ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የልብ ሕክምና ትምህርት የሚከታተሉ ባለሞያዎችን በቫቲካን ሲቀበሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የልብ ሕክምና ትምህርት የሚከታተሉ ባለሞያዎችን በቫቲካን ሲቀበሉ  (@VATICAN MEDIA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ልብን መፈወስ አካላዊም መንፈሳዊም ነው” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የተስፋ ኢዮቤልዩ ዓመት እየተከበረ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ከልብ ሕክምና ሰልጠና ተሳታፊዎች ጋር ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለሐኪሞቹ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ልብን መፈወስ ሳይንሳዊ ጥበብን፣ ርህራሄን እና ሥነ ምግባራዊ ኃላፊነትን የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በፓሪስ የሚሰጥ የልብ ሕክምና ትምህርት በመከታተል ላይ ከሚገኙ የልብ ሐኪሞች ጋር ዓርብ ኅዳር 26/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ተገናኝተዋል።

ቅዱስነታቸው ለሐኪሞቹ ባደረጉት ንግግር፥ የልብ ሕክምና ሳይንስን እና ልምምድን ለማሳደግ ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ሥራቸው በሳይንስ፣ በርኅራሄ እና በሥነ-ምግባራዊ ኃላፊነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

ነፍሳትን ማገልገል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በንግግራቸው፥ “እያንዳንዱ የሕክምና ተግባር ሙሉ ትርጉሙን የሚያገኘው በሕይወት አገልግሎት ላይ ሲመሠረት ነው” ብለው፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጋቢት 1995 ዓ. ም. ይፋ ያደረጉትን “የሕይወት ወንጌል” የተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክት በመጥቀስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕሙማን ያለው ርህራሄ የሕክምና ባለሙያዎች ሕሙማንን እንዲንከባከቡ በሚያነሳሳ ሞዴል እንደሆነ ጠቁመዋል።

“ልብን የመፈወስ ተልዕኮ አካላዊም ሆነ ምሳሌያዊ ገጽታ አለው” ብለው፥ ሐኪሞቹ ልብን ለመፈወስ እንደሚፈልጉ ተናግረው፥ እያንዳንዱ የልብ ምት የሕይወት ስጦታ ዘወትር ሊከበር የሚገባው ምስጢር የሚያስታውስ መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመቀጠልም፥ የሕክምና ቡድኑ በዘርፉ ያለውን ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲያጠናክር አበረታትተው፥ እውቀትን በልግስና የመጋራት አስፈላጊነት በማስታወስ፥ የልብ ሕክምናን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ ሕክምናዎች ለጥቂቶች ብቻ እንዳይሆኑ፣ በልብ እና በደም ሥር ሕክምና ላይ የታዩት ዕድገቶች በተለይ ለድሆች እና ለተገለሉ ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሥራቸው በረከት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ጥረታቸውን የነፍስ እና የአካል ሐኪም ለሆነው ለኢየሱስ ቅዱስ ልብ በአደራ ሰጥተው በመጨረሻም የድርጅታቸው ሳይንሳዊ ዕድገት ለሰው ልጅ አገልግሎት ካለው እውነተኛ ቁርጠኝነት ጋር መሆንን እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ “ድፍረትን የሚጠይቅ ሥራቸው ጽናትን እና ደስታን እንዲሰጣቸው” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

 

06 Dec 2025, 15:55