ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በገና በዓል በዓለም ዙሪያ ለ24 ሰዓታት ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
“ለሁሉም በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ይህንን ጥሪ በድጋሚ አቀርባለሁ፡ ቢያንስ በአዳኙን ልደት በዓል ላይ አንድ የሰላም ቀን እንዲኖር እባካችሁን ለዚህ የሰላም ጥሪዬን አቀርባለሁ" ይህ የገና በዓላትን በተመለከተ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ማክሰኞ፣ ታህሳስ 14/2018 ዓ.ም ከካስቴል ጋንዶልፎ ያቀረቡት ጥሪ ነበር።
በመላው ዓለም የሰላም ቀን
አሁን እንደተለመደው፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ ጋዜጠኞችን ለጥያቄዎቻቸው ለመመለስ ቆም ብለው ነበር። መካከለኛው ምስራቅ እና ዩክሬን ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል ውስጥ ይጠቀሳሉ። በቅርብ ሰዓታት ውስጥ በሩሲያ የተከናወኑ ከፍተኛ ጥቃቶች በርካታ ክልሎችን ስለመቱባት ዩክሬን ሲናገሩ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ “በእርግጥ በእነዚህ ቀናት ከፍተኛ ሀዘን የሚፈጥሩብኝ ነገሮች ሩሲያ የገና ስምምነት ጥያቄውን ውድቅ ማድረጓ ነው” ብለዋል። ስለዚህ የሮም ጳጳስ በገና በዓል ላይ ውጊያውን ለአፍታ እንዲቆም ያቀረቡትን ጥሪ አድሰዋል፡- “ምናልባት እኛን ያዳምጡናል፣ እናም በዓለም ዙሪያ አንድ ሙሉ የሰላም ቀን ይኖራል” ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የሰላም ስምምነት ወደፊት እንዲራመድ
ወደ ሌላ የጦርነት ትዕይንት፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ የተኩስ አቁም ሁለተኛ ምዕራፍ ውይይት እየተደረገበት ወዳለበት ቅዱስነታቸው ሐሳባቸውን ሲያዞሩ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቅርብ ቀናት በጋዛ ባደረጉት “ውብ ጉብኝት” የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ካርዲናል ፒርባቲስታ ፒዛባላ አስታውሰዋል። “ከአንድ ሰዓት በፊት፣ በጋዛ ከተማ በሚገኘው የቅድስት ቤተሰብ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ እረኛ ከሆኑት ከአባ ገብርኤል ሮማኔሊ ጋር ተገናኝቼ ነበር። “በዓሉን በጣም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለማክበር እየሞከሩ ነው።” ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አክለውም “የሰላም ስምምነቱ ወደፊት እንደሚሄድ ተስፋ እናድርግ” ሲሉ ተናግረዋል።
በኢሊኖይስ በጸደቀው ራስን የማጥፋት ሕግ ተስፋ መቁረጥ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ትኩረታቸውን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በማዞር፣ በቅርቡ በኢሊኖይስ ግዛት ውስጥ በማይድን በሽታ የተያዙ ጎልማሶች ራስን የማጥፋት እርዳታ የሚፈቅድ ሕግ እ.አ.አ ከመስከረም 2026 ዓ.ም እንደሚጸድቅ ያላቸውን ትንበያ እና አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ባለፈው ህዳር ወር በቫቲካን በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከግዛቷ ገዥ ጄቢ ፕሪትዝከር ጋር ጉዳዩን “በግልጽ” እንዳነሱ አስረድተዋል፡- “በዚያን ጊዜ ሕጉ ቀድሞውኑ በጠረጴዛቸው ላይ ነበር” ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።
“ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የሕይወትን ቅድስና ማክበር አስፈላጊ መሆኑን በጣም ግልጽ ነበር። እናም በሚያሳዝን ሁኔታ... ያንን ረቂቅ ሕግ ለመፈረም ወስኗል። በዚህ በጣም አዝኛለሁ” ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ።
ከዚያም በተለይ በዚህ የገና ወቅት፣ “የሰውን ሕይወት ተፈጥሮ፣ የሰው ሕይወትን ዋጋ እንዲያስቡበት” ጋብዘዋል። እግዚአብሔር የሰው ሕይወት መኖር ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ለማሳየት እንደኛ ሰው ሆነ።” የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተስፋ እና ጸሎት “ለሕይወት አክብሮት በሰው ልጅ ሕልውና በእያንዳንዱ ቅጽበት፣ ከተፀነሰበት እስከ ተፈጥሯዊ ሞት ድረስ እንደገና ሊያድግ ይችላል” የሚል ነው።
