊታሰቡ የሚገቡ የተወሰኑ ጥያቄዎች መኖራቸውን ሲገልጹ፥ “የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዕድገት በእርግጥ የጋራ ጥቅምን እንደሚያገለግል እና ሃብትን በጥቂቶች እጅ ብቻ ለማጠራቀም የማይውል መሆኑን እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን?” ብለው፥ “ዛሬ በገበያ ላይ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ሸቀጥ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መስክ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
“በዚህ የታሪክ ወቅት ሰው መሆን ምን ማለት ነው?” በማለት ሁለተኛውን ጥያቄ ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በዚህ አውድ መሠረት “በልጆቻችን እና በወጣቶቻችን ነፃነት እና ውስጣዊ ሕይወት እንዲሁም ቴክኖሎጂ በአእምሯዊና በነርቭ ዕድገት ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ተጽእኖ ቆም ብሎ ማሰላሰል እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል።
“የሰው ልጅ ከቴክኖሎጂ የሚመነጩ ይዘቶች ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን በፍጥረት ሥራ ውስጥ ተባባሪ እንዲሆን የተጠራ ነው” ሲሉ አስረድተው፥ “ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለፈጠራ አዳዲስ አድማሶችን የከፈተ ቢሆንም ነገር ግን የሰው ልጅ ለእውነት እና ለውበት ባለው ዝግጁነት፣ ለአድናቆት እና ለማሰላሰል ባለው አቅም ሊያስከትል የሚችለው ተጽእኖ ከፍተኛ ስጋትን አስነስቷል” ብለዋል።
“የሰው ባሕርይ የሚለይበትን መንገድ ማወቅ እና መጠበቅ ሚዛናዊ ዕድገቱን ማረጋገጥ ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው፥ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ውጤቶችን ለማስተዳደር በቂ ማዕቀፍ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
