ፈልግ

Pope Leo XIV� Angelus prayer on St. Stephen's Day in Vatican

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ምዕመናን ለሰላም እና በጦርነት ለሚሰቃዩ ቤተሰቦች እንዲጸልዩ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የላቲን ሥርዓት በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ እሑድ ታኅሳስ 19/2018 ዓ. ም. የተከበረውን የቅድስት ቤተሰብ ዓመታዊ በዓል በማስመልከት ቃለ-ምዕዳን አሰምተዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት በርካታ ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ያደረሱ ሲሆን፥ በዕለቱ የተከበረውን የቅድስት ቤተሰብ በዓል በማስታወስ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ በብቸኝነት፣ በተስፋ መቁረጥ፣ በመለያየት እና በግጭቶች ውስጥ በሚገኝ ማኅበረሰብ ውስጥ ቤተሰቦች ብርሃን ሊሆኑ እንደሚችሉ በማስገንዘብ፥ ለሰላም እና በጦርነት ለሚሰቃዩ ቤተሰቦች ጸሎት እንዲያቀረቡ ምዕመናንን አሳስበዋል።

ክቡራት እና ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዕለቱን በማስመልከት ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! ዛሬ የቅድስት ቤተሰብን በዓል እናከብራለን። በዕለቱ የምናቀርበው መስዋዕተ ቅዳሴም ከማቴ 2:13-15 እና 19-23 ተወስዶ የተነበበውም ኢየሱስ፣ ማርያም እና ዮሴፍ ወደ ግብፅ የመሸሻቸውን ታሪክ ይነግረናል። ይህ ለኢየሱስ፣ ለማርያም እና ለዮሴፍ የፈተና ጊዜ ነበር። በእርግጥም፣ ብሩህ የሆነው የብርሃነ ልደቱ የደስታ ጊዜ በድንገት በሄሮድስ አስጨናቂ ሕይወት ስጋት የተነሳ በሚረብሽ ጥላ ሊጋረድ የተቃረበ ይመስል ነበር። ንጉሥ ሄሮድስ ጨካኝ እና ደም የጠማው እና በጭካኔው የሚፈራ ሰው ነው። በዚህም ምክንያት ከስልጣን የመውረድ ፍርሃትም አለበት።

‘የአይሁድ ንጉሥ’ መወለዱን ከሰብአ ሰገል በሰማ ጊዜ ሥልጣኑ ስጋት ውስጥ እንደወደቀ ስለተሰማው፣ ከኢየሱስ ጋር ተመሳሳይ ዕድሜ ያላቸው ሕጻናት በሙሉ እንዲገደሉ አዘዘ (ማቴ 2፡2)። በዚህ ውስጥ ሁሉም ጥንታዊ የመዳን ተስፋዎች ሲፈጸሙ በመንግሥቱ ውስጥ እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ ትልቁን ተዓምር እያደረገ ነበር። ነገር ግን ሄሮድስ ይህንን ማየት አልቻለም። ምክንያቱም ዙፋኑን፣ ሃብቱን እና መብቱን የማጣት ፍርሃት አሳውሮት ስለ ነበር ነው። አንዳንድ እረኞች በቤተልሔም ውስጥ ብርሃን እና ደስታ መሆኑን በሰሙ ጊዜ ወደ ቤተልሔም መጥተው ሕጻኑ ኢየሱስ በተወለደበት ግርግም ፊት ቀርበው እግዚአብሔርን አመሰገኑ (የሉቃ. 2:8-20)። ነገር ግን በታወረ ዓመፅ እና በስጋት የተዛባ ድምፅ ካልሆነ በስተቀር ከእነዚህ ውስጥ አንዳቸውም የታጠቀ መከላከያን ዘልቀው ወደ ንጉሣዊው ቤተ መንግሥት ሊገቡ አይችሉም።

ይሁን እንጂ የቅዱስ ቤተሰብን መገኘት እና ተልዕኮ ዋጋ የበለጠ የሚያጎላው ይህ የልብ ጥንካሬ ነው። በአምባገነነት በሚታወቅ ጨካኝ እና ስግብግብ ዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር ብቸኛ የመዳን መልስ የተገኘበት ቦታ ነው። እግዚአብሔር ያለ ምክንያት፣ ያለ ገደብና ያለማስመሰል ሙሉ በሙሉ ራሱን ለሰዎች ይሰጣል። ዮሴፍ ማርያምን እና ሕጻኑ ኢየሱስን ደኅንነቱ ወደተጠበቀ ቦታ እንዲወስዳቸው ከእግዚአብሔር ለተሰጠው ትዕዛዝ የመታዘዙ ምልክት በሁሉም ዘንድ ያለውን የመዋጀት ጠቀሜታን ይገለጣል። በግብፅ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ እንደሚገኝ ለመግልጽ በአደራ የሰጠው የፍቅር ነበልባል አድጎ ብርሃንን ለማምጣት ጥንካሬ ያገኛል።

ይህንን ምስጢር በአድናቆት እና በምስጋና ስናሰላስል፥ ቤተሰቦቻችን በምንኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሊያመጡት የሚችሉትን ብርሃን እናስባለን። ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ዓለማችን ዘወትር እንደ ሄሮድስ ያሚያስጨንቋት አስተዳደሮች  አሉ። ይህም በማንኛውም ዋጋ፣ የስኬት አፈ ታሪኮች፣ ሕገ-ወጥ ኃይል፣ ባዶ እና የሐሰት ደህንነት ብዙውን ጊዜ የብቸኝነት፣ ተስፋ የመቁረጥ፣ የመለያየት እና የግጭቶች ዋጋን ያስከፍላል። እነዚህ አስደንጋጭ ክስተቶች በክርስቲያን ቤተሰቦች ውስጥ ያለውን የፍቅር ነበልባልን እንዲያጠፉ መፍቀድ የለብንም። በተቃራኒው በቤተሰባችን ውስጥ የወንጌልን እሴቶች ከፍ አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል። ጸሎት፣ ቅዱሳት ምስጢራትን አዘውትረን መቀበል፥ በተለይም ንስሐ መግባት እና ቅዱስ ቁርባንን መቀበል፣ ጤናማ ፍቅር፣ ቅን ውይይት፣ ታማኝነት እና የዕለት ተዕለት ንግግራችን እና ምልክቶቻችን መልካም፣ ውብ እና ተጨባጭ ሊሆኑ ይገባል። ይህ ለምንኖርባቸው ቦታዎች የተስፋ ብርሃን እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ፍቅርን የምንማርበት እና የእግዚአብሔር የመዳን መሣሪያ ያደርጋቸዋል (ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለ10ኛው የዓለም ቤተሰቦች ጉባኤ ያቀረቡት ስብከት፤ ሰኔ 25/2022 እ.አ.አ)።

ስለዚህ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና በቅዱስ ዮሴፍ አማላጅነት በሰማይ ያለው አባታችን እግዚአብሔር ቤተሰቦቻችንን እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቤተሰቦቻችን በሙሉ እንዲባርክ እንጸልይ። የእርሱ መገኘት እና ማለቂያ የሌለው ፍቅሩ ለሁሉም ሰው ውጤታማ ምልክት ይሆን ዘንድ የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ እንከተል።”

29 Dec 2025, 16:00