ፈልግ

በደቡብ ጣሊያን በሚገኝ የቅዱስ ማርቆስ ቁምስና ውስጥ የሚገኝ የተስፋ እመቤታችን ምስል፥  በደቡብ ጣሊያን በሚገኝ የቅዱስ ማርቆስ ቁምስና ውስጥ የሚገኝ የተስፋ እመቤታችን ምስል፥  

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14፥ የኢዮቤልዩ ዓመት ቢገባደድም የተስፋ ነጋዲያን ሆነን እንቀጥላለን ሲሉ ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. ለሙሉ ዓመት ሲከበር በቆየው የኢዮቤልዩ ዓመት መጨረሻ አካባቢ ለነጋዲያኑ መልዕክት አስተላልፈዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ነጋዲያን ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት ሊገባደድ ጥቂት ቀናት ብቻ ቢቀሩትም ጥልቅ የሆነ ዘላቂ ስጦታ ነው” ብለው፥ ተስፋ የቤተ ክርስቲያንን ጉዞ በማስተካከል ምዕመናን በአዲስ ሕይወት ጉዞአቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስታውሰን መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ቅዳሜ ታኅሳስ 11/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት የኢዮቤልዩ ነጋዲያን ባደረጉት ንግግር፥ የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት ለክርስቲያኖች ያስተዋወቀው መንፈሳዊ ንግደት የማያቋርጥ መሆኑን አስታውሰዋል።

“የኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት ሊገባደድ ጥቂት ቀናት ቀርተዋል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን ዓመቱ የሰጠን ተስፋ የሚያበቃ አይደለም” ብለው፥ ዘወትር የተስፋ ነጋዲያን ሆነን እንቀጥላለን” ብለዋል።

የብርሃነ ልደቱ መታሰቢያ መቃረቡን በማስታወስ በጀመሩት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፥ በክርስቲያናዊ ተስፋ ትርጉም በማሰላሰል፥ የክርስቲያን ተስፋ የተመሠረተው በፍርሃት ላይ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በተገለጠው የእግዚአብሔር ቅርብነት ላይ ነው” ብለዋል።

“ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘እግዚአብሔር ለልጆቹ ቅርብ ነው’ ብለን የምንሰጠው ምስክርነት አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል” ብለው፥ ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚሆን አስረድተዋል።

“በኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታ እንጂ የሚያሰጋን ነገር የለም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የእግዚአብሔር በሥጋ መገለጥ ሕይወትን የሚሰጥ እና ያለማቋረጥ የሚያድስ የመጨረሻ ምልክት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ያለ ተስፋ ሕይወት የለንም

ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ ምዕ. 8:24 ላይ “በተስፋው ድነናልና” ሲል የተናገረውን በመጥቀስ፣ “ተስፋ ግልጽ ያልሆነ ስሜት ሳይሆን ሕያው እና የሚያሳድግ ኃይል ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

“ተስፋ ከሌለ ሞተናል፤ በተስፋ ወደ ብርሃን መጥተናል” ሲሉ ተናግረው፥ ተስፋ ሥነ-መለኮታዊ በጎነት፣ የእግዚአብሔር ኃይል እና ሕይወትን የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

እውነተኛ ጥንካሬ የሚገኘው ከሥልጣን ወይም ከማስፈራራት አለመሆኑን ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “የሚያስፈራራና እና የሚገድለው ኃይል ሳይሆን ነገር ግን ትዕቢት፣ ከባድ ፍርሃት እና ምንም ሊያተርፍ የማይችል ክፋት ነው” ነው ብለው፥ በተቃራኒው የእግዚአብሔር ኃይል ግን ሕይወትን የሚሰጥ በመሆኑ ተስፋ ማድረግ ዘወትር የሚያሳድግ መሆኑን አስረድተዋል።

የምድሪቱን እና የድሆችን ጩኸት ማዳመጥ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የፍጥረትን ጩኸት አስመልክቶ የተናገረውን በማስታወስ፥ የምድሪቱን እና የድሆችን ጩኸት በጥሞና እንዲያዳምጡ ምዕመናንን አደራ ብለው፥ ሃብት በጥቂቶች እጅ ውስጥ እየጨመረ በሚሄድበት ዓለም ውስጥ ያለውን ኢ-ፍትሃዊነት በመጥቀስ፥ እግዚአብሔር የምድርን ሃብት ለሁሉ ሰው እንዲሆን አስቦ መፍጠሩን በማስታወስ፥ “ተግባራችን የተፈጥሮ ሃብትን መስረቅ ሳይሆን ነገር ግን ማሳደግ ነው” ሲሉ በግልጽ ተናግረዋል።

ታሪክ በእግዚአብሔር እና በእርሱ ተስፋ በሚያደርጉት እጅ ነው

መከራም ቢሆን በእምነት ውስጥ አዲስ ትርጉም ይኖረዋል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “እግዚአብሔር መፍጠርን አሁንም እንደቀጠለ እና በተስፋ ላይ የተደገፉት የሰው ልጆች በእርሱ የፈጠራ ሥራ እንዲተባበሩ ተጠርተዋል” ብለው፥ ታሪክ በእግዚአብሔር እና በእርሱ ተስፋ በሚያደርጉት ሰዎች እጅ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

በክርስቲያናዊ ጸሎት ማርያማዊ ገጽታ ላይ ያሰላሰሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ፥ የናዝሬቷ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወትን የሚሰጥ የሕያው ተስፋ ምሳሌ መሆኗን ጠቁመው፥ ምዕመናን በእርሷ ውስጥ ከእኛ መካከል አንዷ እና የምትፈጥር፥ ለእግዚአብሔር ቃል መልክ፣ ሥጋ እና ድምጽ የምትሰጥ መሆኗን ያያሉ” ብለዋል።

“ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገና እንድንወለድ ይፈልጋል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “እንደገና ስንወለድ ሥጋን እና ድምጽን ለእርሱ ልንሰጠው እንችላለን” ብለው፥ ይህም ፍጥረት የሚጠብቀው ልደት እንደሆነ በመግለጽ፥ “ተስፋ ማድረግ ዓለም የእግዚአብሔር ሆኖ ማየት ነው” ሲሉ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

22 Dec 2025, 16:01