ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ወቅት  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ምዕመናን ለብርሃነ ልደቱ በዓል በትኩረት እንዲዘጋጁ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ረቡዕ ታኅሳስ 8/2018 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ ለተገኙት የልዩ ልዩ አገራት ታዳሚዎች ሰላምታቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ የብርሃነ ልደቱ በዓል ዝግጅት የጸሎት እና የአስተንትኖ መሆኑን እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በድምቀት የተዘጋጀውን የብርሃነ ልደቱ ትዕይንት እና የገና ዛፍ ለመመልከት ለመጡት በርካታ መንፈሳዊ ነጋዲያን ባደረጉት ንግግር፥ እስከ ብርሃነ ልደቱ ድረስ ያሉት ቀናት የኢየሱስን የልደት በዓል ለማክበር ዝግጅት የምናደርግባቸው ቀናት እንደሆኑ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ረቡዕ ታኅሳስ 8/2018 ዓ. ም. ረፋድ ላይ ባቀረቡት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ ለተገኙት የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ምዕመናን ባስተላለፉት የማበረታቻ መልዕክት፥ “እያንዳንዳችሁ ከቤተሰቦቻችሁ ጋር ሆናችሁ የእግዚአብሔር ልጅ እና የዓለም አዳኝ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የምትዘጋጁበት ጊዜ የተባረከ እንዲሆንላችሁ እጸልያለሁ” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በሳምንታዊው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ
ቅዱስነታቸው በሳምንታዊው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ   (@Vatican Media)

የኢየሱስ ልደት ትዕይንቶች አስፈላጊነት

“ለብርሃነ ልደቱ በዓል ጥቂት ቀናት ብቻ በቀሩበት በዚህ ወቅ በቤታችሁ ውስጥ ያዘጋጃችሁት የብርሃነ ልደት ትዕይንት የክርስቶስን የልደት ምስጢር የሚያንፀባርቅ ነው” በማለት ከጣሊያን ለመጡት ምዕመናን ባቀረቡት ሰላምታ ላይ ገልጸዋል።

ቫቲካን ሰኞ ታኅሳስ 6/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እና በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ የሚገኙ የብርሃነ ልደቱ ትዕይንቶችን ለምዕመናን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

“የብርሃነ ልደቱ መንፈሳዊ ትዕይንት ለካቶሊክ እምነት ተከታይ ብቻ ሳይሆን በክርስትና ባሕል እና ሥነ-ጥበብ ውስጥ ሰው በመሆን በመካከላችን ለመሆን የመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያስታውሰን የብርሃነ ልደቱ በዓል አካል ሆኖ እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

በዓሉን በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሳይጠመዱ ማክበር

ብርሃነ ልደቱን ለማክበር አንድ ሳምንት ብቻ እንደቀረ አስታውሰው፥ “ምዕመናን በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሳይጠመዱ በዓሉን በጽሞና እንዲያከብሩት” በማለት ለፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ባቀረቡት ሰላምታ አሳስበዋል።

“ለበዓሉ ዝግጅት ሲባል በሌሎች ነገሮች ላይ መጠመድ የለብንም” በማለት ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፥ይህ በዓሉን በጥልቀት ከማክበር ይልቅ ለብስጭት የሚዳርግ ይሆናል” ሲሉ አስረድተዋል። ብርሃነ ልደቱን ለማክበር ስንዘጋጅ ልባችን ትኩረት እንዲኖረው ጊዜን መስጠቱ እንደሚገባ እና ይህም የኢየሱስ ፍቅራዊ መወለድ የሕይወታችን እና የልባችን ዘላለማዊ ሃብት እንዲሆን ለማድረግ ነው” ብለዋል።

ለጀርመን መንፈሳዊ ነጋዲያን ባቀረቡት ሰላምታም፥ “የብርሃነ ልደቱ ዝግጅት ኢየሱስ ክርስቶስን ያለ ጥርጣሬ በመቀበል ለበዓሉ እንድንዘጋጅ ይጋብዘናል” ብለው፥ “ተስፋችን እርሱ በመሆኑ የልደቱን በዓል በደስታ በመጠባበቅ በልበ ሙሉነት ‘ጌታ ኢየሱስ ሆይ’ ብለን መጸለይ ይገባል” በማለት አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከምዕመናን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከምዕመናን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ   (@Vatican Media)

የአስተንትኖ እና የጸሎት ጊዜ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከፖላንድ ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያንም ጭምር ባቀረቡት ሰላምታ፥  ብርሃነ ልደቱን ለማክበር የሚቀሩን የመጨረሻ ቀናት የአስተንትኖ እና የጸሎት መሆን እንዳለባቸው ተናግረው፥ የኢየሱስን ልደት በሚገባ ለማክበር በንስሐ እና በሱባኤ መዘጋጀት እንደሚገባ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ከፖርቱጋል ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን ባቀረቡት ሰላምታም፥ የብርሃነ ልደቱ ዝግጅት ከማክሰኞ ታኅሳስ 7/2018 ዓ. ም ጀምሮ በሚቀርብ የዘጠኝ ቀናት ጸሎት እንደሆነ በማስታወስ፥ ይህም በማኅበረሰቦቻቸው ዘንድ የከበረ ባሕል ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ይህ የአምልኮ ሥርዓት የሁሉንም ሰው ልብ ለማብራት እና ለብርሃነ ልደቱ ለማዘጋጀት አዲስ ዕድል እንደሚሰጥ ተናግረው፥ የተስፋ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ መንፈሳዊ ቁርጠኝነት አብራችሁ እንድትጓዝ እና ሁልጊዜም እናንተን እና ቤተሰቦቻችሁን እንድትጠብቅ” በማለት ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል።

ለአረብኛ ተናጋሪ ምዕመናንም ባቀረቡት ሰላምታ፥ “ክርስቲያኖች በሙሉ ልባቸውን ለእግዚአብሔር እና ለጎረቤቶቻቸው እንዲከፍቱ፣ በእውነተኛ ሰላም እና ደስታ እንዲሞሉ ተጠርተዋል” ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተዘጋጀውን የብርሃነ ልደቱ ትዕይንት እና የገና ዛፍ  ሲጎበኙ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተዘጋጀውን የብርሃነ ልደቱ ትዕይንት እና የገና ዛፍ ሲጎበኙ   (@Vatican Media)

ቀጣዮቹ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮዎች

ረቡዕ ታኅሳስ 18/2018 ዓ. ም. የብርሃነ ልደቱ በዓል ዋዜማ በመሆኑ ቀጣዩ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደማይኖር ተገልጿል።

ቅዳሜ ታኅሳስ 11/2018 ዓ. ም. ከታዳሚዎች ጋር የኢዮቤልዩ በዓል ከተከበረ በኋላ ረቡዕ ታኅሳስ 22/2018 ዓ. ም. እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር የዓመቱ መጨረሻ ቀን ቅዱስነታቸው የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን የሚያቀርቡ መሆናቸው ተገልጿል።   

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ከ50 ዓመታት በፊት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1975 ዓ. ም. በአዲስ ዓመት ዋዜማ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ማቅረባቸው ይታወሳል።

 

18 Dec 2025, 12:38