ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ አንድነትን እንዲመሰክሩ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ተልዕኮ እና ኅብረት የሚሉ ሁለት ጭብጦችን መሠረት በማድረግ ከቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈቶች ቤቶች ሠራተኞች ጋር በተለዋወጡት የብርሃነ ልደቱ የመልካም ምኞት ንግግራቸው፥ ተልዕኮዋቸው የከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈቶች መደበኛ አስተዳደርን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን፥ በዓለም ዙሪያ ወደሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት፣ ጽሕፈት ቤቶች እና አገልግሎቶች በመድረስ ሥራቸውን ይበልጥ በማስፋት ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ ተግዳሮቶችን ለመጋፈጥ በሚያደርጉት ጥረት እንዲተባበሩ አሳስበዋል።
ከእነዚህ ተቋማት ጋር መተባበር ማለት እንደ እምነት፣ የአምልኮ ሥርዓት እና ሥነ-ምግባር ባሉ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ ግትርነቶችን ወይም ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰቦችን በማስወገድ፣ እውነተኛ ግንኙነቶችን በማዳበር እና ብዙውን ጊዜ በአውታረ መረብ እና በፖለቲካ ምክንያት ስብራትን፣ ክፍፍልን እና ጠበኛነትን በማስፋፋት በሚታወቅ ዓለም ውስጥ የሰላም ትንቢታዊ ምልክቶች እንዲሆኑ አሳስበዋል።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ማስታወስ
የብጹዓን ካርዲናሎች ጉባኤ ሰብሳቢ የሆኑት ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሬ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ባቀረቡት የሰላምታ ንግግራቸው ተወዳጅ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አስታውሰዋል። ብጹዕነታቸው በንግግራቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትንቢታዊ ድምጻቸው፣ በሐዋርያዊ የአገልግሎት ዘይቤአቸው እና በጥልቅ አስተምህሮአቸው በቅርብ ዓመታት ውስጥ የቤተ ክርስቲያኗን መንገድ አጉልተው ማሳየታቸውን ገልጸው፥ “የእግዚአብሔርን ምሕረት ዋና ማዕከል እንድናደርግ፣ ለወንጌል አገልግሎት አዲስ እና ልዩ ትኩረትን እንድንሰጥ እና ደስተኞች በመሆን ሁሉን ሰው በደስታ ለመቀበል እና ለድሆች ትኩረት እንድንሰጥ አበረታትተውናል” ብለዋል።
“የወንጌል ደስታ” የሚለውን ሐዋርያዊ ምክር በመጥቀስ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕይወት የሆኑ ሁለት መሠረታዊ ገጽታዎች ማለትም ተልዕኮን እና ኅብረትን የከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞችን አስታውሰዋል።
የቤተ ክርስቲያኒቱ ሚስዮናዊነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ “ቤተ ክርስቲያን በተፈጥሮዋ ከራሷ ወጥታ ወደ ሌሎች የምትመለከት፣ ፊቷን ወደ ዓለም የምታዞር ሚስዮናዊት ናት” ሲሉ አረጋግጠው፥ ይህም እግዚአብሔር ራሱ አስቀድሞ ወደ እኛ መምጣቱን እና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እኛን ለፈልገን የመጣበትን እውነታ የሚገልጽ ነው” ብለዋል። “የመጀመሪያው ትልቁ ፍለጋ የእግዚአብሔር ነው” ብለው፥ እግዚአብሔር ከራሱ ወጥቶ እኛን ሊያገኘን እንደመጣ እና የብርሃነ ልደቱ ምስጢር ይህን በትክክል እንደሚገልጽ እና የወልድ ወደ ዓለም መምጣትም ይህን ተልዕኮ ያካትታል” ብለዋል።
ይህ ተልዕኮ ለእምነት ጉዞ፣ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች እና ለቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች አገልግሎቶች የማሰላሰያ መስፈርት ይሆናል” ሲሉ አፅንዖት የሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ መዋቅሮች የወንጌልን መስፋፋት የሚያደናቀፉ ወይም የሚያዘገዩ መሆን እንደሌለባቸው፥ “በምትኩ ይበልጥ ተልዕኮ ተኮር ማድረግ አለብን” ብለው፥ ይህ መንፈስ ቤተ ክርስቲያናትን እና ሐዋርያዊ እረኞቻቸውን ለማበረታታት ያለመ የአምልኮ ሥራን የሚያነቃቃ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች በዛሬው ዋና ዋና የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ ተግዳሮቶች አንፃር የተቋቋሙ ተቋማት፣ ጽሕፈት ቤቶች እና ተግባራት አስተዳደርን የሚያረጋገጥ ብቻ ሳይሆን የበለጠ ሚስዮናዊ ሊሆኑ ይገባል” ብለዋል።
የመከፋፈል ገጽታዎች
“የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ከኅብረት ጋር በቅርበት የተቆራኘ ነው” ሲሉ አፅንዖት የሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “በጋራ ፍቅር እና አንድነት ላይ የተመሠረተ ምክር ቤትን መመሥረት በውስጥም ሆነ በውጭ እጅግ አስቸኳይ ተግባር ነው” ሲሉ ገልጸዋል። በውስጣዊ መልኩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው የኅብረት ፈተና ዘወትር መለወጥን የሚጠይቅ ሆኖ ይቀጥላል” ብለዋል።
“አንዳንድ ጊዜ ግልጽ ጸጥታ እና የመከፋፈል ስሜት ሊታይ ይችላሉ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በሁለት ተቃራኒ ጽንፎች መካከል የመገኘት ፈተና ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን” ብለው፥ “ለልዩነቶች ዋጋ መስጠት አለመቻል አንድነትን ወይም ኅብረትን ከመፈለግ ይልቅ ልዩነቶችን እና አመለካከቶችን ሊያባብስ ይችላል” ብለዋል።
ልዩነቶች ቢኖሩም ዘወትር አንድ ነን
“በግለሰባዊ ግንኙነቶች እና ውስጣዊ ሥራዎች ወይም የእምነት፣ የአምልኮ ሥርዓት፣ የሥነ-ምግባር እና ሌሎችንም ጥያቄዎች በመፍታት ረገድ በተከሰቱት ግጭቶች ምክንያት በግትርነት ወይም በርዕዮተ ዓለም የመውደቅ አደጋ አለ” በማለት ያስጠነቀቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ሆኖም ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነት ሥልጣናቸው የመረጡትን መሪ ቃል በመጥቀስ “እኛ ብዙዎች እና የተለያየን ብንሆንም ዘወትር ወንድማማቾች እና እህትማማቾች ነን” ብለዋል።
ስለዚህ ለቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ባቀረቡት ግብዣ፥ “ሁሉም በሲኖዳላዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአንድ ተልዕኮ በሚተባበሩበት ወቅት እያንዳንዱ እንደየጥሪው ሚናውን የሚወጣበትን ኅብረት መገንባት እንደሚገባ በማሳሰብ፥ ይህ ኅብረት የሚገነባው በቃላት እና በሠነዶች ሳይሆን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ መታየት በሚገባቸው ተጨባጭ ምልክቶች፣ አመለካከቶች እና ሥራችንም ጭምር መሆን አለበት” ብለዋል።
“በቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ለብዙ ዓመታት ካገለገልን በኋላ አልፍ አልፎ ከስልጣን አጠቃቀም፣ ከመርታት ፍላጎት ወይም የግል ፍላጎቶችን ከማሳደድ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ምሬቶችን ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎች ለመለወጥ አዝጋሚዎች መሆናችን ብስጭትን ሊያስከትል እንደሚችል እንመለከታለን” ብለው፥ ከዚያም በቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ወዳጅነትን ወይም እውነተኛ የወንድማማችነት ግንኙነቶችን መፍጠር ይቻላል ወይ? ብለን እራሳችንን እንጠይቃለን” ብለዋል።
የሰላም ትንቢታዊ ምልክት መሆን
“በዕለት ተዕለት ድካም ውስጥ ማንም የማይገለልበት፣ እውነተኛ ድጋፍ የሚቀርብበት እና የእያንዳንዱ ሰው ማንነት እና ብቃት የሚከበርበት፣ ቂም እና እርካታ ቢስነት የሌለበት ታማኝ ጓደኞችን ማግኘት ጸጋ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች አባላትን የሚጠይቁት የግል መለወጥን እንደሆነ፥ ስለዚህ በአለመግባባት፣ በዓመፅ እና በግጭት በተጎዳ ዓለም ውስጥ ብዙውን ጊዜ በአውታረ መረብ እና በፖለቲካ ጥቅም ምክንያት የጥቃት እና የቁጣ መስፋፋት በሚታይበት ወቅት የሰላም ምልክቶች እንዲሆኑ እንደሆነ ተገልጿል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመልዕክታቸው፥ "የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሰላም ስጦታን የሚያመጣ እና እጅግ በተበታተነ የሰው እና የባሕል አውድ ውስጥ የትንቢት ምልክት እንድንሆን ይጋብዘናል” ሲሉ አሳስበዋል።
የራስን "እርሻ" ብቻ አለመመልከት
የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች እና አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ተግባር በዚህ ሰፊ አድማስ ውስጥ መካተት አለበት” ሲሉ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “እኛ የራሳችንን እርሻ የምንጠብቅ አትክልተኞች ብቻ ሳንሆን በኢየሱስ ክርስቶስ የተጠራን የእግዚአብሔር መንግሥት ደቀ መዛሙርት እና ምስክሮች ነን” ብለው፥ “በተለያዩ ሕዝቦች፣ ሃይማኖቶች እና ባሕሎች መካከል የወንድማማችነት እርሾ እንድንሆን ተጠርተናል” ሲሉ አስረድው፥ “ይህ ሊሆን የሚችለው እኛ ራሳችን እንደ ወንድማማቾች እና እህትማማቾች ሆነን የኅብረት ብርሃን በዓለም ላይ እንዲበራ ስንፈቅድድ ነው” ሲሉ አክለዋል።
ኒቂያ እና ጉባኤው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ያለውን የኢዮቤልዩ ዓመትን ጠቅሰው፥ ቅዱስ ዓመት በተስፋ ጭብጥ ላይ የተወሰነ መሆኑን በማስታወስ፥ በዚህ ወቅት ሁለት አስፈላጊ ዝግጅቶች መከበራቸውን እነሱም ወደ እምነታችን መሠረት የሚመልሰን የኒቂያ ጉባኤ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማትኮር ቤተ ክርስቲያንን የሚያበረታ እና በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ደስታ፣ ተስፋ፣ ሐዘን እና ጭንቀት ትኩረት የሚሰጥ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ መሆኑን አስታውሰዋል።
ከእነዚህ መታሰቢያዎች ጋር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንዲሁም በዘመናዊው ዓለም ውስጥ “ወንጌልን መስበክ” በሚል ርዕሥ ከሃምሳ ዓመታት በፊት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ በጽንሰተ ማርያም በዓል ላይ ይፋ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ሠነድ አክለዋል።
ሐዋርያዊ ሠነዱ፥ “የወንጌል አገልግሎት የመጀመሪያው መንገድ ምንም ነገር ሊያጠፋው በማይችል ኅብረት ለእግዚአብሔር የተሰጠ እና ገደብ በሌለው ቅንዓት ለሰዎች የሚሰጥ እውነተኛ የክርስትና ሕይወት ምስክርነት ነው” ሲል እንደሚያስተምር ይታወቃል።
“ይህንንም በከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች አገልግሎቶች ውስጥ እናስታውሰው” ብለው፥ ይህን ማስታወሱ ለእያንዳንዱ ሥራ አስፈላጊ እንደሆኑ እና በኅብረት የሚገለጽ የክርስቲያን ሕይወት ምስክርነት የምናቀርበው የመጀመሪያው እና ትልቁ አገልግሎት ነው” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ተናግረው፥ “እግዚአብሔር አምልካችን ብርሃኑን እንዲያመጣልን እና ለዓለማችንም ሰላምን እንዲሰጥ” በማለት በጸሎት ጠይቀዋል።
ከወንድም ላውረንስ የቀረበ የመጽሐፍ ስጦታ
እንደተለመደው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ የቀርሜሎሳውያን ማኅበር ካኅን የሆኑት ወንድም ሎሬንስ በትንሣኤው ምስጢር ላይ የጻፉትን መጽሐፍ ለቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች አባላት በስጦታነት የሰጡ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቅርቡ በቤይሩት ካደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲመለሱ ባደረጉት ንግግር፥ ይህ መጽሐፍ የእግዚአብሔርን አለኝታነት በጥልቀት ለመረዳት ዋና መንገድ እንደሆነ መጠቆማቸው ይታወሳል።
