ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕትነት ወደ ብርሃን መምጣትን ያስተምረናል ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቀዳሚው ሰማዕት የቅዱስ እስጢፋኖስ ዓመታዊ በዓልን ከመላው ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር ሆነው አክብረዋል። የላቲን ሥርዓትን በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ በብርሃነ ልደቱ ማግሥት ታኅሳስ 17/2018 ዓ. ም. በተከበረው የቀዳሚው ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ ሕይወት ላይ በማስተንተን ቅዱስነታቸው ቃለ-ምዕዳናቸውን አሰምተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ “ሰማዕትነት ማለት በብርሃነ ልደቱ ደስታ በመታገዝ፥ ፍርሃት እና ጦርነት በበዛበት ዓለም ውስጥ ወንድማማችነትን፣ ይቅርታን እና ሰላምን መምረጥ ማለት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ክቡራት እና ክቡራን ተከታታዮቻችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዕለቱን በማስመልከት ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን ውላችኋል! ዛሬ የቅዱስ እስጢፋኖስን ሰማዕትነት የምናስታውስበት ቀን ነው። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አንድ ጊዜ ብቻ ያልተወለዱ መሆናቸውን በእርግጠኝነት ይናገሩ ነበር። ከዚህም በላይ ሰማዕትነትን በእምነት ዓይን በመመልከት ሞትም ቢሆን በጨለማ ውስጥ መኖር ሳይሆን ወደ ብርሃን መምጣት እንደ ሆነ ይገነዘቡታል። ወደ ዓለም መምጣትን አንመርጥም ነገር ግን ብርሃንን እንድንመርጥ የሚጠየቁንን በርካታ ልምዶችን እናልፋለን። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ እንደምናገኘው እስጢፋኖስ ለሰማዕትነት ሲዘጋጅ የተመለከቱት በሙሉ በፊቱ ብርሃን እና በቃሉ መደነቃቸውን ይመሰክራል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ተብሎ የተጻፈውን እናገኛለን፥ ‘በሸንጎም የተቀመጡት ሁሉ ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት’ (የሐዋ. 6፡15)። ይህ ታሪክን በግዴለሽነት የማይመለከት ነገር ግን በፍቅር ምላሽ የሚሰጥ ሰው ፊት ነው። እስጢፋኖስ የሚያደርጋቸው እና የሚናገራቸው በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠውን እና ጨለማችን የሚያበራ መለኮታዊ ፍቅርን ይወክላል።

የተወደዳችሁ ምዕመናን ሆይ! የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን መወለድ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ይጠራናል። ይህንንም የሚያደርገው እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እንደ ቅዱስ ዮሴፍ እና በዚያች ሌሊት በቤተልሔም የምናገኛቸው እረኞች ባሳዩን ትሕትና አማካይነት ነው። ሆኖም ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ውበት እና እርሱን ለመምሰል የሚጥሩ ሰዎች በሙሉ ውድቅ ተደርገዋል። ምክንያቱም ከመጀመሪያው ጀምሮ የልባቸውን በሚገልጥ በጎነት ምክንያት የእርሱ ኃይል ለሥልጣን የሚታገሉትን እና በኢ-ፍትሃዊ ድርጊታቸው የሚታወቁ ሰዎች ምላሽ አስነስቷል (ሉቃስ 2:35)። ሆኖም ግን እስከ ዛሬ ድረስ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ ምንም ኃይል ሊያሸነፈው አልቻለም፥ አይችልምም። በዓለም በየትኛውም ቦታ ከፍተኛ ዋጋ ቢያስከፍልም እንኳ ፍትህን የሚመርጡ፣ ከፍርሃት ይልቅ ሰላምን የሚያስቀድሙ እና ራሳቸውን ከማገልገል ይልቅ ድሆችን የሚያገለግሉ አሉ። በርካታ ዓይነት ፈተናዎች ቢኖሩም ነገር ግን እግዚአብሔር የሰጠን ተስፋ ዘወትር እየለመለመ የሰማዕትነት በዓልን ለማክበር ምክንያታዊ ይሆነናል።

ዛሬ እርግጠኝነት በሌለበት እና ስቃይ በበዛበት ዓለም ውስጥ ደስታን ማግኘት የማይቻል ሊመስል ይችላል። በሰላም በማመን የኢየሱስ ክርስቶስን እና የሰማዕታትን መንገድ የመረጡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ይቀለድባቸዋል። ከሕዝባዊ መድረኮች ይገለላሉ። አልፎ አልፎ ጠላትን ይደግፋሉ በሚል ሰበብ ይከሰሳሉ። ነገር ግን ክርስቲያኖች ጠላቶች የሏቸውም። እርስ በርሳቸው ባይግባቡም እንኳ በዚህ መልክ ይቆያሉ። የብርሃነ ልደቱ ምስጢር በወንድማማችነት የሚኖሩትን፣ በዙሪያቸው የሚገኙ ጠላቶቻቸውንም ጭምር የእግዚአብሔርን ልጆች የማይጠፋ ክብር የሚያውቁ ሰዎች ጽናት በማነሳሳት ደስታን ይሰጠናል። እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጦር መሣሪያ የበለጠ እውነተኛ ኃይል ያለው በመሆኑ ሌሎችን ይቅር ብሎ ሞተ። በሁሉም ልብ ውስጥ አስቀድሞ በሚገኝ የይቅርታ መንፈስ እንደገና በመነሳሳት ለጎረቤታችን ትኩረት እና እውቅናን መስጠት በተለየ መንገድ ልናያቸው እንጀምራለን። እንደገና መወለድ እና እንደገና ወደ ብርሃን መምጣት ማለት ይህ ነው። የእኛ ብርሃነ ልደት ይህ ነው።

ሕይወትን ከሚሰጡ፣ ትዕቢትን ከሚቃወሙ እና ጥርጣሬን በእምነት ከሚያሸንፉት ሴቶች መካከል ወደተባረከች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ እንጸልይ። በረዶ በሙቀት እንደሚቀልጥ ሁሉ ፍርሃትን እና ስጋቶች በደስታዋ የምታስወግድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እኛን ወደ ራሷ ደስታ ትመልሰን።”

 

27 Dec 2025, 16:13