ፈልግ

የቡሩንዲ ምዕመናን ለሰላም የሚያደረጉት የጸሎት ዑደት የቡሩንዲ ምዕመናን ለሰላም የሚያደረጉት የጸሎት ዑደት  

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የቡሩንዲ ምእመናን ለተሻለ ዓለም ያላቸውን ተስፋ ሕያው እንዲያደርጉት አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2003 ዓ. ም. በቡሩንዲ የተገደሉት የቅድስት መንበር እንደራሴ ሊቀ ጳጳስ ኮርትኒ መታሰቢያ ላይ ከተገኙት የወንድማማችነት ማኅበር አባላት ጋር ተገናኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ረቡዕ ጥቅምት 12/2018 ዓ. ም. ረፋድ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ካቀረቡት ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀደም ብሎ ቅዱስነታቸው የኢዮቤልዩ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሮም ንግደት በማድረግ ላይ ከሚገኙ የሊቀ ጳጳስ አቡነ ኮርትኒ የወንድማማችነት ማኅበር አባላት ጋር ተገናኝተዋል።

የወንድማማችነት ማኅበሩ በቡሩንዲ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2003 ዓ. ም. የተገደሉትን የሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚካኤል አይዳን ኮርትኒ መታሰቢያ ለመጠበቅ ቁርጠኛ መሆኑ ታውቋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኮርትኒ በቀብር ሥነ-ሥርዓት ላይ ከተገኘ በኋላ ወደ ዋና ከተማዋ ቡጁምቡራ ሲመለሱ በጥይት ተመትተው መገደላቸው ሲታወስ፥ በ500 ዓመታት ውስጥ በተከሰቱ ዓመጾች ምክንያት የሞተ የመጀመሪያው የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ እንደ ነበሩ ታውቋል።

ኢየሱስ የቤተ ክርስቲያን እና የዓለም ተስፋ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዓሥራ አራተኛ ለቡሩንዲ ነጋዲያን ባደረጉት ንግግር፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. እየተከበረ ባለው የኢዮቤልዩ ዓመት ተስፋ ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት በማስታወስ፥ “ተስፋችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው! የቤተ ክርስቲያን እና የመላው ዓለም ተስፋ እርሱ ብቻ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዓሥራ አራተኛ፥ የመንፈሳዊ ነጋዲያኑን የእምነት ተግባር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመገናኘት በድጋሚ የሕይወታቸው እና የዓለም ማዕከል ለማድረግ በጓዛቸውን አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው ለቡሩንዲ ምዕመናን በንግደታቸው ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ወደ ዕለታዊ ግዴታዎቻችሁ የምትመለሱት በተስፋ ተጠናክራችሁ በወንጌል ብርሃን በመታገዝ ለእያንዳንዱ ሰው ሁለንተናዊ ዕድገት ለመሥራት በተሻለ ሁኔታ በመዘጋጀት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።


ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያለው ቤተሰባዊ ቅርበት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዓሥራ አራተኛ፥ የቡሩንዲ ቤተ ክርስቲያን ለሊቀ ጳጳስ አቡነ ኮርትኒ ክብር ላደረገችው ሥራ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኮርትኒ ቡሩንዲ ውስጥ ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች እና ለሰላም ሲሉ ራሳቸውን ለአደጋ አሳልፈው መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

“የቡሩንዲ ምዕመናን በሊቀ ጳጳስ አቡነ ኮርትኒ መታሰቢያ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅርብ ቤተሰብ በመሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በድሆች እና በዝቅተኞች መካከል በተልዕኮ ላይ መሆንን ይፈልጋሉ” ብለዋል።

ለሊቀ ጳጳስ አቡነ ኮርትኒ ክብር ለመስጠት የጤና ማዕከል በመገንባት ላይ ያላቸውን ተነሳሽነት፣ ዕለታዊ የበጎ አድራጎት ተግባራቸው ሐዋርያዊ ጳጳስ በሞቱበት ቦታ የመታሰቢያ ሐውልት መመሥረትን ጨምሮ ሌሎች ተነሳሽነቶቻቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን የጤና ማዕከሉን የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ የሊቀ ጳጳስ አቡነ ኮርትኒ ሐውልት መባረካቸው ይታወሳል።

ተስፋን ሕያው አድርጉት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ የወንድማማችነት ማኅበር አባላትን ለጉብኝታቸው ካመሰገኑ በኋላ ለሥራቸው ብርታት በመመኘት፥ “ለተሻለ ዓለም ያላችሁን ተስፋ ሕያው አድርጉ፤ ከክርስቶስ ጋር በመተባበር ጥረታችሁ ፍሬ እንደሚያፈራ እና ሽልማቱን ለመቀበል ያላችሁን እርግጠኝነት ሕያው አድርጉ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመጨረሻም ለወንድማማችነት ማኅበር አባላት ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን በመስጠት የመላው ቡሩንዲ ሕዝብ አደራን ለመቁጠሪያ ጸሎት እመቤታችን ቅድስት ማርያም ጥበቃ ሰጥተዋል።

23 Oct 2025, 14:43