ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ቁማር የቤተሰብን ሕይወት እያፈረሰ እንደሚገኝ አስታወቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“የሥነ-ሕዝብ ቀውስ፣ የቤተሰቦች እና የወጣቶች የኑሮ አለመመቻቸት፣ የአረጋውያን ከማኅበራዊ ሕይወት መገለል፣ የተደፈነ የድሆች ጩኸት፣ የአካባቢ ብክለት እና ማኅበራዊ ግጭቶች በመላው የጣሊያን ከተሞች ውስጥ ከሚታዩ ትላልቅ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሰኞ ታኅሳስ 20/2018 ዓ. ም. የጣሊያን ማዘጋጃ ቤቶች ብሔራዊ ማኅበር አባላትን በቫቲካን ተቀብለው ባደረጉት ንግግር፥ ነዋሪዎችን የሚያጋጥሙ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በቅድሚያ የአቅመ ደካሞችን እና የድሃ ቤተሰቦች ችግሮችን ማወቅ እንደሚገባ አሳስበው፥ አለበለዚያ “ዲሞክራሲ” የሚል ቃል ስም ብቻ ሆኖ እንደሚቀር አስረድተዋል።
የቁማር ጨዋታ መበራከት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ቀጥለውም፥ በተለይም የበርካታ ቤተሰቦች ሕይወት ላወደመው የቁማር መቅሰፍት ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባ ተናግረዋል።
“በቁጥር መግለጫዎች መሠረት በቅርብ ዓመታት ውስጥ በጣሊያን ቁማር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “በትምህርት ዘርፍ፣ በአእምሮ ጤና እና በማኅበራዊ ደኅንነት ላይ ከባድ ችግሮችን እያስከተለ ይገኛል” ሲል ካሪታስ የበጎ አድራጎት ድርጅት በቅርቡ ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሰዋል።
“ጉዳዩ ብቸኝነትን ወይም ከማኅበረሰብ መገለልን የሚገልጽ ነው” ሲሉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥የመንግሥት ባለስልጣናት በዜጎች መካከል እውነተኛ ሰብዓዊ ግንኙነትን በማስተዋወቅ እና በማሳደግ ችግሩን እንዲያስቀሩት ጥሪ አቅርበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በጣሊያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ማኅበራዊ ተሟጋች የነበሩትን አባ ፕሪሞ ማዞላሪን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ “የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን፣ መኖሪያ ቤቶችን፣ የንጹህ ውሃ መስመሮችን እና መንገዶች መገንባት ብቻ ሳይሆን ነገር ግን የመተዛዘን፣ የኑሮ፣ የአመለካከት እና የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት መንገዶችን ማመቻቸት ያስፈልጋል” ብለዋል።
ብርሃነ ልደቱ እና እውነተኛ ኃይል
የላቲን ሥርዓት በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ እሑድ ታኅሳስ 19/2018 ዓ. ም. የተከበረውን የቅድስት ቤተሰብ ዓመታዊ በዓል ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ይህ በዓል ንጉሥ ሄሮድስ ሕፃኑን ኢየሱስን ለመግደል ሲል ትናንሽ ሕጻናትን መጨፍጨፉን ቤተ ክርስቲያን የምታስታውስበት እንደሆነ አስረድተዋል።
“ይህ እልቂት የሰው ሕይወት ክብር ችላ የተባለበት እና የፍቅርን ውበት የማያውቅ የኢ-ሰብዓዊ ኃይል መገለጫ ነው” ሲሉ ተናግረው፥ “የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ግን የትክክለኛ ሥልጣን ገጽታን ከሁሉም በላይ ኃላፊነትን እና አገልግሎትን የሚያሳይ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
