ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል በማቅረብ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል በማቅረብ ላይ  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ፍትሃዊ ያልሆነ ሃብት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሕይወት ዋጋ ነው” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋችን ነው!” የሚለውን የኢዮቤልዩ ዓመት መሪ ሃሳብ መሠረት በማድረግ ያዘጋጁትን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል አቅርበዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ረቡዕ ታኅሳስ 8/2018 ዓ. ም. ለተሰበሰቡት ታዳሚዎቻቸው ባቀረቡት አስተምህሮ፥ “ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ክምችት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሕይወት ዋጋ ነው” ሲሉ ተናግረው፥ “ልባችን እውነተኛ ዕረፍት የሚያገኘው በእግዚአብሔር ብቻ እንጂ ሁልጊዜ እርካታን በማይሰጥ ዕለታዊ ሩጫ አይደለም” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ክቡራት ክቡራን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን የዕለቱን አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን፥ አስተንትኖ ያደረጉበትን የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ እናነብላችኋለን፥

“ብልና ዝገት በሚያጠፉት፥ ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁበት በምድር ላይ ሃብት አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብል እና ዝገት በማያጠፉት፥ ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁበት በሰማይ ሃብት ሰብስቡ፤ ሃብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናልና” (ማቴ. 6:19-21)።

ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ሙሉ ትርጉሙን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ውድ ወንድሞችና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ! እንኳን ደህና መጣችሁ! የሰው ልጅ ሕይወት ዘወትር አንድ ነገር እንዲከናውን እና እንዲፈጽም በሚያነሳሳ የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኑ ይታወቃል። በአሁኑ ጊዜ በልዩ ልዩ ዘርፎች ጥሩ ውጤቶችን ለማግኘት ፈጣን መሆን ያስፈልጋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በዚህ የተሞክሮአችን ገጽታ ላይ ብርሃን ሊፈነጥቅ የሚችለው እንዴት ነው? በሞት ላይ ባመጣው ድል ስንሳተፍ እናርፋለን? እምነታችንም ይህን ይነግረናል፤ አዎ! እናርፋለን። እንቅስቃሴ አልባ አንሆንም። ወደ እግዚአብሔር ዕረፍትም እንገባለን። ይህም እርሱ የሚሰጠን ሰላም እና ደስታ ነው። ታዲያ ዝም ብለን መጠበቅ አለብን ወይስ ይህ ዛሬውኑ ሊለውጠን ይችላል?

ሁልጊዜ እርካታን በማይሰጡን ብዙ ተግባራት እንያዛለን። ብዙ ድርጊቶቻችን ተግባራዊ ከሆኑ ተጨባጭ ነገሮች ጋር የተገናኙ ናቸው። ለብዙ ቃል ኪዳኖች ኃላፊነት መውሰድ፣ ችግሮችን መፍታት እና መጋፈጥ አለብን። ኢየሱስ ክርስቶስም ከሰዎች በመገናኘት በዕለታዊ ሕይወት ውስጥ ተሳትፏል። ሳይቆጥብ ይልቁንም እስከ መጨረሻው ድረስ ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል። ሆኖም ይህ ሩጫችን ብዙ ጊዜ እርካታን ከመስጠት ይልቅ ከመጠን በላይ መሥራትን፣ እርጋታን የሚያሳጣ እና በሕይወታችን ውስጥ በእውነት አስፈላጊ የሆነውን ነገር በሙላት እንዳንኖር የሚያግደን እንደሆነ እናስተውላለን። ከዚያም ድካም እና እርካታ ማጣት ይሰማናል። ሆኖም ግን የሕይወታችንን የመጨረሻ ትርጉም የማይወስኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ነገሮች ላይ ጊዜ የምናባክን ይመስላል። አንዳንድ ጊዜ ከሩጫ በኋላ ባዶነት ይሰማናል። ለምን ቢባል ምክንያቱም እኛ ማሽኖች ሳንሆን ልብ ያለን ሰዎች ነን። በእርግጥ እኛ ራሳችን ልብ ነን ማለት እንችላለን።

ልብ የአስተሳሰባችን፣ የስሜታችን እና የፍላጎታችን ድምር፣ የማይታይ የሰው ልጅ ሁሉ ምልክት እና ማዕከል ነው። ወንጌላዊው ማቴዎስ የኢየሱስን አስደናቂ ንግግር በመጥቀስ የልብን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ ይጋብዘናል፥ ‘ሃብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናል’ (ማቴ 6፡21)።

ስለዚህ እውነተኛ ሃብት የሚቀመጠው አስተማማኝ ነው በምንለው ባንክ ውስጥ ሳይሆን ወይም በትላልቅ የፋይናንስ ኢንቨስትመንቶች ውስጥ ሳይሆን ልብ ውስጥ ነው። እነዚህ ምድራዊ ሥፍራዎች ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ እና ያለአግባብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሰው ልጆች ሕይወት ደም የሚያፈሱ እና የእግዚአብሔርን ፍጥረት በማውደም ላይ ያተኮሩ ናቸው።

በእነዚህ ገጽታዎች ላይ ማሰላሰል አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ያለማቋረጥ በሚያጋጥሙን በርካታ ግዴታዎች ውስጥ አንዳንድ ጊዜ በተሳካላቸው ሰዎችም ጭምር ተስፋ መቁረጥ እና ትርጉም የለሽ የመሆን አደጋ እየጨመረ ይገኛል። በምትኩ ሕይወትን በትንሳኤው ብርሃን መተርጎም፣ ከሞት ከተነሳው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመመልከት ሰብዓዊ ማንነትን በልባችን ውስጥ ማግኘት ማለት ነው (cor inquietum)። በዚህ “እረፍት የለሽ” ከሚለው ቅጽል ጋር ቅዱስ አጎስጢኖስ የሰው ልጅ ለተሟላ ሕይወት ያለውን ናፍቆት እንድንረዳ ያግዘናል። ሙሉ ዓረፍተ ነገር የሚያመለክተው የንስሐ መጀመሪያን ሲሆን፥ ቅዱስ አጎስጢኖስም ‘ጌታ ሆይ! አንተ እኛን ለራስህ ፈጠርከን፤ ልባችንም በአንተ እስኪያርፍ ድረስ ዕረፍት የለውም’ ሲል ጽፏል (1:1)።

እረፍት ማጣት ማለት ልባችን በአጋጣሚ፣ ዓላማ ወይም መድረሻ በሌለው የተዛባ መንገድ ላይ መንቀሳቀሱን የሚያሳይ ነው። ነገር ግን መድረሻው ‘ወደ ቤት በመመለስ’ ላይ ያነጣጠረ ነው። የልብ ትክክለኛ አቀራረብ የዚህን ዓለም ሃብት መያዝን የሚያካትት ቢሆንም ሁሉን ነገር ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ነው። ይህም የእግዚአብሔርን ፍቅር ወይም ፍቅር የሆነውን እግዚአብሔርን ማግኘት ነው። ይህ ሃብት ሊገኝ የሚችለው መንገድ ላይ የምናገኛቸውን ጎረቤቶቻችንን ስንወድ ብቻ ነው። ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ስንወድ፣ የእነርሱ መኖር ልባችንን የሚቀሰቅስ እና ራሳችንን ከፍተን እንድሰጣቸው የሚጠይቅ ነው። ጎረቤቶቻችን ተረጋግተን እንድንመለከታቸው፥ አንዳንድ ጊዜም እቅዶቻችንን እና አቅጣጫችንን እንድንቀይር ይጠይቁናል።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! የሰው ልብ እንቅስቃሴ ምስጢር ይኸው ነው። ወደ ሕልውናው ምንጭ በመመለስ ፈጽሞ በማያልቅ እና በማያሳዝን ደስታ መደሰት ነው። ማንም ሰው ከእውነታው በላይ ያለ ትርጉም መሄድ ወይም ከሚያልፍ ነገር በላይ ሊኖር አይችልም። የሰው ልብ ያለ ተስፋ ሊኖር አይችልም። የሚኖረውም የሚፈልገውን ሁሉ ለማግኘት ሳይሆን ነገር ግን ለሙሉነት መፈጠሩን ሳያውቅ መኖር አይችልም።

ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋው፣ በሕማማቱ፣ በሞቱ እና በትንሣኤው ለዚህ ​​ተስፋ ጠንካራ መሠረት ጥሎልናል። እረፍት የሌለው ልብ ወደተፈጠረለት ፍቅር ውስጥ ከገባ ሊበሳጭ አይችልም። መድረሻውንም በሚገባ ያውቃል። ሕይወትም አሸናፊ ትሆናለች። በኢየሱስ ክርስቶስ ድጋፍ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ እያንዳንዱን የሞት ፈተናን ድል ማድረግን ይቀጥላል። የክርስቲያን ተስፋ ይህ ነው። ይህን ተስፋ የሰጠንን እግዚአብሔር አምላካችንን ዘወትር እንባርከው እናመስግነውም!”

 

17 Dec 2025, 13:59